Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹በእግር ኳስ በአንድ ሌሊት ለውጥ ሊመጣ አይችልም››

‹‹በእግር ኳስ በአንድ ሌሊት ለውጥ ሊመጣ አይችልም››

ቀን:

አቶ ፍሥሐ ወልደ አማኑኤል፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች

በቀደምት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው በርካታ  ተጠቃሽ ተጨዋቾች አሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ከጀመረበት ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ አሻራቸውን ያሳረፉ አይረሴ ተጨዋቾች ይነሳሉ፡፡ ሐረር ከተማ ተወልዶ ያደገውና ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኑሮውን በስድስት ኪሎ አካባቢ በማድረግ ጃንሜዳ አካባቢ እግር ኳስ መጫወት ጀምሮ በክለብ ደረጃ ለአሥር ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ፍሥሐ ወልደ አማኑኤል አንዱ ነው፡፡ በአራተኛው፣ አምስተኛው፣ ስድስተኛውና ሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመካፈል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከአገር ውጪም በመጓዝ በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ በመድረስ የዓለም ኮከብ ከነበረው ፔሌ ጋር የተጫወተ ሲሆን፣ በእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ውስጥ ትልቅ ዝናን ያተረፈው ጆርጅ ቤስት ጋር የመጫወት ዕድል አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተቸገሩና ቤተሰብ አልባ ሕፃናትን በመርዳት ላይና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አቶ ፍሥሐ ወልደ አማኑኤልን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ እግር ኳስ እንዴት ገባህ?

አቶ ፍሥሐ፡- እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከተወለድኩበት ሐረር ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከቤተሰቦቼ ጋር በማምራት ስድስት ኪሎ አካባቢ ኑሯችንን አደረግን፡፡ ስድስት ኪሎ ለጃንሜዳ ቅርብ ስለነበር በቀላሉ ከሠፈር ጓደኞቼ ጋር ለመጫወት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረልኝ፡፡ ጃንሜዳ ስጫወት የተመለከቱኝ ሰዎች በወቅቱ ቡድን ስለነበርና ባሻ ኃይሉን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ከነበሩበት መኩሪያ የሚባል ቡድን በ1953 ዓ.ም. አስገቡኝ፡፡ አስተማሪነት እየሠራሁ መጫወት ጀመርኩ፡፡ በመኩሪያ (ክቡር ዘበኛ) ቡድን አልቆየሁም፡፡ ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመቀላቀል እነመንግሥቱ ወርቁ፣ ይድነቃቸው ተሰማን የመሳሰሉትን የእግር ኳስ ሰዎች ማግኘት ቻልኩ፡፡ ከዛ በኋላ ወደ እግር ኳስ በደንብ መግባት ቻልኩ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለመጀመርያ ጊዜ ከመኩሪያ እግር ኳስ ቡድን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስታመራና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስትመረጥ የነበረህ ስሜት ምን ይመስላል?

አቶ ፍሥሐ፡- በጊዜው በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ተቀባይነት ማግኘት ትልቅ  ደስታ ነበር፡፡ ደግሞ ልክ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መጫወት ስጀምር የተመልካቹ ስሜት በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የነበሩት ስብስቦች በጣም ፈጣንና ጎበዝ ስለነበሩ የሚያጋጥሙንን ቡድኖች ማሸነፍ በጣም ቀላል ነበር፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረን እንቅስቃሴ መሠረት በጊዜው ለነበረው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት እነ ኑሪ፣ ጌታቸውና አብዱ ደምሴ የመሳሰሉ ተጨዋቾች ጋር የመጫወት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ በዚህም ወቅት ከነበሩት ቡድኖች የኤርትራ፣ ሸዋና ድሬዳዋ ቡድኖች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከነዚህም ጋር የሚደረገው ውድድር በጣም ፈታኝና በፉክክር የሚያልቅ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በብሔራዊ ቡድን የነበረኝ ቆይታ በተለይ ከአራተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ እስከ ሰባተኛ የአፍሪካ ዋንጫ የማይረሳና ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በጊዜው ትልቅ ለሚባሉ ክለቦች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተጫወትክ በኋላ ወደ አሜሪካ በማመራት ኑሮህን በዛው አድርገሃል፡፡ ለምን ነበር ከኢትዮጵያ የወጣኸው?

አቶ ፍሥሐ፡- እ.ኤ.አ. በ1969 ወደ አሜሪካ ያመራሁበት ጊዜ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ያመራሁት የነፃ ትምህርት ዕድል በማግኘቴ ሲሆን፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ የነበሩት ጓደኞቼም ከእኔ በኋላ ተከትለውኛል፡፡ በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ዩኒቨርሲቲ በመግባትም አራት ዓመታት በማሳለፍ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማስተርሴን ለመያዝ ችያለሁ፡፡ በአራት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬም ለዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛት ከተውጣጡ ክለቦች ጋር በሚደረግ ውድድር ተካፋይ መሆን ችያለሁ፡፡ በዚህም ጉዞዬ ከፔሌ፣ ከእንግሊዙ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋች ጆርጅ ቤስት እንዲሁም የሃን ክራፍ ጋር የመጫወት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እግር ኳስ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ መሳተፍ ችለሃል፡፡ የእግር ኳስ ዘመንህን ከአሁኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ ጋር እንዴት ታየዋለህ?

አቶ ፍሥሐ፡- በእውነቱ ከሆነ የቀድሞውንና የአሁኑን እግር ኳስን ለማነፃፀር ይቸግረኛል፡፡ በዛ ዘመን የነበረው የእግር ኳስ ዕድገት በጣም ትልቅና ከሌላው ዓለም ያልተናነሰ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ እኛ በዚያ ወቅት ጨዋታ ካደረግን በኋላ 25 ሳንቲም ተሰጥቶን ፍል ውኃ ሄደን እንድንታጠብ ነበር የሚደረገው፡፡ በተቃራኒው ግን የኅብረተሰቡ እንክብካቤና አክብሮት በጣም ትልቅ ነበር፡፡ ክፍያችንም ያው ነው፡፡ ይኼን ስል ግን ያሁኖቹ ክፍያ አያስፈልጋቸውም ማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ሁሉ በዘመኑ ነው የሚመዘነው፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩት ተጨዋቾች እግር ኳሱ ከልባቸው ነው ያለው፡፡ በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ በተለይ በሦስተኛው፣ አራተኛውና አምስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የነበረው ቡድን በሁሉም ሚዲያዎችና በአፍሪካ ታላላቅ አገር ቡድኖች አድናቆትን ያተረፈ ነበር፡፡ እነ መንግሥቱ ወርቁ፣ ሎቻኖ ቫሳሎ፣ ኢታሎ ቫሳሎ፣ ነፀረ ወልደሥላሴ የማይረሱ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ እኛ እግር ኳስን ስንጀምር በትምህርት ቤት በነበረን ብቃት ተመዝነን ነው፡፡ በዚህም መሠረት በትምህርት ቤቶች መካከል የሚደረገው ውድድር በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት የሚገኙት ተጨዋቾችም እንደየብቃታቸው ኤ፣ ቢ እና ሲ ምደብ ውስጥ በመካተት ለተለያዩ ክለቦች ይመረጣሉ፡፡ በእኛ ጊዜ የነበረው ፉክክር በጣም ሰፊ ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በእናንተ ጊዜ ከነበረው እግር ኳስ ይበልጥ የተሻለ እንዲሆን መፍትሔው ምንድነው ትላለህ?

አቶ ፍሥሐ፡- እግር ኳስ ማለት በጣም ጥረት የሚፈልግ ስፖርት ነው፡፡ ለእግር ኳሱ የሚያስፈልገውን እንቅስቃሴና ጥረት ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ ዕቅዶች መተግበር አለባቸው፡፡ ምክንያቱም በእግር ኳስ በአንድ ሌሊት ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ እግር ኳስ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ትኩረት በመስጠት እንደቀድሞ በትምህርት ቤት፣ በአካዴሚ፣ በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ ጊዜ በመስጠት ከሥር መሠረቱ መሠራት አለበት፡፡ ሌላው በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሚባሉት የእግር ኳስ ቴክኒኮች በአግባቡ መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አሠልጣኞቻቸው ከሚሰጡዋቸው ባሻገር በግላቸውም መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አዲስ መዋቅር በማምጣትና የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን በማዘጋጀት የቀድሞ አሠልጣኞችን በማሰባሰብና በማወያየት የተሻለ እግር ኳስ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስክ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ኃላፊነት ተሰጥቶህ ነበር፡፡  ብዙም ሳይቆይ ከኃላፊነት እንድትነሳ የተደረገው ምክንያቱ ለምን ነበር?

አቶ ፍሥሐ፡- እ.ኤ.አ. በ2010 ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የቦርድ ሊቀመንበር ክለቡን በኃላፊነት እንድመራ ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ እኔ በወቅቱ ከቤተሰብ ጋር ስለነበርኩ ክለቡን በኃላፊነት ለመምራት ዝግጁ እንዳልሆንኩ ገለጽኩላቸው፡፡ ከዛ በኋላም በድጋሚ ተደውሎልኝ ጥያቄ ሲቀርብልኝ ምንም ዓይነት ስምምነት ሳላደርግ ኃላፊነቱን  ተቀበልኩኝ፡፡ የሆነ ወቅት ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የዋንጫ ጨዋታ ከደደቢት ጋር ሲያደርግ በዚህ ጊዜ ደደቢት እግር ኳስ ክለብና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ተጨዋች ዝውውር ያለመጠናቀቅ ምክንያት ቁርሾ ውስጥ ስለነበሩ ተጨዋቾቹ ሜዳ ውስጥ አግባብ ያልሆነ ነገር በመሥራት ጨዋታው እንዲረበሽ ምክንያት ሆኑ፡፡ ከዛም በዕለቱ የነበረው የመሀል ዳኛ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጨዋች በቀይ ካርድ አስወጣ፡፡ በዳኛውም ላይ ጉዳት በመድረሱ ተጨዋቾቹ የገንዘብና የዓመት ዕገዳ ደረሰባቸው፡፡ ይኼን በተመለከተ ኮሚሽነሮች ጋ በመቅረብ ምንም እንኳን ሥርዓት በእግር ኳስ ውስጥ ወሳኝ ቢሆንም ቅጣቱ ሚዛናዊ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ በዚህ መካከል ጋዜጣችሁ ስለ ተነሳው ችግር ለጠየቀኝ ጥያቄ የሰጠሁት መልስ በአግባቡ አይደለም በማለት ክለቡ ከኃላፊነቴ መነሳቴ ተነገረኝ፡፡ እስካሁን ግን ከዚህ ውጭ በምን ምክንያት ከኃላፊነት እንደተነሳሁ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ ክለብህ ቅዱስ ጊዮርጊስ 80ኛ ዓመቱን ክብረ እያከበረ ይገኛል፡፡ በዚህም ክብረ በዓል ላይ ሲምፖዚየም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሲምፖዚየሞችን ማዘጋጀት ምን ጠቀሜታ አለው ብለህ ታስባለህ?

አቶ ፍሥሐ፡- በእውነት ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ሲምፖዚየም ማዘጋጀት በጣም ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ክለቦች ትልቅ ታሪክ ነው ያላቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ80 ዓመታት ጉዞ ውስጥ የተለያዩ አጋጣሚዎችን አሳልፏል፡፡ 80 ዓመቱን እንዴት እንዳሳለፈ፣ ምን እንዳሳካና ምን እንዳላሳካ የሚማርበትና ያለፉትን የክለቦቹ ሰዎች የሚያወሳበት መድረክ ነው፡፡ በዚህም ሲምፖዚየም ተካፋይ ስለነበርኩ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በተቃራኒው በነዚህ ዓመታት ውስጥ የስታዲየም ግንባታ አለመደረጉ የሚያስቆጭ ነገር ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌሎችም ክለቦች እንደዚህ ዓይነት ልምድ ቢኖራቸው መልካም ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ለወደፊት በእግር ኳስ ውስጥ ለመሥራት ያቀድከው ነገር ካለ?

አቶ ፍሥሐ፡- አሁን ዕድሜዬ ወደ 76 ተጠግቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከ13 ዓመታት  ወዲህ ቤተሰብ አልባ የሆኑ ልጆችን እየረዳሁ ነው፡፡ በአሜሪካም ከ32 ክለቦች የተወጣጡትን የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡ ስለዚህ ኑሮዬ አንዴ ኢትዮጵያ አንዴ ደግሞ አሜሪካ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሠልጣኝነት ልሥራ ብል የምችል አይመስለኝም፡፡ ግን ባለኝ ዕውቀት የተቻለኝን ባደርግ ደስ ይለኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...