ለሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ቡድን ጥር 27 እና 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሚያደርገው ውድድር ወደ ሞሮኮ ኦጋዲር ከተማ ያቀናል፡፡
በማጣሪያ ውድድሩ ሁለት ሴት አትሌቶች ማለትም ናርዶስ ሲሳይና መታደል ሁነኛው፣ እንዲሁም በወንድ አትሌቶች ሲሳይ ባይከዳኝ ሰለሞን ተፈራ ይሳተፋሉ፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝ ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ እንደተናገሩት ከሆነ ‹‹ከሥነ ልቦና፣ ከቴክኒክና ከታክቲክ አኳያ በኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድሩ ድል ለማቀዳጀት ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡
ለሪዮ 2016 ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶች ማለፍ እንዲችሉ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡
የሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን መሪና የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ በበኩላቸው ‹‹የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለዓለም አቀፍ ቴኳንዶ ቡድን ከዚህ ቀደም ያደረጋቸው ሁሉ አቀፍ ድጋፎች እንደተጠበቁ ሆኖ ለቡድኑ የደርሶ መልስ የትራንስፖርትና የትጥቅ ድጋፍ ያደርጋል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በዘርፉ ጠንካራና ተስፋ ሰጪ የሆኑ አትሌቶችን እያፈራ እንደሆነ በግምገማችን እያረጋገጥን ነው በማለት አቶ ታምራት አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ከ250 በላይ አትሌቶች ልምምዳቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በቦክስ፣ በውኃ ዋናና እንዲሁም በቴኳንዶ አጠቃላይ ከ76 በላይ ልዑካን ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዘንድሮው 31ኛው ኦሊምፒያድ ሁለት ወርቅ፣ ብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ ማቀዱን መናገሩ ይታወሳል፡፡