Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየጥምቀት በዓልን በማይጨው

የጥምቀት በዓልን በማይጨው

ቀን:

በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ዞን የምትገኘው ማይጨው ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ሽር ጉድ ማለት ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ በዓሉ በመላው ትግራይ ክልል ቢከበርም፣ የማይጨው ከተማ ልዩ ድባብ ይላበሳል፡፡ የከተማው ነዋሪዎች እንዲሁም እንግዶች ታቦታቱ ወዳደሩበት ስፍራ ያመሩት ማልደው ነበር፤ በአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ዓውደ ምሕረት የተሰባሰቡት፡፡ ምዕመናን በነጭ የባህል አልባሳት ተውበው፣ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ የሚሉት ብሒል መልካም ማሳያ ሆነዋል፡፡

የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምሥራቃዊ ዞን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ቡራኬ ከሰጡ በኋላ የጥምቀት ሥነ በዓል ተጀመረ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በቀጭን ትቦ ፀበሉን ሲረጩ በጉጉት ይጠባበቅ የነበረው ሕዝብ እንዲደርሰው ይረባረብ ነበር፡፡ ረፋድ ላይ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ በቦታው የተገኙ ሰዎች በደማቅ ሁኔታ በዓሉን አክብረዋል፡፡

ከሌሎች የትግራይ ከተሞች በተለየ ጥምቀት በክልል ደረጃ በማይጨው መከበር ከተጀመረ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ የበዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዳለ ሆኖ በባህላዊ ክንውኖችም የጐብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ መታለሙን ከትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በበዓሉ ዋዜማ ዕለት (ከተራ) የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህል የሚያንፀባርቅ ዝግጅት ተሰናድቶ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ‹‹ቅልስ›› በመባል የሚታወቀው ነጻ ትግል ተካሒዷል፣ ተቀራራቢ ክብደት ባላቸው ወጣት ወንዶች መሀል በሚካሔደው ትግል ጥምቀትን ጨምሮ በተለያዩ በዓሎች የሚዘወተር ነው፡፡ ከነጻ ትግሉ በተጨማሪ የጉማዬ (በራያ አካባቢ የታወቀ ስለተፈጥሮ ሀብት፣ ፍቅር፣ ሐዘንን ወይም ሌላ ስሜት ለመግለጽ የሚውል  ዘፈን) ውድድርም ተከናውኗል፡፡

ዝግጅቱ የተካሔደው በከተራ ዕለት ከሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ ሦስቱ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የሚሔዱበትም ነው፡፡ ምዕመናን ታቦታቱን በዝማሬ አጅበው ቦታሪው ድረስ የሚሸኙበት ሥርዓት አለ፡፡ ሁለቱ ክንውኖች በተመሳሳም ሰዓት መካሔዳቸው ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በጥምቀት ዕለት ንግግር ያደረጉት የአህጉረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጥምቀት በዓል አከባበር መጀመር የነበረበት በዕለቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሥርዓቱ መነሻ መሆን የነበረበት ከጥምቀተ ባሕሩ ሆኖ ሳለ ቅልሱ እንዲሁም የጉማዬ ውድድሩ ታቦታቱ የሚወጡበትን ሰዓት መጋፋት እንዳልነበረበት ተናግረዋል፡፡ ባህሉ ሃይማኖታዊውን ሥርዓት እንዳይጫንም አሳስበዋል፡፡ የጥምቀት በዓልን የሚገልጹ ሥርዓቶች እንዳይደመሰሱ ብለው፣ ሕዝቡ በዓሉን ተከፋፍሎ ሳይሆን በኅብረት ማክበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል በደቡብ ዞን ከሚገኙት ስምንት ወረዳዎች የተውጣጡ የባህል ቡድን አባላት የበዓሉ ተካፋይ ነበሩ፡፡ የየአካባቢያቸውን ባህላዊ አልባሳት፣ አመጋገብ፣ ቁሳቁስና አኗኗር አሳይተዋል፡፡ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች በጥምቀት በዓል ማግስትም በሕዝቡ ተንፀባርቀዋል፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ታቦት ከጥምቀተ ባሕሩ በሚመለስበት ዕለት ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንውኖች ተስተውለዋል፡፡

ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በቡድን በቡድን ሆነው ይጨፍራሉ፡፡ የመቐለ አካባቢ ተወላጆች ከበሮ ይዘው ክብ ሠርተው፣ የራያዎቹ ደግሞ ረዣዥም ዱላዎች ይዘው ይጨፍራሉ፡፡ የ53 ዓመቱ አቶ ሐጐስ ሽፈራው የማይጨው ተወላጅ ናቸው፡፡ በወጣትነታቸው ጭፈራውን እንዲሁም ቅልስ ትግል ይወዱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የቅዱስ ሚካኤል ዕለት ደምቆ ይከበራል፡፡ በጭፈራቸው ስለፍቅር፣ ስለአካባቢው ባህል ያነሳሉ፡፡ የተያዩ ጭፈራዎች ከሚያሳዩ አካባቢዎች የአጋሜ አካባቢ ሆራ ስለስተና የራያ ኮረም ጋፋ ይጠቀሳሉ፡፡

ማይጨው አካባቢ ለጥምቀት ከሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎች ውስጥ ሀይማሎ የተሰኘው አንዱ ነው፡፡ ለጥምቀት አዲስ የተጫጩ ጥንዶችና አዲስ ሙሽሮች ጥቁር ካባና ኮፍያ አድርገው በፈረስ ይዞራሉ፡፡ የራያ ቀሚስ (ቦሬ በመባል የሚታወቀው) የአካባቢው ልዩ መገለጫ ሲሆን፣ ሽፋ (ስአኒ) የሚዘወተረው ጫማ ነው፡፡ ሥነቃል አዘል ዜማዎችና ጭፈራዎች እንዲሁም የማሽላ አገዳ (ጥንቅሽ)ና ወተት ከሕዝቡ ጋር ተያይዘው ይነሳሉ፡፡ አካባቢው የወተት ሀብት የተቸረው በመሆኑ ከምግብነት ባለፈ ለመዋቢያነት የሚውልበት ጊዜም አለ፡፡ የራያ አካባቢ ሰው ‹‹ፀባ ጠገብ›› (ወተት የጠገበ) የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡

ጥምቀትን ለማክበር በማይጨው የተገኘው ሀፍቱ ከበደ ተወልዶ ያደገው አላማጣ ነወ፡፡ በቅቤ የራሰ የራያ ልብስ ለብሶ፣ ዝናር ታጥቋል፡፡ ጐፈሬ ፀጉሩን በባለሁለት ባላ የእንጨት ማበጠሪያው አሁንም አሁንም ያበጥራል፡፡ የራያ ወንዶች ወደ በረሀ አካባቢ በሚሔዱበት ወቅት የሚገለገሉበት ጩቤም በዝናሩ ተሰክቷል፡፡ ረዘም ቀጠን ያለ ዘንግም በእጁ ይዟል፡፡

ጥምቀትን በመሰሉ በዓላትና በሌሎችም ወቅቶች የሚዘወተሩ አለባበሶችና ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለማሳየት ወደ አካባቢው እንደሔደ ይናገራል፡፡ ሌላዋ የበዓሉ ተካፋይ አበባ ገብረሕይወት በአካባቢው ሴቶች እንደየ ዕድሜያቸው በጋሜ፣ አልባሶ፣ ድርማሞና ሌሎችም የሹርባ አሠራሮች እንደሚዋቡ ትናገራለች፡፡

ጥልፍ ቀሚስ ከሚዘወተሩት አልባሳት መሀከል ሲሆን፣ ልዩ ልዩ የአንገት፣ የጆሮ፣ የእጅና የእግር ጌጣጌጦችም ይጥቅማሉ፡፡ ግርኝ ከእግር፣ ዱከት ከእጅ ጌጦች መሀከል ሲሆኑ፣ ፀጉር ላይ የሚሰኩም ጌጣጌጦች አሏቸው፡፡

በበዓሉ ላይ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱና ሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣኖችም ተገኝተዋል፡፡ የደቡባዊ ዞን ባህልና ቱሪዝም አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ታረቀ እንደሚናገሩት፣ የጥምቀት በዓል ለማይጨው ከተማ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አንዳንድ ለውጦች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በብዛት የሚገኙት የአገር ውስጥ ጐብኚዎችና የአካባቢ ተወላጆች ቢሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የቱሪስት ፍሰቱ እንደሚጨምር ያምናሉ፡፡ ማይጨው ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ሀብቶች ቢኖሩም፣ ለበዓሉ የሚሔዱ ሰዎች የሚጐበኙበት አጋጣሚ ውስን ነው፡፡ እሳቸው እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ከተፈጥሮ መስህቦቹ ሓሽንጌ ሐይቅና ሕጉምቡርዳ ጫካ ውጪ ባሉ መስህቦች መሠረተ ልማት አለመዘርጋቱን ነው፡፡

የጐብኚዎች ቁጥር ሲጨምር የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ስለሚያድግ ለውጥ እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡ የጥምቀት በዓልን ልዩ የሚያደርጉ ባህላዊ ክንውኖች ዕውቅና እንደሚያገኙም አክለዋል፡፡ ለበዓሉ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ እንዲሁም በሌሎች እንቅስቃሴአቸው በቂ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የግብዓት እጥረት፣ የባለሙያ አለመሟላትና ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ማነስ እንደሚፈታተናቸውም አቶ ኢያሱ ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው፣ በክልሉ የተለያዩ ከተማዎች በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የተደረገው የየአካባቢውና የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከሃይማኖት በዓላት መካከል መስቀል በዓዲግራት በድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ አሸንዳ ደግሞ በመቐለና ዓቢ አዲ ይከበራል፡፡

የመስቀልና አሸንዳ በዓላት አከባበር ዕውቅና ስላገኙ በርካታ ጐብኚዎች አሏቸው፡፡ ማይጨው የደቡብ ዞን ዋና ከተማ ከመሆኗም አንጻር፣ በዓሉ በከተማው መከበሩ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸው፣ ጥምቀት በማይጨው የበለጠ ሲለመድ እንደሌሎቹ ከተሞች ብዙ ጐብኚዎች እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ በትግራይ ክልል የአክሱም ጽዮን፣ በነጋሽ ደግሞ እንደ መውሊድና አሹራ ያሉ በዓላት ቱሪስት ሳቢ መሆናቸውን ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

በዓላቱ ከውጭ ጐብኚዎች በተጨማሪ የአገሪቱን ተወላጆች ለኢንቨስትመንት በማነሳሳት፣ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞችን ገቢ በመጨመር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ከከተሜነት መስፋፋት እንዲሁም ከጐብኚዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ቱባ ባህሉ እንዳይበረዝ በተለያየ መንገድ ጥንቃቄ ቢደረግም በቂ አለመሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ እሴቶቹን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የሚመለከታቸው በአጠቃላይ መረባረብ እንዳለባቸውም አያይዘው ያነሳሉ፡፡

 

      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...