Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በፔትሮትራንስ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ለሌሎች ኩባንያዎች ትምህርት እንደሚሆን ተጠቆመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦጋዴን የሚገኙ የጋዝ ክምችቶችን ለማልማትና የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለማከናወን ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሞ በውሉ መሠረት ወደ ሥራ ባለመግባቱ ፈቃዱ የተሰረዘበት ፔትሮትራንስ በተሰኘው ኩባንያ ላይ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ፣ ለሌሎች ኩባንያዎች ትልቅ ትምህርት ሊሆን እንደሚችል የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ፔትሮትራንስ በሚኒስቴሩ የተወሰደውን ዕርምጃ በመቃወም በፈረንሣይ ፓሪስ በሚገኘው የዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የመሠረተው የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ክስ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን አስመልክቶ፣ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ዓርብ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ በፔትሮትራንስ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የማዕድን ፍለጋና ልማት ቦታ ወስደው በአግባቡ ለማይሠሩ ኩባንያዎች ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

‹‹አፍሪካዊያን ስለዓለም አቀፍ ሕግ አያውቁም ብለው ለማጭበርበር ለሚሞክሩ ኩባንያዎች ትምህርት እንደሚሰጥ አንጠራጠርም፡፡ በአግባቡ ለሚሠሩ ልማታዊ ኩባንያዎች ደግሞ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃና የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕጋዊ አሠራር የሚከተል መሆኑን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡

ፔትሮትራንስ ከሚኒስቴሩ ጋር እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2011 በተፈራረማቸው አምስት ስምምነቶች መሠረት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በሚገኙ የነዳጅና የጋዝ ብሎኮች ላይ የፍለጋና የማልማት ሥራዎችን ለማከናወን፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት ለልማት የሚውል ብድር ለማቅረብና ከጋዝ ልማቱ ከሚገኝ ገቢ ብድሩ እየተቀናነሰ እንዲከፈል ተስማምቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኩባንያው እንኳንስ ቃል የገባውን ብድር ለማቅረብ ቀርቶ፣ በስምምነቶቹ መሠረት ብሎኮቹን የማልማት ተግባሩን ሊወጣ ባለመቻሉ በውሉ የተመለከቱት የተለያዩ ግዴታዎች የሚፈጸምባቸው የጊዜ ገደቦችም በማለፋቸው፣ የውል ስምምነቶቹ እንዲሻሻሉ ተጨማሪ የማሻሻያ ስምምነትን ተፈራርሞ እንደነበር የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ በተሻሻለው ስምምነት መሠረትም ኩባንያው የውል ግዴታውን ሊወጣ ባለመቻሉ መንግሥት አምስቱንም የውል ስምምነቶች መሰረዙን አስረድተዋል፡፡

የውሎቹን መሰረዝ በመቃወም ኩባንያው የኢትዮጵያን መንግሥት በውሎቹ መሠረት ፓሪስ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ፍርድ ቤት ከሶ፣ ክርክሩ የፍርድ ቤቱ መቀመጫ እንዲሆን ተከራካሪ ወገኖች በተስማሙበት በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሒደት ዓለም አቀፍ የንግድ ፍርድ ቤቱ በተከራካሪ ወገኖች የቀረቡለትን በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰነዶችን መመርመሩንና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሙያና የፍሬ ነገር ምስክሮችን ማዳመጡን አቶ ቶሎሳ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 31 ቀን 2015 ያሳለፈ ሲሆን፣ ይህንኑ ለተከራካሪ ወገኖች ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ፔትሮትራንስ ያቀረበውን የካሳ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለክርክሩ ያወጣውን ወጪ በከፊል እንዲመልስ ወስኗል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ የፍትሕ መድረክ ኢትዮጵያ ያገኘችው ይህ ድል ለአፍሪካና ለሌሎችም ታዳጊ አገሮች የድል ብሥራት ሆኖ የሚያገለግል ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ውስብስብና ግዙፍ ዓለም አቀፍ የፍርድ ቤት ክርክር መንግሥትና ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያገኙበት፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖች የተለዩበት፣ መንግሥት ለተያያዘው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተሻለ መንገድ እንዲከናወን የሚያስችሉ በርካታ ልምዶች የተገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል የተከራከረውን በአሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ቀድሞ አዲስ ኢንተርናሽናል አርቢትሬሽን ግሩፕ ኤልኤልፒ በመባል ይጠራ የነበረውንና አሁን ደግሞ አዲስ ሎው ግሩፕ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮና በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ተባባሪውን ግሪንበርግ ትራውሪግን አመስግነዋል፡፡

መንግሥት ለፍርድ ቤቱ ክርክር ያወጣው ወጪ ድምር በእጃቸው እንደሌለ የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ ወጪው በወጣበት ወቅት ሕመም ማስከተሉን ጠቅሰው መንግሥት ያወጣውን ወጪ በከፊል ፔትሮትራንስ እንዲከፍል መወሰኑን ጠቁመዋል፡፡

ውሳኔውን አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡ የፔትሮትራንስ ኃላፊዎችን ሪፖርተር የጠየቀ ቢሆንም ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ወቅት የምንሰጠው አስተያየት የለም፤›› ብለዋል፡፡

የነዳጅ ልማት ስምምነቱ በተሰረዘበት ወቅት የፔትሮትራንስ ኃላፊዎች ስምምነቱ የተሰረዘው ሥራ ባለመሥራታቸው ሳይሆን፣ ለመንግሥት ለማምጣት ቃል የገቡትን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ባለመቻላቸው እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

ስምምነቱ የተሰረዘው ኩባንያው ብድሩን ባለማግኘቱ እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ቶሎሳ ሲመልሱ፣ ብድሩ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋናው ግን ሁኔታዎች ተመቻችተውለት ሳለ በገባው ውል መሠረት ወደ ሥራ ባለመግባቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፔትሮትራንስ የቀማቸውን የካሉብና የሂላላ የጋዘ ክምችቶችንና የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች እ.ኤ.አ. ኅዳር 2013 ፖሊ ጂሲኤል ለተሰኘ የቻይና ኩባንያ ሰጥቷል፡፡ ፖሊ ጂሲኤል በአሁኑ ወቅት በጋዝ ልማትና የነዳጅ ፍለጋ ፕሮጀክቱ ላይ ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች