Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀዳሚ ሳይንቲስት ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ዕረፍት (1923 - 2008)

የቀዳሚ ሳይንቲስት ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ዕረፍት (1923 – 2008)

ቀን:

የጤና ዘርፍ በተለይ በክትባትና እንስሳት ሕክምና በእብድ ውሻ በሽታ ሥርጭትና የመተላለፊያ መንገዶች ላይ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በመሥራት ታዋቂ የነበሩት ቀዳሚ (ሲኒየር) ሳይንቲስት ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ባይሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በደቡብና ምሥራቅ አፍሪካ የባለሙያዎች ኔትወርክ ከመሠረቱት ሳይንቲስቶች አንዱ የነበሩት ዶ/ር መኰንን የኢትዮጵያ የእንስሳት ሐኪሞች ማኅበርም መሥራች አባል ነበሩ፡፡

ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በአገር ውስጥና በባሕር ማዶ ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡት በአሜሪካ ሲዲሲ (የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል) አትላንታ በቀዳሚ (ሲኒየር) ሳይንቲስትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር መኰንን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) አዲስ በተቋቋመው የሕክምና ፋኩሊቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ በንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ የዋናው ላቦራቶሪና የጥናት ድርጅት (ቀድሞ ፓስተር ኢኒስቲትዩት ይባል በነበረው) ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ በክትባትና እንስሳት ክፍል ኃላፊነት እስከ ኅዳር 1966 ዓ.ም. ካገለገሉ በኋላ ከሁለት ዓመት በላይ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሆነው ማገልገላቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ዶ/ር መኰንን፣  ከ1957 ዓ.ም እስከ 1968 ዓ.ም በቀድሞው የዋናው ላቦራቶሪና የጥናት ድርጅት በቆዩባቸው ዘመናት በተለይም በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርመራና ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ እንዲዋቀር በማድረግ ከአዲስ አበባና ከየክልሉ ለሚቀርቡ የእብድ ውሻ በሽታ የሕክምና አገልግሎት ጥያቄዎች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ከዓለም የጤና ድርጅት የእንስሳት ህክምና ኤክስፐርት ባለሙያዎች ጋርም በቅርብ በመሥራት በአገራችን በወቅቱ የሚመረተው ለሰውና ለእንስሳት የሚውለው ክትባት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡

ከዚያም በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ወደ ውጪ አገር ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በመሄድ አሜሪካ በሚገኘው ሲዲሲ አትላንታ በሙያቸው ተቀጥረው በቀዳሚ ሳይንቲስትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ በሲዲሲ አትላንታና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በጤናው ዘርፍ ልማት ለተጀመረው ሁሉ አቀፍ ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ከሲዲሲ አትላንታ በትውስት ወደ ኢትዮጵያ የጤናና ሥነ- ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ተዛውረው ቀደም ሲል ያካበቱትን እውቀትና ልምድ ለኢንስቲትዩቱ ባለሙዎች ከማካፈላቸውም በላይ በተለይ በኢንስቲትዩታችንና በሲዲሲ አትላንታ መካከል የሁለትዮሽ የምርምርና የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ተግባራት በጥልቀትና በስፋት እንዲከናወኑ በማቀራረብና በማስተባበር እጅግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ዶ/ር መኰንን ከኢንስቲትዩቱና የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በእብድ ውሻ በሽታ ስርጭትና የመተላለፊያ መንገዶች ላይ የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን መሥራታቸውን እነርሱም፡- ውሾች ቫይረሱን ለብዙ ጊዜያት ሳያማቸው ከቫይረሱ ጋር ተሸክመው በመኖር ወደ ሌላ ጤናማ እንስሳ ወይም ሰው ማስተላለፍና በውሾች መካከል ሊኖር ስለሚችለው የበሽታው ስርጭትና ዝውውር አጥንተው በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ የእብድ ውሻ በሽታ አምጪ ቫይረስ በውሾች የምራቅ እጢ ውስጥ ስለመኖሩና በሽታው በአበደ እንስሳ ምራቅ መተላለፍ ስለመቻሉ ባደረጉት ሙከራ በበሽታው ከሞቱት 17 ውሾች በዘጠኙ የምራቅ እጢ ውስጥ ቫይረሱ መገኘቱን በጥናት አረጋግጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ እ.አ.አ. በ1990ዎቹ ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ባደረጉት ጥናት አንድ በዚህ በሽታ የታመሙ እናት ለሕክምና አገልግሎት ወደ ኢንስቲትዩቱ በመጡ ጊዜ ዶ/ር መኰንን ባደረጉት የሕክምና ክትትል ጥናት መሰረት የእናቷን ጡት ስትጠባ የነበረች ታማሚ ሕፃን የእናቷን ጡት በመንከስ በሽታውን ማስተላለፍ እንደቻለች የሚገልጽ ጥናታዊ ሪፖርት ከኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ያበረከቱ ሳይንቲስት እንደነበሩ ተቋሙ ገልጿል፡፡

ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ ገብረማሪያም እና ከአባታቸው ከአቶ ፈቃዱ ባይሩ ሰኔ 23 ቀን 1923 ዓ.ም. በቀድሞው ትግራይ ጠቅላይ ግዛት መቀለ ከተማ የተወለዱት ዶ/ር መኰንን መቐለ ከተማ በሚገኘው አፄ ዮሐንስ 4ኛ ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ መምህራን ትምህርት ቤት ገብተው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

ከ1942 ዓ.ም መስከረም 1 ቀን ጀምሮ ለአራት አመታት በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ አገር ሄደዋል፡፡ ከዚያም ከ1946 እስከ 1956 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ኮፐንሀገን ከሚገኘው ሮያል ቬተሪነሪና እርሻ ዩኒቨርስቲ ቢ.ኤስ.ሲ፣ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ዲ.ቪ.ኤም (D.V.M)፣ እንዲሁም በቬተረነሪና እርሻ ዩኒቨርስቲና ስታትራንስ ሴሩም ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ዲግሬአቸውን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛውን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከስዊድን በቫዮሮሎጂ (Virology) እና ዙኖሲስ (Zoonosis) አግኝተዋል፡፡

ታኅሣሥ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በአሜሪካ ያረፉት ዶ/ር መኰንን ሥርዓተ ቀብራቸው ጥር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡  

ዶ/ር መኰንን ፈቃዱ ባለትዳር፣ የሦስት ልጆች አባትና የሁለት ልጆች አያት ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...