- ዕጣ ለማውጣት የቦርድ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው
- 11,682 ተመዝጋቢዎች ሙሉ ክፍያ ፈጽመዋል
- ተመዝጋቢዎች ቤት የሚያገኙት ሲመዘገቡ በተሰጣቸው መረጃ መሠረት ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት 11 ዓመታት እየገነባቸው ከሚገኙት ቤቶች መካከል፣ መካከለኛና ከዚያ በላይ ገቢ ላላቸው ዜጐች በመገንባት ላይ የሚገኘው የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ዋጋ ለመከለስ የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም እያደረገው ያለው ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ቀንአ፣ ኢንተርፕራይዙ ላለፉት ስድስት ወራት በ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ዙሪያ ያከናወናቸውን ተግባራት ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በተገለጸበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዋጋ ግሽበት በየዓመቱ 12 በመቶ እየጨመረ ነው፡፡ ‹‹ይህ በመሆኑም አስተዳደሩ ተነጋግሮ አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው ዋጋን በሚመለከት ጥናት አድርጐ እያጠናቀቀ ነው፡፡ ጥናቱ በሚመለከተው አካል አስተያየት እንዲሰጥበት ከተደረገ በኋላ ውሳኔ ይሰጥበታል፤›› ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኃይሉ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ታሪክ አዲስ የሆነ ባለ 18 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ቱሪስት ንግድ ሳይት ላይ ተጀምሯል፡፡ በሳይቱ ላይ 11 ሕንፃዎች ይገነባሉ፡፡ 2,346 ቤቶች እንደሚኖራቸውም አስረድተዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በሰንጋ ተራ፣ ክራውን ሆቴል አጠገብ፣ አስኮ፣ እህል ንግድ፣ ሕንፃ አቅራቢ፣ ቦሌ ቡልቡላ (1)፣ መሪ ሳይት፣ ቦሌ አያት (1)፣ ቦሌ በሻሌ፣ ቦሌ አያት (2)፣ ቦሌ ቡልቡላ (2) እና ሰሚት ግንባታ እያካሄደ መሆኑንና በአጠቃላይ ግንባታቸው ከ90 በመቶ በላይ የተጠናቀቀና ከ11 በመቶ በላይ የተገነቡ በድምሩ 379 ብሎኮች ወይም 38,790 ቤቶች መኖራቸውን አክለዋል፡፡
ግንባታቸው ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁ የተገለጹት የሰንጋ ተራ (410 ቤቶች) እና የክራውን (882 ቤቶች) ቤቶች ዕጣ መቼ እንደሚወጣ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹የእነዚህ ቤቶች ግንባታ ከዚህ በኋላ የሚፈጀው የአንድ ወር ጊዜ ነው፡፡ የቀረን በር መግጠም ነው፡፡ ነገር ግን ቤቶቹ በዚህ ቀን ይወጣሉ ብሎ መናገር የእኔ ሥልጣን አይደለም፡፡ መቼ ዕጣ እንደሚወጣ የሚወሰነው ከላይ ያለው ቦርዱ ነው፡፡ ከላይ ውሳኔው ሲተላለፍ ቤቶቹም ይተላለፋሉ፤›› ብለዋል፡፡ የቤቶቹ ግንባታ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ የዘገየው የማጠናቀቂያ ግብዓት እጥረት በመከሰቱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይሉ፣ አሁን ያ ችግር የሚፈታበት አቅጣጫ በመቀመጡ ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ስለዕጣ አወጣጡ የተለያየ ነገር እየተባለ ተመዝጋቢዎች ወዲያና ወዲህ እንዲናጡ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ዕጣው ወይም ቤቶቹ የሚተላለፉት 40/60 ተመዝጋቢዎች ሲመዘገቡ በነበራቸው መረጃ፣ በሞሉት ፎርም መሠረትና በአከፋፈላቸው ቅደም ተከተል መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች ቁጥር 160 ሺሕ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች 6,000 ያህሉ ሲያቋርጡ፣ 154 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ቤታቸውን እየተጠባበቁና በአግባቡ እየቆጠቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ካሉት 154 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ውስጥ 11,682 ያህሉ መቶ በመቶ የከፈሉ መሆናቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ 29 ሺሕ የሚሆኑት 40 በመቶውን መቆጠባቸውን ተናግረዋል፡፡ የተቀሩትም በገቡት ውል መሠረት እየቆጠቡ መሆኑን አክለዋል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን ገልጸዋል፡፡
ተመዝጋቢዎች የሚስተናገዱት እንደገቡት ውልና የክፍያ አፈጻጸም መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ቤቱ ተጠናቆ ሲተላለፍ በቀናትና በሰዓታት ልዩነት እንዳከፋፈላቸው እንደሚስተናገዱ አስረድተዋል፡፡
አዲስ የሚገነቡት የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለ 18 ፎቅ መሆናቸው፣ በተለይ ከውኃና ከአሳንሰር አቅርቦት ጋር ስለሚገጥማቸው ችግርና እንዲሁም መንግሥት በመልሶ ማልማት በሚነሱ የከተማ ክፍሎች ውስጥ እንደሚገነቡ ተናግሮ እያለ ከከተማ እየወጡ ስለመሆናቸው የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ የአንድ ሕንፃ ዲዛይን ሲሠራ በአገሪቱ የሕንፃ አዋጅ መሠረት መሆኑንና አስተዳደሩም በሕጉ መሠረት ዲዛይኖችን መሥራቱንና ሁሉንም ነገር ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱንና የከተማዋን የወደፊት ራዕይ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የሕንፃዎቹ ዲዛይን መሠራቱን ጠቁመው፣ የተለያዩ አገሮችን ልምድ ለመቅሰም ተብሎ ግብዣ የተደረገላቸው አገሮች ስለምቹነቱና አጠቃላይ አሠራሩ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ቢኖርም፣ እየተሠሩ ያሉ ግዙፍ ግድቦች ሥራ ሲጠናቀቅ በቅርቡ የሚፈታ ችግር መሆኑንም አክለዋል፡፡
መንግሥት የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮግራምን ሲጀምር በአሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ እንደሚገነባ መግለጹን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ አሁንም እየተገነቡ ያሉት ሕንፃዎች በተባለው መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግን ማዕከል ላይ ብቻ እየተባለ የሕዝቡን የቤት ፍላጐት ማርካት ስለማይቻል አማራጮችንም ማየት ተገቢ እንደሆነም አክለዋል፡፡
በ40/60 ኮንዶሚኒየም ፕሮግራም ዳግም ምዝገባ ስለመካሄዱ ተጠይቀው፣ በ40/60 ፕሮግራም ላይ ምንም የተባለ ነገር እንደሌለ አሳውቀዋል፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ግን በ20/80 ኮንዶሚኒየም ፕሮግራም ላይ የሽግሽግ ምዝገባ ይኖራል ማለቱንና ገና በመመርያ አለመፅደቁን ጠቁመዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ስድስት ወራት የማጠናቀቂያ ዕቃዎች እጥረት እንዳጋጠሙት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላት፣ የሥራ ተቋራጮች የሥራ መርሐ ግብር ከሥራው ጋር ተጣጥሞ ሥራውን በጊዜው አለመጀመር፣ የብረት እጥረት (አሁን 40 ሺሕ ቶን ብረት ጂቡቲ ወደብ ላይ ደርሷል)፣ የሰው ኃይል እጥረትና ሌሎችም ተግዳሮቶች ለቤቶቹ ግንባታ መጓተት ዓይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ አስተዳደሩ የ40/60 ቤት ልማት ከጀመረ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት የሆነው ሲሆን፣ ለግብዓት ማምረቻና ለግንባታ የሚሆን 176 ሔክታር መሬት ከሊዝ ነፃ ድጋፍ ማድረጉን፣ ለ2008 በጀት ዓመት ለሚጀመሩ ቤቶች 57 ሔክታር መሬት ተዘጋጅቶ ርክክብ መደረጉን አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ለ60,000 ዜጐች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ በ2008 በጀት ዓመት ለ884 ዜጐች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩንና የ50 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩን አቶ ኃይሉ አክለዋል፡፡