Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አንዱ የሌላውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ እየተወዛገቡ ነው

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አንዱ የሌላውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ እየተወዛገቡ ነው

ቀን:

‹‹ሥራ አስፈጻሚው በሌለው ሥልጣንና ኃላፊነት እየተንቀሳቀሰ ነው›› የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ

‹‹ብስለት የጐደለውና ማስተዋል የራቀው አሠራር ነው›› የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት

የሰማያዊ ፓርቲን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ ጥሰዋል ተብለው ከፓርቲው አባልነታቸው ተሰናብተዋል በተባሉት አራት አባላት ላይ በተላለፈው ውሳኔ ላይ፣ አመራሮቹ አንዱ የሌላኛውን ውድቅ በማድረግ እየተወዛገቡ ነው፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ አቶ ዮናስ ከድር፣ አቶ እያስጴድ ተስፋዬና አቶ ጋሻየነህ ላቀን፣ የፓርቲው ብሔራዊ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ከጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከአባልነት እንዲሰናበቱ የወሰነ ቢሆንም፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‹‹የተወሰደው ዕርምጃ ምልዓተ ጉባዔው ባልተሟላበት ነው፡፡ በመሆኑም ውሳኔው ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቆ ነበር፡፡

የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴውን ውሳኔ ውድቅ ያደረገውን የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውሳኔ ደግሞ፣ ‹‹ያለ ሥልጣኑና ኃላፊነቱ የሰጠው ውሳኔ ነው፤›› በማለት የፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን የአራት ቀናት ዕድሜ ያለውን ውሳኔ ውድቅ ከማድረጉም በላይ፣ ‹‹ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከሕገወጥ ተግባሩ ይታቀብ፤›› ሲልም አስጠንቅቋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ብሔራዊ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው በአራቱም አባላት ላይ ውሳኔ ቢያስተላልፍም ኮሚሽኑ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ራሳቸውን መከላከልም ሆነ ይግባኝ ማለት ስለማይችሉ የተላለፈባቸውን ውሳኔ እየመረመረው ነው፡፡

ኮሚሽኑ ይኼንን እየሠራ ባለበት ወቅት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያስተላለፈው ውሳኔና የሰጠው መግለጫ የፓርቲውን ደንብ የሚጣረስ መሆኑን በደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ ብሔራዊ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው በፓርቲው ደንብ አንቀጽ 44/1 መሠረት የተቋቋመና የሥነ ሥርዓተ ክሶችን የሚያይ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በፓርቲው ደንብ አንቀጽ 10 መሠረት ከጠቅላላ ጉባዔው ቀጥሎ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ክስ የተመሠረተባቸው አባላት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ተገቢ ካልሆነ፣ ለኮሚሽኑ ይግባኝ ማለት ያለባቸው ራሳቸው ተሰናባች አባላቱ መሆናቸውን ደብዳቤው ያብራራል፡፡ ነገር ግን ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከተሰጠው ኃላፊነት በላይ ሄዶ ውሳኔውን ውድቅ ማድረግና መግለጫ መስጠት እንደማይችልም አብራርቷል፡፡

የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሰብሳቢና የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር አነጋግሯቸው እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የጻፈውን ደብዳቤ አይተውታል፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሶታል የተባለው የትኛውን ሕግና አንቀጽ እንደሆነም የሚለው ነገር የለም፡፡ ውሳኔ ባረፈበት ጉዳይ ላይ ሕዝብም ሆነ ኮሚቴው አስተያየት የመስጠት መብት አለው፡፡ ቀደም ብለው እንደገለጹት፣ እንደ ፓርቲ ሊቀመንበርነታቸውና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ሕግን የማስከበርና የማክበር ግዴታቸውን መወጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ሊቀመንበሩ በሰማያዊ ፓርቲ ደንብና መመርያ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት እንዳለባቸውና መብታቸውም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሌላውን ኮሚቴ ውሳኔ የመሻር ወይም ያለመቀበል ሥራ እንዳልሠራ የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ ብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ምልዓተ ጉባዔው ሳይሟላ ያስተላለፈው ውሳኔ በፓርቲው ደንብ መሠረት ሕገወጥ በመሆኑ ሕግ እንዲከበር ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ዕርምጃ ለመውሰድ የተቻለው፣ ብሔራዊ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው አራት አባላት ተስማምተውና ቃለ ጉባዔ ፈርመው አባላቱን እንዳሰናበተ ከገለጸ በኋላ ከአራቱ አንዱ ናቸው የተባሉት አቶ ሲሳይ ካሴ፣ በኮሚቴው ውይይት እንዳልተስማሙና በቃለ ጉባዔው ላይም እንዳልፈረሙ፣ ለፓርቲው ልሳን ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ›› በመግለጻቸው (በድምፅ ተቀርፀው) መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ባልተሟላ ምልአተ ጉባዔ የተወሰነን ውሳኔ ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ዝም ብሎ ማለፍ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ብስለት የጐደለውና ማስተዋል የራቀው አሠራር ተከትሎ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጐደለው ከመሆኑም በላይ፣ መግለጫ የማውጣት ሥልጣን እንደሌለው ኢንጂነር ይልቃል አስረድተዋል፡፡

የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የወሰደውን ሕግን የማስከበር ዕርምጃ በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ከሪፖርተር ተጠይቀው እንደተናገሩት፣ ምልዓተ ጉባዔ እንዳልሞላ በመግለጽ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ያስተላለፈውን ውሳኔ፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ባልሆነበት ሁኔታ ጉዳዩን ማገድ ሳይሆን የመመልከትም ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡

‹‹ባለኝ መረጃ መሠረት በቃለ ጉባዔው ላይ አልፈረመም የተባለው ግለሰብ በስብሰባው ላይ ነበር፡፡ ወጥቶ መግለጫ ከመስጠት እዚያው በውስጥ መነጋገርና መጨረስ ይችሉ ነበር፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ ግለሰቡ ስለመፈረማቸው እርግጠኛ ሆነው መናገር አልቻሉም፡፡

የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው አባል እንዳልፈረሙ እየተናገሩና እሳቸው መፈረማቸውን ሳያረጋግጡ ኮሚቴው የወሰደውን ዕርምጃ እንዴት ሊደግፉ እንደቻሉ ተጠይቀው፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መጀመሪያ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴውን፣ በመቀጠል ኮሚሽኑን መጠየቅ እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ የአካሄድ ስህተት እንደተፈጸመ ጠቁመው፣ የተሰናበቱት አባላት ለኮሚሽኑ ይግባኝ ሳይጠይቁና የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ውሳኔ ተቃውሞ ሳይነሳበት፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የአሠራር ሥነ ሥርዓት ጥሶ የወሰደው ዕርምጃ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው የወሰደውን የማሰናበት ውሳኔም አለማየታቸውንም አክለዋል፡፡

በብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል መጀመሪያ መሄድ ያለበት ወደ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ መሆን እንደነበረበትም አቶ አበራ ጠቁመዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...