Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልውበትና ጤና በወይባ ጢስ

ውበትና ጤና በወይባ ጢስ

ቀን:

ውበት እንደየተመልካቹ በልዩ ልዩ መንገድ እንደሚገለጸው ሁሉ፣ መዋቢያዎችም አንዳቸው ከሌላቸው ይለያሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች እንደየባህላቸው የውበት መገለጫ አድርገው የሚያስቀምጧቸው መሥፈርቶች አያሌ ናቸው፡፡ በመሥፈርቶቹ መሠረት ውብ ሆኖ ለመታየት ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶችም አያሌ ናቸው፡፡ ግብዓቶቹ ከቦታ ቦታ ይለያዩ እንጂ፣  ተፈጥሮን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው በተወሰነ መልኩ አንድ ያደርጋቸዋል፡፡

እንደ አፈርና ዕፀዋት ያሉ ተፈጥሮ ለሰው ልጅ የቸረቻቸው ሀብቶች ዕፀዋቱ ለምግብ፣ አፈርና ዕፀዋቱ በአንድ ላይ ደግሞ ለመጠለያና ለአልባሳት በመዋል በሰው የዕለት ከዕለት ሕይወት ከሚጫወቱት ጉልህ ሚና ባሻገር፣ መዋቢያ ሲሆኑም ይስተዋላል፡፡ ከሰሞኑ የጐበኘነው ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በክልሉ ደቡባዊ ዞን፣ ማይጨው ከተማ ስንዘዋወር በተለያየ ዕድሜና የኑሮ ደረጃ ያሉ ነዋሪዎች በተፈጥሯዊ ግብዓቶች ተውበው ተመልክተናል፡፡ ወቅቱ የጥምቀት በዓል የተከበረበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ብዙዎች ደመቅ ብለው ተስተውለዋል፡፡

እንደ ምሳሌ መጥቀስ የሚቻለው የራያ አካባቢ ወንዶች የሚለዩበትን ረዥም ዘንግና መፋቂያ ነው፡፡ በተለይም ወጣቶች አምረው መታየት የሚሹበት ወቅት በመሆኑ ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው በጥንቃቄ ይዋባሉ፡፡ በራያ አካባቢ የሚዘወተረው ልብስ ሽፋ ነጭ ሲሆን፣ በቅቤ ሲርስ ጠቆር ይላል፡፡ የአካባቢው ተወላጅ ሴቶች እንደየዕድሜያቸው ራሳቸውን የሚያስውቡበት የሹሩባ አሠራር አላቸው፡፡ በአንገታቸው፣ በጆሯቸው፣ በጣታቸውና በእጃቸውም የሚያደርጓቸው ጌጣጌጦችም ውበት ያላብሷቸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ራያ አካባቢ የሚዘወተረው የወይባ ጢስ ሴቶች ከሚዋቡባቸውና ጤናቸውንም ከሚጠብቁባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ለዓመታት በይበልጥ በገጠራማ አካባቢዎች ይካሔድ የነበረው የወይባ ጢስ ዛሬ ዛሬ ከተማ ቀመስ በሚባሉ አካባቢዎችም ተለምዷል፡፡ ሴቶች ለአቅመ ሔዋን ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ለውበት በሌላ በኩል ደግሞ ለጤናም ይታጠናሉ፡፡ የወይባ ጢስ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ከመሆኑ ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሔድበት መንገድ አለ፡፡

በራያ በራሳቸው ተነሳሽነት አልያም በቤተሰብ ወይም በፍቅር ጓደኛ ግፊት ለመታጠን ሲዘጋጁ፣ የሚታጠኑበትን እንጨት የሚሰበስቡላቸው የሚቀርቧቸው ወንዶች ናቸው፡፡ የአንዲት ሴት እጮኛ ወይም ባለቤት፣ ያላገባች ከሆነች ደግሞ ወንድሞቿ ወደ ጫካ ሔደው የምትታጠንበትን እንጨት ይሰበስባሉ፡፡ ለወይባ ጢስ ተመራጭ የሆነው እርጥብ የወይራ እንጨት ቢሆንም፣ አንዳንዴ ሌሎች ዓይነት እንጨቶችም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ከራያ ውጪ በሌሎች አካባቢዎች ከወይራ ውጪ ያሉ ቅጠሎችና ስራስሮች በመጠቀም የሚታጠኑ አሉ፡፡

የአካባቢው ተወላጅ ሀፍቱ ከበደ እንደሚናገረው፣ እንጨት ለመሰብሰብ ወደ ጫካ የሚሔዱት ሁለት ወንዶች ናቸው፡፡ የእንስቷ እጮኛ ወይም ባለቤት የቅርብ ጓደኛ የሆነው ሰው አብሮ የሚሔድ ሲሆን፣ ቁጥራቸው የሚጨምርበትም አጋጣሚ አለ፡፡

ወደ ጫካ ለመሔድ ቀን ቆርጠው ቀጠሮ ይይዙና ተሰባስበው ይሔዳሉ፡፡ እንጨቱን በሚቆርጡበት ወቅት ስለተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያወሩ ሲሆን፣ አዲስ ሙሽራ ከሆነ በትዳር ሕይወቱ ስለሚጠብቁት ነገሮች ያወጋሉ፡፡ እንጨቱን ተሸክመው ከጫካ ሲመለሱ በሚያገኙት ወንዝ ይታጠባሉ፤ ከወንዶቹ አንዱ ሙሽራ ከሆነ ደግሞ አብሮት የሔደው ጓደኛው ፀጉሩንና ልብሱን ያስተካክልለታል፡፡

ሴቷ የወይባ ጢስ የምትታጠነው በእናቷ ቤት ነው፡፡ በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ደግሞ ገንዘብ አስከፍለው አገልግሎቱን የሚሰጡ ግለሰቦች አሉ፡፡ ሀፍቱ እንደሚለው፣ ወንዶቹ ወይራ ይዘው ወደ ሴቲቷ እናት ቤት ሲሔዱ አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ ያመጡትን እንጨት ከፈለጡ በኋላ ወደቤት ገብተው ወተት ይጠጣሉ፡፡ ‹‹የራያ ወንድ እጮኛው ወይም ባለቤቱ ጢስ በምትገባበት ወቅት ይንከባከባታል፤›› ይላል ሀፍቱ፡፡ የወይባ ጢስ ለመግባት የሚመረጥ ልዩ ጊዜ ስለሌለ በበዓላት እንዲሁም በአዘቦት ቀንም ሊካሔድ ይችላል፡፡

የወይባ ጢስ ጥሩ ገፅታና መልካም ጠረን እንዲኖር ያስችላል ተብሎ ስለሚታመን አዘውትረው የሚታጠኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ሰውነትን በተለይም ወገብና ማህፀንን ለማጠንከር እንደሚረዳ ይነገራል፡፡ የወር አበባ ወቅት ያለ ሕመምን ለመቀነስ፣ መሀኖች መውለድ እንዲችሉ ለማድረግም የወይባ ጢስ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ ወይባ ጢስ አዘውትረው ከሚገቡ አንዷ አበባ ገብረሕይወት ናት፡፡ ለአቅመ ሔዋን የደረሰች፣ የታጨች ሴትና የወለደች ሴት ጢስ ሲገቡ ያለው ሥርዓት እንደሚለያይ ትናገራለች፡፡

ያላገባች ሴት የወይባ ጢስ የምትገባው አምራ ለመታየትና ትዳር ለማግኘትም ነው፡፡ የታጨች ሴት ደግሞ ውበቷን ለማጉላት ትጠቀምበታለች፡፡ የወለዱ እናቶች ሰውነታቸው እንዲጠነክር፣ ከወለዱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጢስ ይገባሉ፡፡ አግብታ የፈታች ሴት ጢስ ስትገባ በትግርኛ ‹‹ዕጣን ግብኣ›› እየተባለ ይነገርላታል፡፡ ቀትር ላይ ፀሐዩ ሰውነት እንደሚጐዳ ስለሚታመን የወይባ ጢስ መታጠን የሚካሔደው ምሽት አካባቢ ነው፡፡ ከታጠኑ በኋላ ሰውነታቸው እንዲቀዘቅዝ ለጥቂት ደቂቃዎች ከቤት አይወጡም፡፡

የታጨች ሴት አንዴ ታጥና ትወጣለች፡፡ የወለደች ሴት ግን እየገባችና እየወጣች ትታጠናለች፡፡ ቅቤ አናቷ ላይ ይደረግላታል፡፡ ገንፎና ወተትም ይሰጣታል፡፡ አበባ እንደምትለው፣ ከግማሽ ሰዓት ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ መታጠን ይቻላል፡፡

የሚታጠኑበት እንጨት የሚገባው ከከብት እዳሪ በሚሠራ ጐድጐድ ያለ ቦታ ነው፡፡ ከጉድጓዱ በላይ ሴቲቷ በምትታጠንበት ወቅት የምትለብሰው ሸማ የሚያርፍበት ከፍታ አለ፡፡ ሸማ ጢሱ እንዳይወጣ አፍኖ የሚይዝ ወፍራም ጨርቅ ነው፡፡ ከሸማው በላይ ደግሞ ከከብት ቆዳ የተሠራ ቁርበት ይለበሳል፡፡ አንድ ሴት ከመታጠኗ በፊት መላ ሰውነቷን ቅቤ ከተቀባች በኋላ ልብሷን አውልቃ ሸማና ቁርበት ደራርባ ጐድጐድ ባለው ቦታ ትቀመጣለች፡፡ ቅቤው ጢሱ ሰውነቷን እንዳይጐዳው ይከላከልላታል፡፡ በዕድሜ ከፍ ያሉና ልምዱ ያላቸው ሴቶች ረዘም ላለ ጊዜ ይታጠናሉ፡፡

አበባ እንደምትለው፣ በምትታጠንበት ወቅት ቆዳዋ ይለሰልሳል፤ ጥሩ ስሜትም ይሰማታል፡፡ ገጠር አካባቢ በብዙዎች መኖሪያ ቤት የወይባ ጢስ ያለ ሲሆን፣ ከተማ ውስጥ ለወለደች ሴት ብቻ የሚያዘጋጁም አሉ፡፡ እሷ እንደምትናገረው፣ በአካባቢው አንዲት ሴት በተደጋጋሚ ጢስ መግባቷ ጥንካሬዋንም ያሳያል፡፡ ያነጋገርናት አንድ ወጣት የምትኖረው በማይጨው ከተማ ሲሆን፣ ቢያንስ በወር አንዴ 100 ብር እየከፈለች እንደምትታጠን ትገልጻለች፡፡ ገጠር አካባቢ እንደሚደረገው ወደ እናቷ ቤት ባትሔድም፣ የወይባ ጢስ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቦታዎች እንደ አማራጭ ትጠቀማለች፡፡ ወይባ ጢስ ለመገጣጠሚያ ጥንካሬ በተለይም ለማህፀን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ ትናገራለች፡፡  

ሴቶች ከጢሱ በተጨማሪ  እንሶስላ ይቀባሉ፡፡ ያልታጨች ሴት እጇን ብቻ ትቀባለች፡፡ ያገባች ሴት እጇንና እግሯንም እንሶስላ ትቀባለች፡፡ በአካባቢው ሰዎች የሚተጫጩት በተለያየ ጊዜ ቢሆንም፣ በአዲስ ዓመትና በጥምቀት በዓል ያመዝናል፡፡ ወንዶች የሴቶች ፀጉር ላይ ሣር በመሰካት ወይም ሎሚ በመወርወር ፍላጐታቸውን ካሳዩ በኋላ ሽማግሌ ይልካሉ፡፡

የወይባ ጢስ አገልግሎትን በዘመናዊ መንገድ በማዘጋጀት የሚሠሩ ተቋሞች እየተበራከቱ ነው፡፡ ወይባ ጢስን ስቲምና ሳውናን ከመሰሉ በጢስ ኃይል ለውበትና ለጤና እንክብካቤ የሚውሉ መንገዶች ጋር የሚያነጻጽሩም አሉ፡፡

ስለቱሪስት መስህቦች የሚያትቱ ድረ ገጾችም የወይባ ጢስን እንደ አንድ መስህብም ያስቀምጣሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ቲፕስ ዶት ኮም፣ በተለያዩ አካባቢዎች በባህላዊ መንገድ የሚካሔዱ መዋቢያዎች በሚል ከሚያስቀምጣቸው መካከል የወይባ ጢስና ቆቆባ ጡሽ (ጢስ) ይገኙበታል፡፡   

ከወይባ ጢስ ጋር አያይዘው ብዙዎች የሚጠቅሷቸው ሳውናና ስቲም ከኢትዮጵያ ውጭም ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ከውበት በተጨማሪ ሰውነትን ለማፍታታትና ለደም ዝውውር፣ ፍቱን መድኃኒት እንደሆኑም ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...