የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ይመራ ዘንድ እንዲቋቋም የተወሰነው ምክር ቤት በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሥር ከሚሆን ይልቅ፣ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ክላስተር ሥር ሆኖ ሚኒስቴሩ እንዲቆጣጠረው ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ መቅረቡ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የከተሞች የምግብና የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤትን ለመመሥረት ሐሙስ ጥር 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ፣ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በአቶ መኩሪያ ኃይሌ ነው፡፡ ቀደም ሲል ታስቦ የነበረው እሳቸው የሚመሩት ሚኒስቴር በቀዳሚነት፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሆኖ ምክር ቤቱን እንዲቆጣጠር ነበር፡፡
በአሥር ዓመት ውስጥ 4.7 ሚሊዮን ዜጐችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሙከራ በተመረጡ 11 ከተሞች በመጪው ሐምሌ ወር እንደሚጀመር የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ መዋቅሮችን የመዘርጋትና የሰው ኃይል ቅጥርን የመሳሰሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል፡፡
የከተሞች የምግብ ዋስትናና ሥራ ፈጠራ ስትራቴጂና ፕሮግራም ዝግጅት ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ጴጥሮስ፣ የፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ መመርያዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዜጐች ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው ከፕሮግራሙ ውጪ እንዳይሆኑና በተቃራኒው መግባት የሌለባቸው እንዳይገቡ እንደሚደረግ፣ ለንብረት ምዝበራ የሚንቀሳቀሱ ከተገኙም መቅጣት የሚያስችል ደንብ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በፕሮግራሙ አተገባበር ባለድርሻ አካላት ተብለው የከተሞች የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ላይ ከተቀመጡ ሚኒስቴሮች የመካተታቸው አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ የተነሳባቸው ሲኖሩ መካተት ይገባቸዋል የተባሉ አሉ፡፡ በፕሮግራሙ አጠቃላይ ተጠቃሚ ይሆናሉ ከተባሉ 972 ከተሞች በሙከራው ወይም በመጀመሪያው ዙር የሚገቡት አሥራ አንድ ብቻ መሆናቸውን፣ ቁጥሩን ትንሽ ሊያስብለው እንደሚችልም ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡
የከተሞች የምግብ ዋስትናና ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲና ምክር ቤቱ በቅርቡ ይቋቋማል ያሉት አቶ አብርሃም፣ የምክር ቤቱ መቋቋም የመንግሥትን ውሳኔ እየጠበቀ ነው ብለው፣ የኤጀንሲው አደረጃጀትን የሚመለከት ሰነድ ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ለፕሮግራሙ የሙከራ ትግበራ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ መገኘቱንና 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በመንግሥት መመደቡን የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ ከበጀቱ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚውል ነው ብለዋል፡፡ ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚሆነው ለምርታማ ሥራዎች፣ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያና ለሰው ኃይል አጠቃላይ አደረጃጀት እንደሚውልም አስረድተዋል፡፡