Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የፓሪስ ስምምነት በአብዛኛው የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበረ ነው››

ዶ/ር ሙሉጌታ መንግሥት አያሌው፣ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተባባሪ አማካሪ

ዶ/ር ሙሉጌታ መንግሥት አያሌው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተባባሪ አማካሪም ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ በዩሮፒያን ሎው ኤንድ ኮምፓራቲቭ ሎው ቤልጅየም ከሚገኘው ጌንት ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቁ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ሱሬይ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀዋል፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲና በሱሬይ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ስለምታራምደው አቋምና ዓለም አቀፋዊ ገጽታው በተመለከተ ዶ/ር ሙሉጌታን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በፓሪስ በተደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ በተለያዩ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ እነዚህን ስምምነቶች ከኢትዮጵያ መቀበሏ ምን ያህል ተጠቃሚ ያደርጋታል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የፓሪሱ ኮንፈረንስ ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ ወደ መጨረሻ ላይ ጫፍ ላይ ደርሰው በተወሰደ ደረጃ መቋጫ ያገኙበት ዓለም አቀፍ መድረክ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1992 የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ የስምምነት ማዕቀፍ በሪዮ ዲጄኔሮ ተፈርሟል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1997 ኪዮቶ ፕሮቶኮል ተፈረመ፡፡ በዋናነት ሁለቱ ስምምነቶችና በእነሱ ዙሪያ ያሉ ፈራሚ አገሮች ጉባዔዎች ሲካሄዱ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች አሉ፡፡ እነዚህ ውሳኔዎችና ስምምነቶች ናቸው በዋነኛነት የአየር ንብረት ለውጥን እየገዙት ያሉት፡፡ ነገር ግን በቂ አልነበሩም፡፡ ችግሩን በአጥጋቢ ሁኔታ ለመፍታት ስላልተዋቀሩ አዲስ ስምምነት ያስፈልጋል የሚለው ብዙ አገሮችን አስማምቷል፡፡ ይኼን አዲስ ስምምነት ለመደራደር እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 ኮፐንሃገን ላይ በተካሄደው ስብሰባ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ደርባን ላይ በተካሄደው ስብሰባ ድርድሩ እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡ አሁን የተቋጨው ይህ አዲስ ጅምር ነው፡፡

ኢትዮጵያና የአየር ንብረት ለውጥ ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭና ተጎጂ ከሚባሉ አገሮች አንደኛዋ ናት፡፡ ይኼ የሆነበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከጂኦግራፊ አንፃር አገሪቱ ያለችበት ቦታ በራሱ ለተጋላጭነቷ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ያላት የኢኮኖሚ መዋቅርና የልማት ደረጃ ለተጋላጭነቱ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የዓለም የሙቀት መጠን ሲጨምር ኢትዮጵያ ውስጥም ይጨምራል፡፡ ከ1960ዎቹ ወዲህ የተደረጉ የሙቀት መጠን መለኪያዎች እንደሚጠቁሙት አማካይ የሙቀት መጠኑ ከአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ጨምሯል፡፡ የዝናብ ሥርጭትን ብናይ ደግሞ አጠቃላይ በአገሪቱ ደረጃ የዝናብ መጠኑ ባይቀንስም እንኳን፣ በወቅትና በአንዳንድ አካባቢዎች ሲታይ ዝቅተኛ ዝናብ እያገኙ ያሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ አሁን ቡና የሚያበቅሉ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የዝናብ መጠን እያገኙ ነው፡፡ ሥርጭቱ ላይ ለውጥ አለ፡፡ ዝናብ ዘግይቶ ይመጣል፣ ቶሎ ያቋርጣል፡፡ ስለዚህ የዝናብ አመጣጥን መገመት አይቻልም፡፡ በረዥም ጊዜ ልታገኘው የምትችለውን ዝናብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታገኘዋለህ፡፡ በዚህ ምክንያት የጎርፍና የድርቅ አደጋ ይከሰታል፡፡ ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ በየሦስትና አምስት ዓመቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው፡፡ የድርቅ ድግግሞሹ እየጨመረ ነው፡፡ መጠኑም እየከፋ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን የግብርና ዕድገት፣ የሰብል ምርትና የከብት እርባታን በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ያለ ክስተት ነው፡፡ ልማት ላይ የምታወጣቸው ወጪዎች፣ ኢንቨስትመንቶችና የምትገነባቸው መሠረተ ልማቶች የአየር ንብረት ለውጥን ግምት ውስጥ አስገብተው ካልተፈጸሙ የልማት ዕድሎቹ ወደኋላ የመመለስ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልማትን ልታቅድ የምትችለው አየር ንብረት ለውጥን ግምት ውስጥ አስገብተህ ነው፡፡ የልማትህ ትልቁ መሰናክል የሚሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ግምት ውስጥ በማስገባት በአገር ውስጥ የሚታቀደውና የሚሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ችግሩ እንዲፈታልህ ትፈልጋለህ፡፡ ምክንያቱም ግንባር ቀደም ተጋላጭ አገር ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የምትሳተፈው የችግሩ ግንባር ቀደም ተጋላጭ አገር ስለሆነች ነው፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ደግሞ ግንባር ቀደም መናገር ያለባት አገር ናት፡፡ ከመናገር አልፎ ደግሞ ምሳሌ የመሆን ሥራ ደግሞ ትሠራለች፡፡ ችግሩን ሌሎች አገሮች ናቸው ያመጡት ብላ ቁጭ አትልም፡፡ በተቻላት መጠን ማድረግ የምትችለውን ለማድረግና ሌሎች አገሮችን ለማንቀሳቀስ ትሞክራለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ አረንጓዴ የልማት መስመርን ነው የምከተለው ብላ ስትራቴጂ አውጥታ እየሠራች ነው፡፡ አረንጓዴ የልማት መስመር ማለት የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ማለት ነው፡፡ የዚህ ሁለተኛ ደረጃ ጥቅም የልቀት መጠንን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2025 ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ለመግባትና ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ ያቀደች ሲሆን፣ የልቀት መጠኗን ግን ያለማሳደግ አቋም ነው ያላት፡፡ እስካሁን ዓለም የመጣበት መንገድ የኢኮኖሚና የልቀት መጠን አብረው እንደሚሄዱ ነው የሚያሳየው፡፡ ኢትዮጵያ ግን የልቀት መጠኗን ባለበት ለማቆየት ነው ያቀደችው፡፡ ታዳሽና ንፁህ የተፈጥሮ ሀብት ስላለን እሱን በመጠቀም ማድረግ ይቻላል ብለን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ በረዥም ጊዜ ርቀት የሚጠቅመን ይኼ አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ ሀብታችንን ከሸረሸርነው መካከለኛ ገቢ ብንደርስም የመመለስ አደጋ አለው፡፡ በመንግሥት ዕቅድ ኢትዮጵያ ከመካከለኛ ገቢም በላይ የመሄድ ራዕይ አላት፡፡ ለዚህ ዘላቂ የሆነ የልማት መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ኢትዮጵያን የሚጠቅማት ስምምነት ራሷን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር አጣጥማ እንድትሄድ በቂ ድጋፍ ማንቀሳቀስ የሚችል ስምምነት ነው፡፡

ሁለተኛ ችግሩን ከሥሩ ከመሠረቱ ለመፍታት በቂ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስምምነት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የፓሪስ ስምምነት በአብዛኛው የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበረ ነው፡፡ ለምሳሌ የፓሪስ ስምምነት ግልጽ የሆነ አማካይ የሙቀት የልቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ በክፍለ ዘመኑ መጨሻ እንዳይበልጥ ማድረግ፣ ቢቻል ደግሞ ከአንድ ነጥብ አምስት በታች እንዲሆን ማድረግ የሚል ግብ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ሁሉም አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ የፓሪስ ስምምነትን ከሌሎች የሚለየውም ይኼው ነው፡፡ ለምሳሌ የኪዮቶ ፕሮቶኮል ግዴታ የሚጥለው ባደጉና በበለፀጉ አገሮች ላይ ነው፡፡ ይኼ አስተሳሰብ የመጣው ችግሩን ያመጡት ያደጉ አገሮች በመሆናቸው ኃላፊነቱን መውሰድ ያለባቸው እነሱ ናቸው በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የዓለም አሁን ያረጋገጠው ያደጉ አገሮች የፈለጋቸውን ያህል ቢያደርጉ ብቻቸውን ችግሩን ሊፈቱት እንደማይችሉት ነው፡፡ አማቂ ጋዞችን የሚለቁ ፋብሪካዎች ካደጉ አገሮች ወደ በማደግ ላይ ወዳሉ አገሮች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ስለዚህ ችግሩን በተሟላ ሁኔታ ለመፍታት ሁሉም አገር አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት የሚል እሳቤ መጥቷል፡፡ ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያንም የሚጠቅም ነው፡፡ አሁን ፓሪስ ላይ በተደረገው ስምምነት በአየር ንብረት ለውጥ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ 190 የሚሆኑ አገሮች አስተዋጽኦ እናደርጋለን ብለው አሳውቀዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ ከማለቷ በፊት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ብዙም ውጤታማ እንቅስቃሴ አላደረገችም ተብላ አልፎ አልፎ ትተቻለች፡፡ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንድትሰጥ ያደረጋት መነሻ ጉዳይ ወይም ጉዳት ምንድነው?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ይኼ አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩ መስተካከል ያለበት ነው፡፡ በቅርቡ ወይም አሁን የተከሰተ መነቃቃት ወይም የፖሊሲ ዕርምጃ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሽግግሩ ጊዜ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ ስትራቴጂ አውጥታ ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና አካባቢ ጥበቃን ይመለከታል፡፡ ከዚያ በኋላ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲና ስትራቴጂ አውጥታለች፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ብዙ ሕጎችን በአካባቢ ጥበቃ ላይ አውጥታች፡፡ የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚያተኩሩ የተለያዩ ስትራቴጂዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ አወጣጥና የማስፈጸም አካሄድ ብዙ ጊዜ የሚያተኩረው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋነኛው የአካባቢ ችግር እሱ ነበር፡፡ ችግሩ ከኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዋናው የኢኮኖሚ መሠረታችን ግብርና ነው፡፡ ግብርና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ግብርና ለረዥም ጊዜ እያሽቆለቆለ ወይም ዕድገት ሳያሳይ የቆየው የተፈጥሮ ሀብት መሠረታችን እየተሸረሸረ በመምጣቱ ነው፡፡ በአፈር መሸርሸር፣ በደን መመንጠርና መመናመን የተነሳ ግብርናው ምርታማነቱ እየቀነሰ መምጣቱ እዚያ ላይ እንድታተኩር ያደርግሃል፡፡ ስለዚህ ያለ ደን ልማትና ጥበቃ ግብርና የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለች በተደጋጋሚ ትገለጻለች፡፡ 12 ዓለም አቀፍ የወንዞች ተፋሰሶች አሏት፡፡ ግን እነዚህ የውኃ ሀብቶች ያለ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ያለ ደን ልማት በዘላቂነት ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ለኢኮኖሚ ልማት፣ ለኃይል ምንጭና ለግብርና ዕድገት የግድ የአካባቢ ጥበቃ ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ የምናደርገው ከልማት ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡ የተጀመረውም ቆየት ብሎ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1992 ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ትሳተፍ ነበር፡፡ አንዳንድ አገሮች በአካባቢ ጥበቃ ላይ መነቃቃት የሚያሳዩት አንድ የሆነ የአካባቢ አደጋ ሲከሰት ነው፡፡ ያኔ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ ይጀምራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን በአንድ በተከሰተ አደጋ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ አብሯት በቆየ ድህነትና የአካባቢ ጥበቃ ችግር በመነሳት ነው ለችግሩ ትኩረት የሰጠችው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትም ለረዥም ጊዜ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በኮፐንሃገኑ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል ከፍተኛ ሚና ከተጫወተች በኋላ ለአካባቢ ጥበቃ ስሟ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ነገር ግን በተግባር የአገሪቱ ይዞታ የተጎሳቆለ በመሆኑ ጉዳዩን እንደ ተቃርኖ ያዩት ነበሩ፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ተቋማት በተግባር የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በጣም አበረታች ውጤቶች መጥተዋል፡፡ ይኼ በሁሉም  ክልሎች ሳይሆን በአንዳንድ ክልሎች የተስተዋለ ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን አበረታች ሥራዎችና መልካም ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የማዛመት ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ትግራይን ለአብነት ብንወስድ ሰፊ የሆነ ነዋሪውን የማንቀሳቀስና አካባቢን መልሶ የማቋቋም ሥራ ተሠርቷል፡፡ በጣም የተራቆተ አካባቢ መልስ እንዲያገግም፣ የጠፉ ዛፎች እንዲበቅሉ፣ አካባቢውን ከሰውና ከከብት እንቅስቃሴ በመገደብ ድሮ የነበሩ ሥነ ምኅዳሮች እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳዎች በሽሬ አካባቢ እንዲመለሱ ሁሉ ተደርጓል፡፡ የእርከን ሥራ፣ የአፈረና የውኃ ጥበቃ፣ የዛፍ ተከላ ሥራዎች በሰፊው ተሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ በዓመት በአማካይ ከ30 ሰዓታት በላይ ነፃ ጉልበት በእነዚህ ሥራዎች ላይ ያበረክታል፡፡ ስለዚህ ዕውቅናው ከተገኙ ውጤቶችም ጭምር የመጣ ነው፡፡ እርግጥ አሁንም ሰፊ ችግሮች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ በኋላ የአየር ንብረት ለውጥ አዲስ ድርድር እየተደረገ ባለበት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እገነባለሁ ብላ ተነስታለች፡፡ ይኼ በዋናነት መሠረት ያደረገው የአገርን ጥቅም ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግን ዓለም አቀፋዊ አስተዋጽኦም ያደርጋል፡፡ ይኼ ተጨማሪ ዕውቅና እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ ይኼ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሪነት ሚና እንድትጫወት በር ከፍቶላታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 ኮፐንሃገን ላይ ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት ነው ኢትዮጵያ በዚህ ላይ እንቅስቃሴ ያደረገችው፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ አፍሪካ በተናጠል ተደራድራ የምታመጣው ውጤት በጣም ትንሽ ስለሚሆን፣ እንደ አኅጉር በተቀናጀ መንገድ በአንድ ድምፅ መደራደር አለብን የሚል አቋም በተለያዩ መድረኮች ታንፀባርቃለች፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ አቋም ነው የነበራት፡፡

በዚህም መሠረት ሊቢያ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ርዕሰ ብሔሮችና ርዕሰ መንግሥታት ስብሰባ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ ይህንኑ ሐሳብ አቅርበው የአሥር አገሮች መሪዎች ያሉበት ኮሚቴ እዚያው ተቋቁሞ፣ ኮሚቴውን እንዲመሩት አቶ መለስ ተመረጡ፡፡ ከኮፐንሃገኑ ኮንፈረንስ ጀምሮ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት የመሩ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በላይ ቃል አቀባይ ሆነውም አገልግለውታል፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተረክበው ለአንድ ዓመት ተኩል አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ኮሚቴውን ለአራት ዓመታት መርታዋለች፡፡ በዚህም አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እየደረሰባት ያለውን ችግር፣ ለመፍትሔው እየወሰደች ያለውን ዕርምጃ ለማስተዋወቅ ጥራለች፡፡ በመሠረቱ የኮሚቴው ሊቀመንበር በየሁለት ዓመቱ በተራ ይቀያየራል፡፡ አቶ መለስ እንዲቀጥሉ የተደረገውና ለአራት ዓመታት እንዲሠሩ ተመርጠው የነበረው በጣም ልዩ የሆነ ሥራ ስለሠሩ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ ታንዛኒያ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት መራችው፡፡ አሁን ተራው የግብፅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የግብፅ ፕሬዚዳንት በፓሪስ የአፍሪካ የመሪዎች ኮሚቴን ወክለው የሄዱት፡፡ ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ተባብራ መሥራቷን አላቆመችም፡፡ በባለሙያዎች ደረጃና በሚኒስትሮች ደረጃ በሚደረጉ ድርድሮች ሁሌ የአፍሪካ ቡድን አባል ሆነን እንሳተፋለን፡፡ በፓሪሱ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር በዋናነት የሙቀት መጠኑ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንቲግሬድ መሆን አለበት የሚለው የአፍሪካን ጥቅም የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኮፐንሃገን ጉባዔ አፍሪካ ባደጉ አገሮች ይበልጥ የተጎዳች በመሆኗ ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚለውን አቋም በኢትዮጵያ በኩል ይዛ ቀርባ ነበር፡፡ በፓሪሱ ጉባዔ ደግሞ በሁሉም አገሮች ላይ ኃላፊነት የሚጥለውን ስምምነት ፈርማለች፡፡ ይኼ የአቋም ለውጥ ለምን መጣ? የኮፐንሃገኑ ስምምነት ውጤትስ የት ደረሰ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የመንፈስ ለውጥ አለ፡፡ የበፊቱ ካሳና የክስ መንፈስ ነበረው፡፡ የአየር ንብረት ችግር በእርግጥ ታሪካዊ ችግር ነው፡፡ በአብዛኛው ችግሩንም ያመጡት ያደጉና የበለፀጉ አገሮች ናቸው፡፡ እነዚሁ አገሮች አቅምና ቴክኖሎጂው ስላላቸው ኃላፊነቱን ብቻቸውን ይወጡ የሚል ነበር፡፡ ይኼ አባባል የካሳና የክስ መንፈስ አለበት፡፡ የፓሪሱ ስብሰባ ይኼንን መንፈስና ቃና በተወሰነ መልኩ የሸረሸረ ነው፡፡ አሁን የትብብር መንፈስ ጎልብቷል፡፡ ችግሩን ያመጡት ያደጉ አገሮች ቢሆኑም ችግሩን ብቻቸውን ሊፈቱት አይችሉም፡፡ ከቻላችሁ ፍቱት ካልቻላች የራሳችሁ ጉዳይ አትልም፡፡ ምክንያቱም አንተ ነህ የምትጎዳው፡፡ የመሪነት ሚናውን ያደጉ አገሮች ቢወጡም ግን ሁሉም አገሮች በተቻለ መጠን አስተዋጽኦ ያድርጉ ወደሚለው ተመጥቷል፡፡ ይኼ የወንድማማችነትና የትብብር መንፈስ ነው፡፡ በተወሰነ መንገድ ገንቢ ነው፡፡ የበፊቱ ያደጉ አገሮችን ተከላካይ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁን ግን ኑ እንተባበርና የጋራችንን ችግር አብረን እንፍታው የሚል በመሆኑ የተሻለ ነው፡፡ ኮፐንሃገን ላይ ቃል የገቡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አልተወጡም ማለትም አይቻልም፡፡ የገንዘብ ድጋፍ እየተሰጠ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን ግሪን ክላይሜት ፈንድ የሚባል የተቋቋመ አለ፡፡ ወደፊት ብዙ ቢሊዮን ብር ያንቀሳቅሳል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ግን አሁን ለመነሻ ያህል ከበለፀጉ አገሮች አሥር ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ ችሏል፡፡ በፓሪስ ስብሰባ ላይ አፍሪካን ሪኒዌብል ኢነርጂ ኢንሺየቲቭ የሚባል ፕሮግራም እንደዚሁ አፍሪካ ውስጥ ያለውን የታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅምን እ.ኤ.አ. በ2020 ብቻ 20 ጊጋ ዋት፣ በ2030 ደግሞ 300 ጊጋ ዋት የማድረስ ዓላማ ያለው በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል የሚፈጸም ኢኒሺየቲቭ ይፋ ተደርጓል፡፡ አስቀድሞ የአሥር ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ቃል የተገባለት ነው፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ፍሰት አለ፣ ግን በቂ አይደለም፡፡

ያደጉ አገሮች ቃል የገቡትን መቶ በመቶ አይፈጽሙትም፡፡ ይኼ የእምነት መጓደል ያመጣል፡፡ ቁርጥ የሆነ የመክፈያ ጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡ ፓሪስ ላይ የታየው ይኼ ነው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2025 በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር የማሰባሰብ ዕቅድ ተነድፏል፡፡ ከዚያ በኋላ ፍላጎቱና አፈጻጸሙ ታይቶ ሌላ ግብ ይፋ ይደረጋል፡፡ የእምነት መጉደሉን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የተጠበቀውን ያህል ገንዘብ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ግን ደግሞ ለውጥ አለ፡፡ የኪዮቶ ፕሮቶኮል እ.ኤ.አ. በ1992 የገንዘብ ዕርዳታ መስጠት ያለባቸውን ሀብታም አገሮች ዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን በሒደት አንዳንድ ደሃ አገሮች ሀብታም ሲሆኑ ሌሎች ሀብታም አገሮች ደግሞ ደሃ የሆኑበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ግሪክ ያኔ ከሀብታም አገሮች ምድብ ነበረች፡፡ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር ያሉ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አኅጉሮች እንዲሁም ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ አገሮች አሉ፡፡ ያኔ ደሃ ምድብ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም አሁን የተሻለ አቅም ስላላቸው አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው የሚል አቋምም አለ፡፡ ለምሳሌ ለግሪን ክላይሜት ፈንድ ሜክሲኮና ባንግላዴሽ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ መጠኑ የይስሙላ ነው፡፡ ግን ይህንን እየተፈጠረ ያለ የወንድማማችነት መንፈስ የሚያጠናክረው ይመስለኛል፡፡ በፓሪስ ስምምነት መሠረት ሁሉም አገሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው፡፡ ሁሉም በየአምስት ዓመቱ ይህን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ እያለ ያሳውቃል፡፡ በፓሪስ ስምምነት በሁለተኛው አምስት ዓመት የምታደርገው አስተዋጽኦ በመጀመሪያው አምስት ዓመት ካደረከው አስተዋጽኦ በተራማጅነት ማደግ አለበት፡፡ ግቡ የክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ላይ ሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መድረስ ቢሆንም ያለህ ጊዜ ግን ትንሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በፓሪስ ጉባዔ የአፍሪካ ድምፅ በተገቢው መንገድ ያልቀረበው ጥሩ ተደራዳሪ ስላልነበራት ነው በማለት የሚቀርበውን ወቀሳ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በፓሪሱ ስብሰባ ከማንኛውም ዓለም አቀፍ ስብሰባ በተለየ መልኩ በጣም ብዙ መሪዎች በአንድ የስብሰባ አዳራሽ የተገኙበት የመጀመሪያው ስብሰባ ነው፡፡ ከ150 በላይ መሪዎች ነበሩ፡፡ የብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ንግግር በማድረግ፣ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች፣ ፍላጎታቸውን፣ ጥያቄዎቻቸውን፣ ሥጋታቸውን አሳውቀዋል፡፡ በእርግጥ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አንድ ሰው ሆኖ በመሪ ደረጃ ትኩረት በሚስብ ሁናቴ የተናገረ ላይኖር ይችላል፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ መሪ አገሩን ወክሎ ነው የተናገረው፡፡ የአፍሪካ ወኪል ነኝ ብሎ የተንቀሳቀሰ መሪ አልነበረም፡፡ ያን ያደርጋሉ ተብለው የሚገመቱት የግብፅ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ምክንያቱም የመሪዎች ኮሚቴ ተረኛ ሊቀመንበር እሳቸው ናቸው፡፡ ግን በተለያዩ ፖለቲካዊና ሌሎች ምክንያቶች ይኼ አልሆነም፡፡ በሌላ በኩል በፓሪሱ ስብሰባ መዋቅሩ ተቀይሯል፡፡ በፊት ባለሙያዎችና ሚኒስትሮች ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ ዋናው ስብሰባ ላይ መሪዎች ይመጣሉ፡፡ መሪዎች ለአንድ ሦስትና አራት ቀናት በተለያዩ መድረኮች ይገኛሉ፣ እርስ በርስም ይደራደራሉ፡፡ በአሁኑ የፓሪስ ስብሰባ ግን የመሪዎች ስብሰባ የነበረው አንድ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ የመታየት ዕድል አልነበረም፡፡ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ይህን አውቀው ያደረጉት ለጉባዔው ውጤታማነት ይረዳል በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የአፍሪካን ቡድን በባለሙያዎችና በሚኒስትሮች ደረጃ ከወሰድከው እስከ ዛሬ ከነበሩት ስብሰባዎች ሁሉ የፓሪሱ ኅብረት የታየበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እርግጥ ወደ መጨረሻ አካባቢ አፍሪካ በሚባለው ቡድንና ያላደጉ አገሮች ቡድን መካከል በተወሰነ ደረጃ አለመግባባት ነበር፡፡ ያላደጉ አገሮች ቡድን 48 አገሮች ያሉበት ሲሆን ከዚያ ውስጥ ግማሹ አፍሪካውያን ናቸው፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ፍላጎት ላይ አንዳንድ ግጭት አለ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች የሁለቱም ቡድኖች አባል ናቸው፡፡ በጣም በከፋ ደረጃ ተጋላጭ አገሮች ተብለው ሲዘረዘሩ ያላደጉ አገሮችና ትንንሽ ደሴቶች ተብሎ ሲጠቀስ የአፍሪካ ቡድን እንዲጠቀስ እስከ መጨረሻው ተሟግቷል፡፡ መጠቀሱ የሚጠቅመው የገንዘብና የተለያዩ ድጋፎች ለማግኘት ቅድሚያ ስለሚሰጥህ ነው፡፡ የአፍሪካ ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በአፍሪካ እንደ ቡድን መጠቀስ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ናይጄሪያ መካተታቸውን በተለይ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተቃውመውታል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መርሆዎችን በተገቢው መንገድ ያካተተ ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የሚገጥሙን የአካባቢ ችግሮች ይለያያሉ፡፡ አንዳንድ አካባቢያዊ ችግሮች ዓለም አቀፋዊና ክልላዊ ባህሪ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አካባቢያዊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመሬት መጎሳቆል በተወሰነ መልኩ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ አለው፡፡ የመሬት መጎሳቆል፣ የአፈር መሸርሸር፣ የአፈር ለምነት መቀነስ አካባቢያዊ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን አስመልክቶ ያለን የሕግ ማዕቀፍ ብዙ ጊዜ ከአካባቢያዊ ችግር የተሳበ ነው፡፡ አንዳንድ የሕግ ማዕቀፎች ደግሞ ምንጫቸው ዓለም አቀፍ ስምምነት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ስናፀድቅ ማስፈጸም አለብን፡፡ አንዳንዴ አካባቢያዊ ችግሮችን ለመፍታት ብለህ የውጭ ልምድን ልትወስድ ትችላለህ፡፡ እና አሁን ከአካባቢያዊ ችግሮች አኳያ እስካሁን ብዙ ያልተሠራባቸው ግን ወደፊት ችግር እየሆኑ የሚቀጥሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢንዱስትሪና የከተማ ብክለትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ያለን የኢንዱስትሪ ዕድገት ትንሽ ነው፡፡ ግን ወደፊት ኢንዱስትሪው እያደገ ሲሄድ ችግሩ በዚያው መጠን እየተባዛ ይሄዳል፡፡ የያኔው የሕግ ማዕቀፍ ብቃት ያለው መሆን አለበት፣ የማስፈጸም አቅምህም ማደግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ከፋብሪካዎች የሚወጣ ተረፈ ምርት የውኃ ጥራት ላይ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ምን ማድረግ ትችላለህ የሚለው እንደየአገሩ ነው የሚለያየው፡፡ ምርጥ ተሞክሮ ብለህ የእንግሊዝን የውኃ ሕግ ልትወስድ አትችልም፡፡ ምክንያቱም የእንግሊዝ የውኃ ሕግ ላይ መሠረታዊና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ ገነጣጥለህ የኢንዱስትሪና የከተማ ብክለትን በተመለከተ ልምድ ልትወስድ ትችላለህ፡፡ ዋናው ጥያቄ በኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ማመጣጠን መቻል ነው፡፡ ኢኮኖሚው ሲያድግ የቴክኖሎጂ አቅምህ ያድጋል፡፡ በዚህም ብክለት የመቋቋም ቴክኖሎጂ አብሮ ያድጋል፡፡ የዜጎች ጥያቄም አብሮ ያድጋል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመጣ ካለፈው ዓመት የተሻለ የአየርና የውኃ ጥራት ትፈልጋለህ፡፡ የእንግሊዝ የውኃ ጥራት ቁጥጥር ሕግ ደረጃው ከፍተኛ ነው፡፡ የቴክኖሎጂውና የገንዘብ አቅሙ አላቸው፡፡ ዜጎቻቸውም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን አሟልተው አሁን በየጊዜው የተሻለ አካባቢ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡ ያንን ቀጥታ አምጥተህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ልታውለው አትችልም፡፡ ነገር ግን ከሆነ መጠን በላይ ያለ ብክለት ለኢኮኖሚውም ዕድገት የማይጠቅም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ሕግ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ሁኔታ፣ የገንዘብ አቅም፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ መቀረፅ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አድጎ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ተብሏል፡፡ በአንድ በኩል ይህ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ የሰጠችው ትኩረት ማደግን ያሳያል ብለው የደገፉት አሉ፡፡ በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ሆኖ ልዩ ተሰሚነት የነበረው ሲሆን፣ አሁን ግን እንደማንኛውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ስለሚሠራ አደገ ማለት አይቻልም የሚሉ አሉ፡፡ ለእርስዎ የመወቅር ለውጡ ምን ያሳያል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የመዋቅር ለውጡን ያስነሳው ለረዥም ጊዜ ባለሥልጣን ሆኖ ሲሠራ የተስተዋሉ ችግሮች መኖራቸው ነው፡፡ መዋቅሩ ችግሮቹን ለመፍታት እንደ አንድ ዕርምጃ የታየ ይመስለኛል፡፡ በዋናነት ለውጡ የደን ልማትና ጥበቃ ከግብርና ሚኒስቴር ተነስቶ ወደዚህ ሚኒስቴር መምጣቱ ነው፡፡ የደን ልማትን ለግብርና ሚኒስቴር መስጠት ቀበሮን በግ ጠብቂ እንደማለት ነው በማለት አንዳንድ ሰዎች አስተያየት ይሰጡ ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የደን ምንጠራና መመናመን ምክንያቱ ግብርና ነው፡፡ ግብርናው እያደገ ነው፡፡ የዚህ ምንጩ በአንድ በኩል ምርታማነት መጨመሩ ነው፡፡ ግማሹ ደግሞ የጨመረው የመሬት መጠኑ በመጨመሩ ነው፡፡ የመሬት መጠን ደግሞ ሊሰፋ የሚችለው ደን በመመንጠር ነው፡፡ ስለዚህ ግብርናን እንዲያሳድግ ኃላፊነት የሰጠኸው የመንግሥት ተቋም አብሮ ደን እንዲያለማ መጠበቅ አብሮ የሚሄድ ነገር አይደለም፡፡ ደን ልማት ለረዥም ጊዜ ባለቤት አልባ ነው ይባል ነበር፡፡ አሁን ገለልተኛ ወደሆነ መሥሪያ ቤት ሄዷል፡፡ ይኼ አንዱ ለውጥ ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር ከባለሥልጣን ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አድጓል፡፡ እንደ ባለሥልጣን በተለየ ሁኔታ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር፡፡ አሁን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ለሚኒስትሮች ምክር ቤትም ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቅንጅት ሥራ ይሠራበታል፡፡ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ስለሚገኙ መንግሥት አንድ ዓይነት ማንነት እንዲኖረው፣ የተለያየ ምላስና ራስ እንዳይኖረው እንደ አንድ አካል ሥራውን እንዲሠራ ይረዳዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ እዚያ መወከሉ በፌዴራል መንግሥቱ ያሉ የመንግሥት ሥራዎች ሁሌ የአካባቢ ጥበቃን ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ዕድል ይሰጣል፡፡ ሌላው ደግሞ እንደ እኩል እንዲያዩት ይረዳል፡፡ ከሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚለየው ከሚሠራቸው የቀጥታ ሥራዎች ይልቅ የቴክኒክ ድጋፍና የቁጥጥር ሥራዎቹ ይበልጣሉ፡፡ እነዚያን የቁጥጥር ሥራዎች በተገቢው መንገድ ለመሥራት የብዙ አገሮች ችግር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ጉዳዬ ብሎ የሚወስደው ስለሌለ ይቸገራል፡፡ አሁን ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጠረጴዛ ላይ እኩል ቦታ ስትሰጠው ተሰሚነት ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ይኼ እንደየአገሩ ሥርዓት ይለያያል፡፡ ለምሳሌ የአንግሎ አሜሪካ የፖለቲካና የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን አካል ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ቁጥጥር አንደኛው የመንግሥት ሥራ ነው ብለው የሚያምኑ አገሮች ደግሞ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ገበሬዎችንና ነዋሪዎችን የሚያሳትፍ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተፈጻሚ ሆኗል፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ነበር?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- የደን ልማት የሚከናወንባቸው ብዙ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሴፍቲኔት ፕሮግራም የደን ጥበቃ ክፍል አለው፡፡ በአሳሳቢ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ያለባቸው አባወራዎች በዓመት ለስድስት ወራት የገንዘብና የእህል ድጋፍ የሚሰጥበት ይህ ፕሮግራም በተለይ አቅም ላላቸው ሰዎች በነፃ ድጋፍ አይሰጥም፡፡ የሚሠሩት ሥራ አለ፡፡ ከሚሠሩት ሥራዎች መካከል የአፈርና የውኃ ጥበቃ፣ የደን ጥበቃና ተከላ ሥራ ይካተታል፡፡ ሁለተኛ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ፕሮግራም የሚባል አለ፡፡ የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት ጊዜ ጨርሶ አሁን ሁለተኛው በኦሮሚያና በደቡብ ክልል እየተፈጸመ ነው፡፡ ይኼ በጣም ስኬታማ የሆነ ፕሮግራም ነው፡፡ በአንድ ወቅት መሬት የሚባል ፕሮጀክትም ነበር፡፡ ይኼ በትግራይ ክልል ነው የተከናወነው፡፡ የጠፉ የሚባሉ ዛፎች መልሰው እንዲበቅሉ ያስቻለ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ሰፊና ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ፕሮጀክት ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው በደን ልማት እኩል ያለመሥራት አለ፡፡ አንዱ ክልል ችግሩን ለመቆጣጠር ዕርምጃ ሲወስድና ሲያሻሽል ችግሩ ከመቀረፍ ይልቅ ወደ ሌላ ክልል ሊሸጋገር ይችላል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ልትፈታ የምትችለው የተቀናጀና አገር አቀፍ ምላሽ ሲኖርህ ነው፡፡ በአንድ ወቅት 30 እና 40 ዓመት የነበረው የደን ሽፋን ተሽቆልቁሎ እስከ ሦስት በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ አሁን ባለቤት አግኝቶ በደንብ መሥራት እየተጀመረ ነው፡፡ ወደፊት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲዎች ለማውጣትና ኢንቨስትመንት ለማካሄድ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢና የደን ልማት ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ዓመታት መረጃዎችን ሲያደራጅ ነበር፡፡ የደን ሀብቶቻችን ምን ያህል ናቸው? ዓይነታቸውና ይዘታቸው ምን ይመስላል? የሚለውን ሲያጠናቅር ነበር፡፡ በቅርቡ ባወጣው መረጃ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15 በመቶ መድረሱን ገልጿል፡፡ ይኼ የደን ጥበቃና ተከላ ሥራዎች ውጤት ነው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ከመረጃ አለመሰብሰብ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ የደን ትርጉምም ይወስነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተስፋፋውን ድርቅ ከአካባቢ ጥበቃ ችግር ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ሥራ አልተሠራም በማለት የሚቀርበውን ወቀሳ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- አለመቋቋም አለመቻል ለውጥ የለም ማለት አይደለም፡፡ ተጨማሪ ሥራ መሥራት አለበት አንድ ነገር ነው፡፡ የመቋቋም አቅምን የሚጎዱ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ብቻ አይደለም የመቋቋም አቅምህን የሚረዳህ፡፡ አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ዕድገት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቤተሰብ አቅም ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ኢኮኖሚው በጣም ቢያድግም ዝቅተኛ ገቢ ያለን አገር ነን አሁንም፡፡ ለውጡ በዚህ ከቀጠለ የመቋቋም አቅም ይኖረኛል የሚል መንግሥት ነው ያለው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ 21 ሚሊዮን ሔክታር መሬት መልሶ እንዲያገግም የማድረግ ዕቅድ አለ፡፡ እስከ ዛሬ ተቋማዊ ባለቤትነት አለመኖር ነበር፡፡ ለምሳሌ ክረምት ሲመጣ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤት እየወጣ ዛፍ ይተክላል፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ያህሉ ፀደቀ? ማነው ከዚያ በኋላ የሚንከባከበው? የተተከለበት ቦታ ተገቢ ነው ወይ? በማለት የሚከታተል አልነበረም፡፡ ስለዚህ የተሠራውን ያህል ውጤት ላይኖር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በአንድ በኩል ያለውን የማደግና የመልማት ፍላጎት፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ያለውን የአካባቢ ጥበቃ የሚያመዛዝን አሠራር ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዚህ አሠራር አፈጻጸም ላይ በርካታ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይህን የማስፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በውክልና ለሚመለከታቸው የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መስጠቱን የሚቃወሙ አሉ፡፡ ውክልናው ከአካባቢ ጥበቃ ይልቅ ለኢንቨስትመንት ያጋደለ አሠራር እንዲመጣ አድርጓል የሚለው ወቀሳ ተቀባይነት አለው?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- እዚህ ጉዳይ ላይ በቂ መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን ትልልቅ የሚባሉ ፕሮጀክቶች ከመፈጸማቸው በፊትና ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማድረግ እንዳለባቸው ሕጉ ያስቀምጣል፡፡ ራሱ ፈቃድ ሰጪው አካል ይህንንም ቢያስፈጽም ይሻላል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ግን ደግሞ ውክልና ማለት እንዳሻህ አድርገው ማለት አይደለም፡፡ ውክልና የሚፈጸመው በወካዩ አካል ክትትል ሥር ነው፡፡ ተገቢ ክትትል ማድረግና ድጋፍ መስጠት የወካዩ አካል ድርሻ ነው፡፡ በፊት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አሁን የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እንደ ወካይ አካል ትክክለኛውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ አለበት፡፡ ለውክልናው ግን ምክንያት አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚህ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ፈቃድ ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ፈቃድ ሲሰጡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡ የፍላጎት ግጭት ሊኖር ይችላል፡፡ የደን ልማት እኮ ከግብርና ሚኒስቴር የተዘዋወረው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ከአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጋር የሚያያዘው ሌላው ችግር የአቅም ነው፡፡ በቂ የሆኑና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችና አማካሪዎች ገበያው ውስጥ የሉም፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን ማንኛውም አማካሪ እየሠራው ነው፡፡ የወካዩ አካል የብቃት ችግርም አለ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...