Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በመልካም አስተዳደር ላይ የሚደረጉ ግምገማዎችም ሆኑ ዕርምጃዎች ግልጽነት ይኑራቸው!

ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ከመልካም አስተዳደር ዕጦት ጋር በተገናኘ ግምገማዎችና ከኃላፊነት የማንሳት ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ እነዚህ ግምገማዎችና ዕርምጃዎች እየተካሄዱ ያሉት በቀጥታ ከሕዝብ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች በሚገኙ የተጣሩ መረጃዎች ላይ ተመሥርተው ካልሆነ፣ ውጤቱ የሚሆነው ስህተትን በስህተት ማረም ነው፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ የሚገኙ ግብዓቶች ላይ በመመሥረት፣ ችግር አለባቸው በሚባሉ በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች ላይ ሕጋዊና ተገቢ ዕርምጃ መውስድ አስፈላጊ ነው፡፡ የሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲኖር ግልጽነት ይሰፍናል፡፡ የተጠያቂነት መጠኑም ይጨምራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብን በከፍተኛ ደረጃ የሚያስመርሩ ተሿሚዎች በሕዝቡ ዘንድ በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ ግምገማዎቹና ዕርምጃዎቹ ግልጽነት የሚጎድላቸው ከሆነ ሕዝቡ አይቀበላቸውም፡፡ በኔትወርክ የተሳሰሩ ኃይሎች መድረኮቹን ተቆጣጥረው የይስሙላ ግምገማ በማካሄድ ዕርምጃ የሚወስዱ ከሆነ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መጓደልና በሙስና ላይ የሚደረገው ዘመቻ መሳቂያ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጉልህ የሚታዩ ችግሮችን የሚፈጥሩና በሕዝብ ላይ የሚያላግጡ ሹማምንት በግልጽ ድርጊቶቻቸው ተወግዘው ዕርምጃ ሲወሰድባቸው፣ ሕዝቡ የዘመቻው አጋር ብቻ ሳይሆን ባለቤት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ግልጽነት ሊኖር ይገባል፡፡

የአገልጋይነት መንፈስ ርቆአቸው በሕዝብ ጀርባ ላይ የተፈናጠጡ ሹማምንት ላይ የሚደረገው ግምገማም ሆነ ዕርምጃ፣ ሌሎችን ተተኪዎችና በሥራ ላይ ያሉትንም ጭምር የሚያስተምርና ምሕረት የለሽ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግሥታዊ አገልግሎቶች በሚገኙባቸው በየደረጃው በሚገኙ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሰጪዎች፣ በትራንስፖርትና መገናኛ ተቋማት፣ በመሬት አስተዳደር፣ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በፖሊስ፣ በዓቃቤያነ ሕግ፣ በዳኞች፣ በአስተዳደራዊ መዋቅሮች፣ ወዘተ ውስጥ በብልሹ አሠራር በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ ሲጋለጡ አሳማኝ መሆን አለባቸው፡፡ የሕዝቡ ተሳትፎ በግልጽ መታየት አለበት፡፡

ሕዝቡ ዘወትር ‹‹እንቢ›› በማለት በሚታወቀው የቢሮክራሲ አሻጥር የት እንደሚንገላት ያውቃል፡፡ ፍትሕ የት እንደሚጓደልበት ከማንም በላይ ይናገራል፡፡ መብቱ የት እንደሚረገጥበት በትክክል  ያመላክታል፡፡ እነማን በሙስና እንደሚያስቸግሩት ማስረዳት ይችላል፡፡ ግምገማዎቹም ሆኑ ዕርምጃዎቹ የሕዝቡን ይሁንታ የሚያገኙት ዒላማቸውን በትክክል ሲመቱ ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት እየዘረፈ የከበረው ማን ነው? የመሬት ወረራ በማካሄድ የሚዘርፉት እነ ማን ናቸው? የመንግሥት ግብር የሚያጭበረብሩትና የሚተባበሩዋቸው እነ ማን ናቸው? ፍትሕን በገንዘብ የሚሸጡት የትኞቹ ናቸው? ጉቦ ካልተሰጣቸው በስተቀር መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የሚነፍጉትስ የት ነው ያሉት? ወዘተ ተብሎ ከተጠየቀ ምላሹ ያለው ሕዝብ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ግልጽነት ማለት ይህ ነው፡፡

በከተማም ሆነ በገጠር፣ በትልልቅ ከተሞችም ሆነ በትንንሾቹ ከሕዝቡ የተደበቀ አንዳችም ጉዳይ የለም፡፡ የሕግ ክፍተቶችን በመጠቀም ማስፈጸሚያ መመርያ ወይም ደንብ አልወጣም በማለት ለአንዱ መንገዱን ሲያመቻቹ፣ ሌላውን ደግሞ እያስለቀሱ በአንድ አገር ሁለት ዜጎችን የሚፈጥሩ አልጠግብ ባዮችን ሕዝብ ያውቃቸዋል፡፡ የመንግሥት ሕጋዊ የግዥና የጨረታ ሥርዓትን እየተላለፉ ቢጤዎቻቸውን የሚያበለፅጉ ሹማምንትና ምንዝሮች የማይታወቁ ቢመስላቸውም ሕዝቡ ግን ያውቃቸዋል፡፡ በዘር፣ በጓደኝነትና በጥቅም ተጋሪነት ሕገወጥነትን በማንገሥ የቡድን ዝርፊያ የሚፈጽሙትንም እንዲሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሳይገመገሙ ወይም ሕጋዊ ዕርምጃ ሳይወሰድባቸው ርብርቡ ትንንሾቹ ዓሳዎች ላይ ብቻ ከሆነ ያስተዛዝባል፡፡ ለዚህም ነው ግልጽነት የሚፈለገው፡፡

በተለያዩ ሥፍራዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ በሐሰተኛ ሰነዶች ሳይቀር ከግንባታ፣ ከጨረታ፣ ከመሬት፣ ከግብር፣ ከፍትሕ፣ ከትምህርት፣ ወዘተ ማጭበርበሮች ጋር ስማቸው የሚነሳ ሹማምንት በየቦታው አሉ፡፡ ተገቢው የትምህርት፣ የልምድና የብቃት ዝግጅት ሳይኖራቸው በየሥፍራው የተጎለቱም እንዲሁ አሉ፡፡ ሕግና ደንብ ተከትለው መሥራት የማይችሉ፣ ከአድርባይነትና ከአስመሳይነት በቀር ለሥራ የማይመጥኑ፣ ለበላዮች በማጎብደድ ብቻ የሚኖሩ፣ የተቋማትን ጥንካሬ ሽባ እያደረጉ የቡድንተኞችን የበላይነት የሚያሰፍኑና የመሳሰሉትም ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ በሕዝብ ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን ጎልቶ ሌሎች ላይ መዝመት የሚያስገምት ብቻ ሳይሆን፣ አደጋ የሚያመጣ ስለሆነ ግልጽነት ይኑር፡፡

ሁሌም እንደሚባለው ጠንካራ ግምገማዎች ውጤታቸው አመርቂ ነው፡፡ የተልፈሰፈሱ ከሆኑ ግን በሕዝብ ላይ የሚቀልዱ የበላይነቱን ይይዛሉ፡፡ ተገምጋሚው ራሱ ገምጋሚ ይሆንና ንፁኃን ይመታሉ፡፡ እስከ ዛሬ ከነበሩት ልምዶች የታየው ንፁኃን ተሸናፊ ሲሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብ ተስፋ ቆርጧል፡፡ አሁን የማያዳግም ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ሲፎከር እንኳ የሕዝቡ ልብ በጥርጣሬ የተሞላ ለመሆኑ በርካታ ማረጋገጫዎች አሉ፡፡ ሕዝብ ይህንን ያህል ጉዳዩን የሚከትተለው ምሬቱ ከመጠን በላይ በመሆኑ ነው፡፡ በተገመገሙ ሰዎች ላይ የማባረር ዕርምጃ ሲወሰድም፣ እነ እከሌ የታሉ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ጥያቄ አሳማኝ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ነገሩ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከር ግን የብሶቱን መጠን የበለጠ በመጨመር ብጥብጥ መፍጠር ነው፡፡ ግልጽነት የሚያስፈልገው ለዚህ ጭምር ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ከምንም ነገር በላይ ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲሸረሸር ሕገወጥነት የበላይነት ያገኛል፡፡ ሕገወጥነት በተስፋፋ ቁጥር የመልካም አስተዳደር ዕጦት ይባባሳል፡፡ ፍትሕ ይጠፋል፡፡ ሙስና ይነግሣል፡፡ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ ሕዝብ አላስፈላጊ ለሆኑ ችግሮች ይጋለጣል፡፡ ግምገማዎቹና ዕርምጃዎቹ በሙሉ በግልጽነት ላይ ተመሥርተው ሕጋዊውን አካሄድ ይዘው ሲጓዙ ግን፣ የሕዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት ስለሚኖር ውጤታቸው ጥሩ ይሆናል፡፡ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ሕገወጥነትን ማስወገድ ይቅደም፡፡ የሕዝብ ወሳኝነት ያለባቸው ግምገማዎችና ዕርምጃዎች ይኑሩ፡፡ ስለዚህም በመልካም አስተዳደር ላይ የሚደረጉ ግምገማዎችም ሆኑ ዕርምጃዎች ግልጽነት ይኑራቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...