Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዩክሬን መኪኖች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ላይ የተካሄደው የማፍረስ ተግባር ታገደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዩክሬን ሠራሽ አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የተቋቋመው ኒማ ሞተርስ የመኪና መገጣጠምና መለዋወጫ ኩባንያ፣ ላይ ሲደረግ የነበረው የማፍረስ ዕርምጃ እንዲቆም ፍርድ ቤት አገደ፡፡

ኩባንያው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይዞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ውስጥ አወልያ ትምህርት አካባቢ የግል ይዞታው በነበረው በ7,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ ሲያካሂድ መቆየቱን ይገልጻል፡፡ ሆኖም የክፍለ ከተማው አስተዳደርም ሆነ ወረዳው ሕገወጥ ግንባታ በማለት እየተገነባ የነበረውን ፋብሪካ በግሬደር ያፈረሱት ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ኩባንያው በፍርድ ቤት ሲካሄድበት የነበረውን የማፍረስ ተግባር ለተወሰኑ ቀናት እንዲገታለት አድርጓል፡፡

የልደታ ምድብ 14ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ጥር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ተካሳሽ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ጽሕፈት ቤት ምላሹን ለጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ይዞ እስኪቀርብ አዟል፡፡ ‹‹ከኢንቨስትመንት ፈቃድ ቁጥር EIA-IP022260/05 የተመዘገበው የመኪና መገጣጠሚያና ማምረቻ ድርጅት በዚህ ችሎት ክስ እስከሚሰማበት ወቅት ድረስ እንዳይፈርስ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር ቁጥር 154 መሠረት ታግደዋል፡፡ ታዟል፤›› በማለት ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

ኒማ ሞተርስ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ሲገነባበት የነበረው ቦታ ከዚህ ቀደም ለሸክላና ለሲሚንቶ ውጤቶች ማምረቻ በነበረው ቦታ ግማሹን ለመጠቀም ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ የኒማ ሞተርስ መሥራችና ከዩክሬኑ ዛዝ ኩባንያ ጋር በእሽሙር ወይም በጆይንት ቬንቸር የ50 ከመቶ ባለድርሻ በሆኑት በዶ/ር ብርሃኑ ዘውዴ ስም የተመዘገበውን 7,000 ካሬ ሜትር ቦታ ግማሹን ለመኪና መገጣጠሚያነት እንዲውልና ግንባታ እንዲፈቀድላቸው፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ግንባታ ፈቃድ ክትትልና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ያቀረቡት ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር የሰነድ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኩባንያው የይዞታ ማረጋገጫና ካርታ እስኪያገኝ ድረስ ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚያስችለውን ግንባታና የሥራ ፈቃድ የትብብር ደብዳቤ ከክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤትም ደብዳቤ ተጽፎለት ነበር፡፡ ይህንንም በማስመልከት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሒደቱን ጠቅሶ ጽፏል፡፡

ኮሚሽኑ ኅዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ለዚሁ ጽሕፈት ቤት በጻፈው የድጋፍ ደብዳቤ ኩባንያው የፋብሪካ ግንባታ አጠናቆ ለሥራ አስፈላጊ መሣሪያዎችንና ዕቃዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ እንዳስገባና የሚፈለግበትን ካፒታልም በገንዘብና በዓይነት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳስተላለፈ ጠቅሷል፡፡ ከዚህም ባሻገር መኪና ለመገጣጠም የሚያስችል የንግድ ፈቃድ ተሰጥቶት ወደ ምርት ከገባ በኋላ ግን በድጋሚ ሕጋዊ ፈቃድ የለውም የሚለው ችግር መፈጠሩን የገለጸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከዚህ ቀደም ኩባንያው ላይ የተጻፈው ማስጠንቀቂያ ተስነቶ ሥራውን መቀጠል እንዲችል ይደረግ ሲል፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት፣ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት፣ ለወረዳ 10 አስተዳደር እንዲሁም ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር በግልባጭ አስታውቆ ነበር፡፡  

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ይህንን ደብዳቤ ቢጽፍም የመሬት ልማትና ማኔጅመንትም ሆነ ክፍለ ከተማው፣ እንዲሁም ወረዳው የኩባንያውን ፋብሪካ ከማፍረስ አልተቆጠቡም፡፡ የኩባንያው የገበያና የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ታምራት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በግምት የፋብሪካው 40 በመቶ የሚሆነው ክፍል ፈርሷል፡፡ በአንድ መኪናና በማሽነሪዎች ላይም ጉዳት ደርሷል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ የደረሰው የጉዳት መጠን ገና እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተርን ጨምሮ የሌሎች መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ይካሄድ የነበረውን የማፍረስ ተግባር በቦታው በመገኘት ለመዘገብ ያደረጉት ጥረትና ጥያቄ፣ የማፍረስ ሒደቱን እንዲቆጣጠር በኮማንደር ወጋየሁ ሶርሳ በተመደበው የፀጥታ ኃይል ክልከላ ተደርጎበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 ከአዲስ አበባ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በተገኘው መረጃ፣ ኩባንያው በሕገወጥ መንገድ ከሌሎች ጋር ተጠግቶ ሲሠራ ነበር ማለቱም ተዘግቧል፡፡ ኩባንያው በበኩሉ ሕጋዊ ጥያቄዎችን ያቀረበበትና ስምምነት የፈጸመባቸውን፣ ፈቃድ ያገኘባቸውንና ሌሎች ሰነዶችን በማቅረብ በነባር ይዞታው ላይ ያካሄደውን ግንባታ ቢከላከልም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን ግንባታውም ፈቃድ የሌለው በመሆኑ ሊፈርስ መቻሉን ገልጿል፡፡

ባለፈው ዓመት ሥራ ሲጀምር 35 መኪኖችን ገጣጥሞ እንደነበር አስታውቆ የነበረው ኒማ ሞተርስ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ፋብሪካው ገብተው ሊገጣጠሙ የነበሩ 20 የመኪና አካላት በጂቡቲ ወደብ እንደሚገኙ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ሊገጣጠሙ የነበሩትን ጨምሮ ሌሎች አሥር መኪኖችንም በማስመጣት ለመገጣጠም ከዩክሬን ተጭነው በመጓጓዝ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

‹‹ዛፖሪዚያ አውቶሞቢል ቢዩልዲንግ ፕላንት›› ወይም በአጭር አጠራሩ ‹‹ዛዝ›› በሚል ስያሜው የሚታወቀው የዩክሬኑ መኪና አምራች፣ ከኒማ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጋር በጋራ በመሆንና የሃምሳ ከመቶ እኩል ድርሻ በመያዝ፣ በኢትዮጵያ የገጣጠማቸውን መኪኖች ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

የኒማ ሞተርስ ባለቤቶች የ57 ሚሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት ጀምረው፣ በአሁኑ ወቅት እያካሄዱዋቸው ባሉት ማስፋፊያዎች ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ከፍ እንደሚያደርጉት ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች