ኧረ ጎበዝ መግባባት እያቃተን ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በመዝናኛ፣ በሚዲያ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ ወዘተ. ሐሳብ መለዋወጥ እየከበደ ነው፡፡ በተለይ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ በሚዲያ ሳይቀር መላ ቅጡ እየጠፋ፣ የቋንቋ ሥርዓቱ እየተመሳቀለና የአነጋገር ዘይቤው እየተቀያየጠ መደናገር በዝቷል፡፡ በተለያዩ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችም ሆነ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቋንቋው ፍርክስክሱ እየወጣ ነው፡፡ ያውም በተናጋሪዎቹ፡፡
በቀደም ዕለት አንዲት የሬዲዮ ፕሮግራም አስተናጋጅ ከሚደውሉልላት ሰዎች ጋር ስትነጋገር በተደጋጋሚ፣ ምላሷን እየደረበች የእንግሊዝኛ ወይም የፈረንሣይኛ ዘዬ ባለው አነጋገር የምታወጣቸው ድምፆች አይሰሙም፡፡ የእኔ ጆሮ ችግር ይኖርበት ወይ ብዬ በአካባቢዬ ያሉትን ሰዎች ስጠይቃቸው መልሳቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ‹‹ምን እንደምታወራ አይሰማም፤›› የሚል፡፡ እኔን የገረመኝ የፕሮግራሙ ወይም የሬዲዮ ጣቢያው ኃላፊዎች ቁጥጥር ማነስ ወይም መጥፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በኋላም ልጅቷ ብሶባት ቀጥላለች፡፡
እሷም ሆኑ ሌሎች የሬዲዮና የቴሌቪዥን አስተናጋጆች ‹‹ከ›› የሚባለውን ፊደል የማይገባው ቦታ እየደነጎሩ፣ ‹‹እንዴት ነክ? እኔ ምልክ? መጣክ፣ በላክ፣ …›› እያሉ ለመስማት የማይመቹ መንቻካ ቃላትን ይደረድራሉ፡፡ ‘እንዴት ነህ? እኔ ምልህ? መጣህ? በላህ?…’ ተብለው መጠራት ያለባቸው ቃላት ከየትኛው መዝገበ ቃላት እየተሸመጠጡ እንደሚመጡ አይገባኝም፡፡ ይኼ ዓይነቱ ሃይ ባይ ያጣ ድርጊት በፌስቡክ ታዋቂ ጸሐፊዎችና በየጎዳናው ላይ በሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ላይ ሳይቀር በስፋት እየታየ ነው፡፡
ቋንቋ ለመግባቢያነት የሚያገለግል ነው ተብሎ ዝም የሚሉት ነገር አይደለም፡፡ ከቃላቱ ጀምሮ እስከ ዓረፍተ ነገር አሰካክና ሰዋሰው ድረስ ያሉት ጉዳዮች በሙሉ በሥርዓት እንዲመራ ያደርጉታል፡፡ በዘፈቀደ እንዳሻቸው በሚዲያ ላይ ጆሮን በሚጎረብጡ ቃላት አዕምሮን ማናወፅና ንግግርን ‘መከካት’ ነውር ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ወረርሽኝ ዓይነት ‘እወድሀለሁ’ ለማለት ‘እወድሀለው’፣ ‘እመጣለሁ’ ለማለት ‘እመጣለው’ የሚሉ አስገራሚ ቃላት የካሴትና የሲዲ ልባሶች ላይ ማየት ተጀምሮ ይቆማል ሲባል፣ በዚያው ተገፍቶበታል፡፡ ለምን? ተቆጪና ገሳጭ የለማ፡፡
በቅርቡ አንድ የሚመረቅ ፊልም ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቼ የፊልሙ ዳይሬክተሮች፣ ፕሮዲዩሰሮችና ታዋቂ የሚባሉ ተዋንያን ሲናገሩ የሰማሁት ደግሞ የበለጠ ያበግናል፡፡ በእርግጥ ብዙዎቹ ፊልሞቻችንና ሙዚቃዎቻችን የቋንቋ ድህነት ያለባቸው ናቸው፡፡ በአካል ተገኝቶ ባለቤቶቹን በእነዚያ እንኩሮ ቃላት የተቀነባበሩ ንግግሮቻቸውን ደግሞ መስማት ያበሳጫል፡፡ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ሊቃውንት ባሉበት አገር ውስጥ በተበላሸ ቋንቋ የተሠሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዞ መቅረብ እብደት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ ይህንኑ ጉዳይ አንስቼ ሰዎቹን ስወቅሳቸው አንዷ ታዋቂ ነኝ ባይ ተዋናይ፣ ‹‹በእናትክ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ በማተኮር ስህተት ፈላጊ አትሁን…›› ስትለኝ ትቼ ከመሄድ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡
የቋንቋ ሥርዓትን እየደፈጠጡና ትውልዱን እያላሸቁ፣ ‹‹… ጥቃቅን ነገር ላይ አታተኩር…›› መባል ከተጀመረ አካፋ በእርግጥም አካፋ መባል አለበት፡፡ በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ የሚደመጡ ዜናዎችን ልብ ብላችሁ ስሙ፡፡ ብዙዎቹ ሥርዓተ ነጥብ እስከመኖሩም አያውቁም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ቃላት መምረጥ አይችሉም፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በተበላሹና በተወላገዱ ሐረጎችና ዓረፍተ ነገሮች የተጀቦኑ፣ ነገር ግን ለመረዳት አዳጋች የሆኑ ነገሮች ያወራሉ፡፡ በዚህ ላይ እነ ‘ከ’ ማጣፈጫ ይመስሉ በቃላት መካከል ይመላለሳሉ፡፡ ለጆሮ የሚከብዱ የንግግር ዘዬዎች ያለ ተቆጣጣሪ ይፈሳሉ፡፡
እኔ የቋንቋ ባለሙያ ባልሆንም፣ ከረጂም ጊዜ ልምድና የንባብ ባህል ያዳበርኩት የራሴ ዕውቀት አለኝ፡፡ አንድ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያን በዚህ ረገድ ለምን ዝም ይባላል ስለው፣ ‹‹የሚያዳምጥ ሲኖር እኮ ነው? ይህ ጉዳይ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማትም ሆነ የትምህርት ተቋማት ሲነገር አዳማጭ የለም፡፡ አንዳንዴ ይህንን የአገር ችግር ብለህ ስታነሳ፣ ተማርን የሚሉት ጭምር ቁምነገሩ መልዕክቱ እንጂ የቋንቋው አይደለም እያሉ ያራክሱታል፤›› አለኝ፡፡ በበኩሌ ይኼንን አባባል አልቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ቋንቋን ማበላሸት መምከን እንጂ ዕውቀት አይደለም፡፡ ይልቁንም እንዲህ የሚያስቡ ካሉ አይደመጡ፡፡ ቋንቋን እንደ እሬት እያመረሩ መልዕክቱን የሚያፋልሱ ትምህርት ይሰጣቸው፣ ወይም ለቋንቋው ባለቤቶች ዕድሉ ይሰጥ፡፡ በለፍዳዳ ንግግሮችና በተበላሹ ቃላት ጆሮአችን አይደንቁር፡፡ (ደረጀ አያልነህ፣ ከልደታ)