Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕክምና መሣሪያ ግዢ ውድቅ...

ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕክምና መሣሪያ ግዢ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ውሳኔ መሠረት ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሊገዛ የነበረው ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ (5,139,742.50 ዶላር) የሚያወጣ የኤችአይቪ የመመርመሪያ መሣሪያ፣ በመንግሥት የግዢ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ ውድቅ ተደረገ፡፡

የመንግሥት ግዢ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ላይ በጻፈው የዕግድ ደብዳቤ፤ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የኤችአይቪ ፈጣን የቅድመ ምርመራ ኪት ለመግዛት ባወጣው ጨረታ፣ አሸናፊ የተባለው ድርጅት ያላግባብ መሆኑን ማረጋገጡን በመግለጽ፣ የውጤት ውሳኔው ውድቅ አድርጎ ከተቀሩት ተጫራቾች መካከል አወዳድሮ እንደ አዲስ ግዢ በአግባቡ እንዲያከናውን አሳስቧል፡፡

አሸናፊ ተብሎ በኤጀንሲው ውሳኔ ላይ የተደረሰበት “First Response HIV ½ – card Test” በሚል የምርመራ ኪት ያቀረበው ባዮቴክ ፒኤልሲ ነው፡፡ ሌላው ተጫራች ሜዲካ ፋርማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አሸናፊው የተባለው ድርጅት፣ ‹‹ኤጀንሲው ያወጣቸውን አነስተኛ መሠረታዊ የጨረታ መገምገሚያ መሥፈርቶችን የማያሟላና የብቃት ደረጃው ዝቅተኛ መሆኑ በጥናት ተረጋግጦ ውድቅ የተደረገው ኪት (የምርመራ መሣሪያ) ያቀረበ ነው፤›› በማለት ለኤጀንሲውና ለመንግሥት የግዢ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ለቀረበው አቤቱታ ምላሽ የሰጠው የመንግሥት የግዢ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ ቦርድ፣ ኤጀንሲው ካቀረባቸው መግለጫዎችና የሰነድ ማስረጃዎች፣ ከፌዴራል መንግሥት የግዢና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 እና ሰኔ 2002 ዓ.ም. ከወጣው የአፈጻጸም መመርያ አኳያ መመርመሩን ገልጿል፡፡ ኤጀንሲው ለቀረበለት አቤቱታ በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሽ አለመስጠቱ የግዥ ሕጉን የጣሰ አሠራር መሆኑ፣ እንዲሁም ለአሸናፊና ለተሸናፊዎች ለምን እንዳሸነፉና እንደተሸነፉ በቂ የሆነ ምክንያት አለመግለጹን በመጠቆም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ግዢውን ውድቅ ያደረገባቸውን መሠረታዊ ምክንያቶችም ዘርዝሯል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ቅድመ ምርመራ (WHO Prequalified Diagnostics) የአቅራቢዎች ዝርዝር ላይ የጨረታው አሸናፊ የተባለው ድርጅት ስምና ኪት በወባ መድኃኒት ምርት ላይ ብቻ እንጂ፣ የኤችአይቪ ፈጣን ምርመራ ኪት ላይ ያልተመዘገበ መሆኑ፣ በኤጀንሲው በተዘጋጀውና በተሸጠው የጨረታ ሰነድ እንደ መሥፈርት የተቀመጠውን ነጥብ በመተው በምትኩ ሌላ መሥፈርት በማስቀመጥ በግምገማው ላይ መጠቀሙ፣ አሸናፊ የተደረገው ተጫራች በዓለም ጤና ድርጅት ቅድመ ምርመራ ዝርዝር ላይ ለመመዝገብ በሒደት ላይ መሆኑን በመጠቆም፣ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን መሥፈርት አሟልቶ ያልተመዘገበ መሆኑን በዚህም በጨረታ ሰነዱ የተጠየቀውን የማያሟላ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም በጨረታ ሰነዱ ላይ ያልተቀመጠን መሥፈርት ለግምገማ መጠቀሙ በፌዴራል መንግሥት የግዢና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 6 በግዥ አፈጻጸም መመርያው፣ ‹‹በጨረታ ሰነዱ ውስጥ ከተቀመጠው መሥፈርት ውጪ ግምገማ ማድረግ አይፈቀድም፤›› በማለት የተደነገገውን የሚጥስ መሆኑንም የቦርዱ ውሳኔው ያስረዳል፡፡

ተጫራቾች የግድ ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርት አሸናፊ የተባለው ድርጅት ባለማሟላቱ ከጨረታ ውጪ ሊያደርገው ሲገባ፣ ኤጀንሲው በአሸናፊነት መምረጡ አግባብ አለመሆኑን ቦርዱ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ መወሰኑን ገልጿል፡፡

በውሳኔው መሠረት አሸናፊ የተባለውን ድርጅት ከጨረታው ውጪ በማድረግ አቤቱታ አቅራቢውን (ሜዲካ ፊርማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) ጨምሮ በተቀሩት ተጫራቾች መካከል የጨረታ ሰነዱንና የግዢ ሕጉን ብቻ ተከትሎ ግምገማውን እንደገና እንዲያከናውን ቦርዱ አዟል፡፡ እንዲሁም ኤጀንሲው የተጠቀሰው ግዢ በቦርዱ ውሳኔ መሠረት ስለመፈጸሙ ደብዳቤው በደረሰው በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ለቦርዱ ጽሕፈት ቤት እንዲያሳውቅ አሳስቧል፡፡

የጨረታ ሒደቱን የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲከታተለው መቆየቱን ጥቅምት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በሥሩ ላሉት ለመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ ከአልጎሪዝም ክለሳና ይህንንም መሠረት አድርጎ በሚከናወነው የኤችአይቪ መመርመርያ መሣሪያዎች ግዢ ዙሪያ የተፈጠረ የግልጽነት ችግር እንዲቀረፍ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ጥረት ሲደረግ የቆየ መሆኑን ገልጿል፡፡

እንዲሁም ተወዳዳሪ ተቋማት የሚመዘኑበት ሥርዓት ምዘናው ከመከናወኑ በፊት በግልጽ ተመላክቶ እያለ፣ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ውጤት ሊያዛባ በሚችል ሁኔታ የተቀመጠውን መሥፈርት ያልተከተለ አሠራር ተፈጻሚ ሲደረግ ቢስተዋልም፣ ኤጀንሲው ችግሩን ለማረም ፈቃደኛ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡ በወቅቱ ማለትም በ2005 ዓ.ም. የአልጎሪዝምን ክለሳ በተመለከተ የታዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ በኮሚሽኑ በኩል ጥያቄዎች ሲቀርቡ አጣዳፊነቱ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሲቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ግን ግዢው እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ አለመከናወኑ የችግሩን አመጣጥ ይበልጥ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው ሲል ኮሚሽኑ በደብዳቤው አስፍሯል፡፡

ከሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ ግልጽ የሆነ የግዢ ሥርዓት እንዲዘረጋ ተደጋጋሚ ጥረቶች ማድረጉን በመግለጽ፣ ‹‹እስካሁን ድረስ ይህ ነው የተባለ ተግባራዊ ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም፡፡ ይልቁንም ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የተበጣጠሱ ግዢዎችና ውሎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፤›› ብሏል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ የመንግሥትና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሲል፣ ጉዳዩን ከሙስና መከላከል ባለፈ ወደ ሕግ ማስከበር ዘርፍ ተሸጋግሮ በዚሁ አግባብ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚገደድ መሆኑን በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት ጥር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኤችአይቪ መመርመሪያ ኪት የግምገማ ውጤትን ባሳወቀበት ደብዳቤ፣  ለሁለቱም ድርጅቶች ማለትም ባዮቴክ ፒኤልሲ (አሸናፊነቱ ውድቅ የተደረገበት) እና አሁን በመወዳደር ላይ ላለው ሜዲካ ኢትዮጵያ ፒኤልሲ የዓለም የጤና ድርጅት ያሰፈራቸውን መሥፈርቶች የማያሟሉ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...