Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጥረት አንድ ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ለማቅረብ ተስማማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢንዶውመንት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ጥረት ኩባንያ፣ ከኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ጋር አንድ ሺሕ ቶን የሚደርስ የተዳመጠ ጥጥ ለማቅረብ የግዥ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ዓርብ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀድሞው የጅንአድ (ጅምላ ንግድ አስመጪ ድርጅት) በተካው የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ቢሮ ተፈራርመዋል፡፡ የግዥ ስምምነቱ በቅርብ ጊዜ በሚኒስሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም ለተወሰነው የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ተጨማሪ ውጤታማ ሥራ መሆኑን፣ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አስፋወሰን አለነ ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱ በአገር ውስጥ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የጥሬ ዕቃና የሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተመሠረተ መሆኑን ከጥረት ድርጅት ጋር ያደረገው ስምምነትም ለዚህ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ባለፉት ዓመታት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ንዑስ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተስተዋለውን የጥጥ አቅርቦት እጥረት ለማገዝ፣ እስከ ዓመቱ  መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 15 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ለመግዛት መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡

ለሚገዛው አጠቃላይ የጥጥ ምርት በመሀል አገር ካለው በተጨማሪ፣ በኮምቦልቻና በአዋሽ ተጨማሪ መጋዘኖች መዘጋጀታቸውን ኃላፊው አክለዋል፡፡

የጥረት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ከበደ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን ከመፍታት ባሻገር ጥሬ ዕቃዎችን የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የሚደርስባቸውን የገበያ ችግርና የምርት ብክነት ለማስቀረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

ከግብዓት አቅራቢው ድርጅት ጋር የተደረገውን የግዥ ስምምነት በተመለከተ፣ ድርጅቱ ከጥረት በዓለም አቀፍ የገበያ ሥርዓት መሠረት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ስፌት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሚተምነው ዋጋ መሠረት ግዥ እንደሚፈጽም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከጥጥ አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ በዘርፉ ተዋናዮች መካከል እንደ ትልቅ ችግር ሲጠቀስ የቆየው የዋጋ ጉዳይ ነው፡፡

የጥጥ አቅራቢዎች ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች በሚቀርብላቸው ዋጋ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ በሚገባቸው የመሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ሲጎተጉቱም ነበር፡፡ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በበኩላቸው የዓለም ገበያ ከሚጠይቀው በላይ ተጠይቀናል በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡

ጥረትም እንዲሁ በዋጋ አተማመን ላይ ቅሬታ እንዳለው በስምምነቱ ወቅት የጥረት ጥጥ ልማት እርሻና የመዳመጫ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ መንግሥቴ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በዋጋ አተማመን ላይ ችግሩ አሁንም አለ፡፡ ዛሬ ከመንግሥት ጋር ይህንን ዓይነት ስምምነት ያደረግነው የዋጋ ተመኑ ጉዳይ ስለተወሰነ ሳይሆን በሒደት ይሻሻላል የሚል ዕምነት ስላለን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ከአገር ውስጥ አልፎ ከውጭ ጥጥ ግዥ መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ጥጥ አምራቾች በጥራትም በብዛትም አምርተው ግዥ በማጣታቸው ምርቱ እየተበላሸባቸው መቸገራቸውን ሲገልጹም ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች