Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ቀጣይ ዕድል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አሻራ የጐላ ነው፡፡ የባንኮች ዕድገት በእጅጉ የሚፈለግና ዕድገታቸውም ቴክኖሎጂዎችን ያገናዘበና የጠነከረ አቅም በመፍጠር ውህደት አስፈላጊነትን ያሳየ እየሆነ ነው፡፡

በኢትዮጵያም በተለይ የግል ባንኮች አሁን ባሉበት የአገልግሎት ደረጃ ያለውን ከፍተኛ ፍላጐት የማያሟላ ብቻ ሳይሆን እያደገ ካለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ቀጣይ ጉዟቸው ዓለም አቀፋዊውን አካሄድ የተከተለ መሆን እንደሚገባው እየተገለጸ ነው፡፡ አቅማቸውን ለማጐልበት ምን መደረግ አለበት የሚለው ጉዳይ ወቅታዊ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡ በቅርቡ 20ኛ ዓመቱን ያከበረው ዳሸን ባንክ በዓሉን ካከበረባቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የተመለከተ የምክክር መድረክ ላይም ይህ ጉዳይ በሰፊው ታይቷል፡፡ በዚህ የውይይት መድረክ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረበው ደግሞ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ነው፡፡ የኩባንያው ማኔጂንግ ፓርትነርስ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኩባንያቸውን ጥናት ለመወያያ ያቀረቡት ጽሑፍ አጠቃላይ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ የተመለከተ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ እውነታዎችንም ከኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ጋር በንጽጽር ያሳየ ነው፡፡  

በተለይ ዘርፉ ቀጣይ ጉዞ ምን መምሰል እንደሚኖሩበት የጠቆሙበትም መድረክ ሲሆን፣ በጥናታዊ ጽሑፉን መሠረት በማድረግ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ከሪፖርተር ጋር ያደረጉት ቆይታም ነበር፡፡ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የዓለምና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ  

 አቶ ዘመዴነህ ለውይይት ባቀረቡት ጥናት መንደርደሪያ ያደረጉት የዓለም ኢኮኖሚን ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ ግብ ምን ይመስላል በሚል ነበር፡፡ ዓለም አቀፋዊ ምልከታው የዓለም ኢኮኖሚና ሌሎች ዓለም አቀፍ (መርሆዎችን ከግምት በማስገባት ዓለማችን ወደ ዝቅተኛ ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ዘመን እየተጓዘች የምትገኝ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም የዓለም አቀፉን የዕድገት ዝግመት በአስገራሚ ሁኔታ ማሽቆልቆል፣ የዮሮ ዞን ኢኮኖሚ ባለበት ሁኔታ የቆመና ለውጥ የሚያሳይ መሆኑ፣ የአሜሪካም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሁለት በመቶው ብቻ እያደገ መቀጠሉ፣ የአዳዲስ ገበያዎች መፈጠርም በተለይም የቻይና ገበያ አዝጋሚነት እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በ2016 የሦስት ነጥብ ስምንት በመቶ ዕድገት ብቻ እንደሚኖረው መተንበዩ አስረጂዎች ሆነው ቀርበዋል፡፡

በተያያዥነትም የሥጋቶች መጨመር መኖሩን ታሳቢ ያልሆኑና ጥንካሬ የሌላቸው ዕድገቶች፣ አነስተኛ ኢኮኖሚያዊ ግሽበት ወይም ድቀት፣ ጂኦፖለቲካዊ ሥጋቶችና አስገራሚ ምጣኔ ሀብታዊ ፖሊሲዎች እየተለመዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም ባደጉ አገሮች ላይ በተደረገው ምልከታ በተለይም በአውሮፓ ኅብረት ያለው ሁኔታ ጠጣር መሆን ተጨማሪ ጥንካሬ እንደሚያስፈልገው፣ የወጪ ንግዱም ከ2010 ጀምሮ የጐላ ያለመሆኑ እንዲሁም የገቢ መጠኑም በተጨናነቀ ሁኔታ ላይ የቆየ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በ2015/16 ዓለም በተለየ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ከግንዛቤ በማስገባት ግዙፍ ሁነቶች መጪውን ጊዜ የሚተነብዩ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ለውጦች እየታዩ ነውም ተብሏል፡፡ ይህ ለውጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የሚመለከት ስለመሆኑ አስታውሰዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ሁኔታ ላይም ልዩነትንና የቅርጽ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ስድስት ግዙፍ ሁነቶች የተለዩ መሆናቸው በጥናቱ ላይ ሰፍሯል፡፡ እነርሱም መጪው የዲጂታል ዓለም ጊዜ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ የኢንተርፕርነርሺፕ (የሥራ ፈጣሪነት) መነሳሳት፣ ዓለም አቀፍ የገበያ ስፍራዎች፣ በዓለም የከተማነት መስፋፋት፣ የምድር ሀብትና ጤና ደግሞ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን፣ እነዚህ ግዙፍ ሁኔታዎች እያንዳንዳቸው አስፈላጊ ቢሆኑም እርስ በእርሳቸውም በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፡፡

መጪው የዲጂታል ዓለም ጊዜ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ቁልፍ ማሳያዎች ናቸው ተብለው ከቀረቡ ማብራሪያዎች ውስጥ ዲጂታል ለውጦች የገቢ መስመሮችን ጨምሮ የቢዝነስ አካሄዶችን በመለወጥ ላይ የሚገኙ መሆኑ ነው፡፡ ኮምፒውተሮችን የመጠቀም ሁኔታ እየቀነሰ የሞባይል መሣሪያዎች መለመድ ዕድገት ማሳየቱ ዓለም ‹‹ቅድሚያ ለሞባይል›› እንዲሰጥ የሚያስገድድ እየሆነ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡ የሥራ ልማዶችና በክህሎቶች የመሰማራት ሁኔታ በዲጂታሉ ዓለም ከፍተኛ የተለዋዋጭነት ሁኔታ የሚታይበት መሆኑ፣ ዲጂታልና የሮቦት ቴክኖሎጂዎች የሠራተኞችን ስፍራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፎካከሯቸው ወይም በመተካት ላይ መሆናቸው በምሳሌነት ቀርቧል፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ስለመሆኑ ከወዲሁ መተንበይ ይቻላል ተብሏል፡፡ በተለይ የባንክ ኢንዱስትሪው ወደ ሞባይል ቴክኖሎጂ መሸጋገር ግድ እያለው ነው፡፡ እንደ አቶ ዘመዴነህ ገለጻ ባንኮች በቴክኖሎጂ መታጠቅ የግድ መሆኑና ዕድሉም ያላቸው መሆኑን ነው፡፡

ሁሉም ሰው ሞባይል እየያዘ መምጣቱ መልካም ዕድል ነው ያሉት አቶ ዘመዴነህ ዲጂታል አገልግሎት በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እያደገና እየተመረጠ ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚከፈተው የባንኮች ቅርንጫፎች አስፈላጊነት እየቀነሰ፤ በሞባይል ቴክኖሎጂ እየተቀየረ ስለሚሄድ ይህ እንዲሆን መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ በተለይ ከአምስት ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞች ይኖራሉና በዚህ በመጠቀም ቅርንጫፍ መክፈቱ ሁለተኛ ነገር ቢሆን ይምረጣል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡  

የኢንተርፕርነርሺፕ ዕድገትም የሚገለጽባቸው መንገዶች በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉ ገበያዎች እየታየ ነው፡፡ የሥራ ፈጠራ ተግባራት አንቀሳቃሾች ከአስፈላጊነት ይልቅ ወደ ምቹ ሁኔታ እየተቀየሩ በመሆናቸውና ከፍተኛ ተፅዕኖ ሥራ ፈጣሪዎች በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉም ሆነ ባደጉ ገበያዎች ላይም ቢሆን በቀጣይነት የሚለዋወጡ የሥራ ዘርፎችን (ቢዝነሶችን) የሚገነቡ በመሆናቸው፣ የወደፊቱ እንቅስቃሴ ከዚህ ጋር መራመድ ይኖርበታል፡፡  

የሥራ ፈጠራ ገጽታ በቀጣይም የማያረጅ መሆኑ በዓለም ላይ ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት ሥራ ፈጣሪዎች ከሃያ አምስት እስከ አርባ አራት ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ፣ ከሃያ አምስት እስከ ሰላሳ አራት ዓመት ድረስ ያለው ዕድሜ ከፍተኛው የሥራ ፈጠራ ተግባር የሚታይበት ወቅት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሚሊዮን ሴቶች በስልሳ ሰባት የዓለማችን ኢኮኖሚ ውስጥ አዳዲስ የሥራ መስኮችን በመክፈት ወይም በአዲስነት በተመዘገቡ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ቢያንስ አርባ ስምንት ሚሊዮን ሴት ሥራ ፈጣሪዎችና ስልሳ አራት ሚሊዮን ሴት ባለሀብቶች በአሁኑ ወቅት አንድ ወይም ከአንድ በላይ ሠራተኞችን በሥራቸው ቀጥረው የሚያሠሩ በመሆኑ፣ የሥራ ፈጣሪነት ገጽታዎች በእጅጉ ወደ ሴትነት ያጋደለ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ለቀጣዩ የባንኮችም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል ተብሏል፡፡     

የኢትዮጵያ ባንኮችና ተስፋና ሥጋት

ለኢትዮጵያዊያን ባንኮች ስኬት ሦስት ቁልፍና አስገዳጅ አጋዦች ተብለው የተጠቀሱ ዘርፎች ቴክኖሎጂ ሰዎችና ሽርክናዎች መሆናቸውን የአቶ ዘመዴነህ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

በተለይ ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ባንኮች መሠረተ ልማቶቻቸውን እንዲያሻሽሉና የአፈጻጸም ቅልጥፍናቸውን ለማጐልበት ወሳኝ ነው፡፡ አዳዲስ የሞባይል ቴክኖሎጂዎች አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራትና ያሉትንም ይዘው መቆየት እንዲችሉ ያግዛቸዋል፡፡ የሞባይል ግኝቶች የዕዳ ሥጋት ደረጃዎችንም ያሻሽላል፡፡ በሰዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስም የደንበኞች አገልግሎትን ለማሻሻልና የአዳዲስ ምርትና አግልግሎት ፈጠራ አቅምን በቢሮዎቹ የፊት ለፊትም ሆነ የጀርባ የሥራ ባልደረቦች ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ባንኮች ፈጠራንና የአፈጻጸም ብቃትን በማጐልበት ረገድ ወደ ሠራተኞቻቸውም ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ሽርክናን (የጋራ ስምምነትን) መገንባት በአክሲዮን የተቋቋሙ ባንኮች ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማትና በሌሎች ዘርፎችም ካሉ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መሥራት የክህሎት ክፍተቶችን በመሙላትና ራሳቸውም የአፈጻጸም አቅም በሚያንሳቸው ጊዜም ሆነ ለደንበኞቻቸው አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለማቅረብ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የዓለም አቀፍም ሆነ አካባቢያዊ ባንኮች ለአዳዲስ ደንበኞች ተደራሽ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ራዕይና ፈጥጦ የመጣው የውህደት ጥያቄ

በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የ2020 ተልዕኮ የለውጥ ዕድሎች በአገር በቀል ውህደቶችና ይዞታዎች መስፋፋት መነሻነት መቀራረብ የአክሲዮን ግብይት (የካፒታል ግብይት) የሚመሠረት መሆን እንደሚገባ በመግለጽ አሁን ያሉት የግል ባንኮች ፊታቸውን ወደ ውህደት በማዞር ጠንካራ ባንክ መፍጠር ይገባቸዋል ተብሏል፡፡ የውጭ ገንዘብ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ የመግባታቸው ነገር የሚታወቅ አይደለም፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ በግልጽ እንዳስቀመጠው ለውጭ ባንኮች ፈቃድ የመስጠት ዕቅድ የለውም፡፡ ከዚህ አንፃር አገር በቀል ባንኮች ጠንክረው መውጣት አለባቸው፡፡   

የአገር በቀል ውህደቶችን ይዞታ መስፋፋት አቅርቦት ከሚስተዋልባቸው ምክንያቶች ውስጥ የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ከኢኮኖሚው መጠን ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑ የሚገለጽ ነው፡፡ ይኸውም ከአገሪቱ ምርታማነት ዕድገት ጋር ሲነጻጸር የባንክ ኢንዱስትሪው ድርሻ ከሃያ በመቶ በታች መሆኑ ነው፡፡

የባንክ ዘርፍ የ2020 ተልዕኮውን እንዲያሳካ የመመርያ ተፅዕኖዎች የተጨመረበት በመሆኑኧ የስኬት ግቡን ያሰፋና የኢትዮጵያም ኢኮኖሚ በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ከመሆኑ በተጨማሪ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሥራ አንድ በመቶ አገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እውን ለማድረግ የአገልግሎት ዘርፉም በበኩሉ ከአሥር በመቶ በላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ለፋይናንስ ተቋማትም የበኩላቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ያስረዱት አቶ ዘመዴነህ፣ ዓመታዊ የተቀማጭ (የቁጠባ) ገንዘባቸው መጠን በአማካይ ከሠላሳ ከመቶው በላይ ዕድገት እያስመዘገበ በመሆኑ እንደተስፋ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ ዝቅተኛው የመጠባበቂያ ካፒታል መጠን በሦት እጥፍ በማደጉ በ2020 ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚደርስና የፋይናንስ ተቋማት በተለይም የባንኩ ዘርፍ አፈጻጸሙን በቅርንጫፎች ማስፋፋት መስክ እስከ 2015 ከሁለት ሺሕ በላይ እንደደረሰ በ2020 በእጥፍ በማሳደግ ከአራት ሺሕ አምስት መቶ በላይ ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑ በዘርፉ ያለውን ተስፋ ያመለክታል ተብሏል፡፡

‹‹የግል ባንኮች የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ መንገድ መከተል አለባቸው፡፡ እርስ በእርስ ተዋህደው ትልቅ ወደመሆን ቢሔዱ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁን ባላቸው አቅም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኩባንያዎችን ፋይናንስ ለማድረግ አቅም የላቸውም፡፡ ተወዳዳሪ መሆን የሚቸግራቸው ብቻ ሳይሆኑ አሁን ያላቸውን አቅም ይዘው መቀጠላቸውም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው ይሄዳል፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ደረጃ ትልቅ ተግዳሮት የባንክ ቁጥጥር እየተጠናከረ የሚሄድ መሆኑ ነው፡፡ ቁጥጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሚሄድ መሆኑ ደግሞ የባንኮች አቅም እያደገ ካልሄደ ችግር ውስጥ ሊከታቸው ይችላል፡፡

ቁጥጥሩ የግድ ካፒታላቸውን እንዲያድጉና ቴክኖሎጂ መጠቀም ያሻል፡፡ ስለዚህ ቁጥጥሩ እየተጠናከረ ውድድሩም የበለጠ እየጠነከረ መሄዱ ግልጽ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም እያደገ ስለሚሄድ ይህንን የሚመጥን ዕድገትና አቅም ማጐልበት ስለሚመጣ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ኢኮኖሚው እየተቀየረ መሄድና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቀ በመሆኑም ለዚያ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች እስካሁን በአትራፊነት የዘለቁት አገልግሎት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ወደፊት ግን የኢኮኖሚ አካሄድ እየተቀየረ ብዙ ካፒታል የሚፈለጉ ዘርፎች ስለሚመጡ በመመርያ ወደ ውህደት ከመጓዛቸው በፊት ከአሁኑ መዋሃዱ ግድ ይሆናል ይላሉ፡፡ ውህደቱም አቅም በማሳደግ ላይ ብቻ ሳይሆን ልዩ የባንክ አገልግሎት የሚፈጠርበትን መንገድ መቅረጽ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ለምሳሌ የእርሻ ባንክ፣ የመሠረተ ልማት ባንክ የመሳሰሉትን በመፍጠር ጭምር ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥምረት ካለ ንግድ ባንክን ጨምሮ ስድስት ወይም ሰባት ጠንካራ ባንኮች መፍጠሩ ጠቀሜታው የጐላ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የሚጠበቁ ተግዳሮቶች

የእስካሁን በኢንዱስትሪው ጉዞ ከግምት ውስጥ በማስገባት ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስልሳ ሦስት በመቶ የኢንዱስትሪው ሀብት የያዘው ተፅዕኖ አድራጊ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑ አንዱ ነው፡፡ መካከለኛ መጠን ያላቸው የግል ባንካችም በጥብቅ መመርያዎች ሥር ሆነውም አወንታዊ ፋይናንሳዊ አቋም ያሳያሉ፣ አነስተኛ ባንኮች በምሥረታ ላይ ያሉ ቢሆኑም ብቻቸውን የወጪዎችን ማሻቀብ፣ የመመርያ ተፅዕኖዎችንና ውድድርን ተቋቁመው የመቀጠል ሥጋታቸው ከፍተኛ ቢሆንም መመዘኛዎችን ለማሟላትና ገበያውን ለማገልገል የሚታገሉ ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የሽግግርና ለውጥ ላይ ስለሚሆን ለዚህም መንግሥትም ሆነ ባንኮች ስትራቴጂዎቻቸውን መገምገም እንደሚጠበቅባቸው ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ይህንንም መሠረት በማድረግ የተለያዩ አገሮች ባንኮች በኢንዱስትሪዎቻቸው ውስጥ ያለውን የባንኮች ሀብት ክፍፍል ስናነጻጽር በኬንያ ስድስት ባንኮች የኢንዱስትሪውን ሃምሳ ከመቶ፣ በናይጄሪያ ስድስት ባንኮች የኢንዱስትሪውን ስልሳ ከመቶ፣ በደቡብ አፍሪካ አምስት ባንኮች የኢንዱስትሪውን ዘጠና ከመቶ እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ስድስት ባንኮች የኢንዱስትሪውን ዘጠና ከመቶና በካናዳ አምስት ባንኮች የኢንዱስትሪውን ሰማኒያ አምስት በመቶ የሚያስተዳድሩ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ግን አንድ ባንክ የኢንዱስትሪውን ስልሳ በመቶ ሀብት የሚያስተዳድር ነው፡፡ ይህም ዓለም አቀፉ አሠራር የሚያሳየው ብዙው የኢንዱስትሪው ሀብት በጥቂት ግን ተወዳዳሪ በሆኑ ባንኮች ዘንድ የተያዘ መሆኑንና በኢትዮጵያ የባንኩ ዘርፍ ግዙፍ ውህደቶችንና ይዞታን በማሳየት ተወዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡

የአክሲዮን ግብይት ሥርዓት የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ አሻሻጭ (ወኪል) ድርጅቶችና ተያያዥ ተቋማት እንዲመሠረቱ የሚያስችል ሲሆን፣ መዋቅሩም እነዚህ ተቋማት በባንኮች ሥር የሚተዳደሩበት ወይም ተለይተው በራሳቸው የተዋቀሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  

ሰዎች እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ ወደ መኖሪያቸው የማይመለሱበት ጊዜ እየመጣ በመሆኑ የተለመደው የባንክ የሥራ ሰዓት ገደብ በቂ የማይሆንበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም የባንክ አገልግሎት በሳምንት ለሰባት ቀናት የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት ሊሆን እንደሚገባው የኧርነስት ኤንድ ያንግ ጥናት አሳይቷል፡፡

በዚህ ጥናት ግምት በ2020 በመጠን እስከ ሃምሳ በመቶ የሚደርሰው የሁሉም ባንኮች ግብይት በሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት የሚፈፀም ይሆናል፡፡

ከባንኮች ጥምረት ባሻገር

የባንኮች የወደፊት አቅጣጫ በመዋሃድ ጠንክሮ መውጣት ከሚለው አመለካከት ባሻገር አገልግሎታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ሊሆን እንደሚገባም የአቶ ዘመዴነህ ጥናት ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች አገልግሎት አካባቢያዊ ራዕይ እንዲኖረው ያስፈልገዋል፡፡ ወደፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አካባቢያዊ ነው የሚሆነው፡፡ ባንኮቿም ይህንን መመጠን አለባቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ባንኮች ካላት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ኃያል ለማድረግ ይረዳል፡፡

እንደ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እየሄዱ መሆኑን በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ ዘመዴነህ፣ እነሱን የሚደግፍ ስለሚሆንም ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መክፈት ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ባንኮች ኢትዮጵያን ዳያስፖራዎች ያሉባቸው አገሮች ቅርንጫፍ መክፈት ይኖርባቸዋል፡፡ ህንዶች ተመሳሳይ ሥራ ሠርተው ውጤት ያገኙበት በመሆኑ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሌሎችም አገሮች ቅርንጫፎች ሊከፈቱ ይገባል፡፡ እንደ ኩባንያቸው ጥናትም በ2020 የተወሰኑት ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ባንኮች በምሥራቅና በአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አኅጉራዊ መገኛቸውን እንደሚመሠርቱ ከዚህ በተጨማሪም ጥቂቶቹ ደግሞ ከአፍሪካም ባለፈ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች በሚገኙባቸው በመካከለኛው ምሥራቅና አሜሪካ መሥራት ይጀምራሉ ብሎ ይገምታል፡፡

በ2025 የተወሰኑት ኢትዮጵያዊያን ባንኮች በአፍሪካ በተለይም በኮሜሳ (COMESA) አካባቢ ጉልህ አካባቢያዊ ሚና የሚኖራቸው ይሆናሉ፡፡ ይህንንም በክፍለ አኅጉሩ ይዞታቸውን በማስፋትና በተፈጥሮአዊ ዕድገታቸው የሚያሳኩት ይሆናል የሚለውን ግምታቸውን አቶ ዘመዴነህ አስቀምጠዋል፡፡ በ2025 ቢያንስ አንድ ኢትዮጵያዊ ባንክ በሰጡት ደረጃው ከሰሐራ በታች ካሉ አሥር ግዙፍ ባንኮች አንዱ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ ሌሎች ከሦስት እስከ አምስት የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ባንካች ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አንድ መቶ ግዙፍ ባንኮች ውስጥ የሚካተቱ የሚለውን ግምትም ጥናቱ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች