Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹ትምህርት ቤቴ ማርና ወተቴ››

ትኩስ ፅሁፎች

በትግራይ ክልል በኣጉላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሚማሩት ተማሪዎች መካከል፣ በማርፈዳቸው ምክንያት በሩ ሲዘጋባቸው የወሰዱት አማራጭ፡፡ አራቱ ተማሪዎች የተንጠላጠሉበት ሰሌዳ ላይ ከሰፈረው ራዕይ ውስጥ አንዱ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ሁሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚል ይገኝበታል፡፡ (ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን)

* * *

ሳይፀልዩ ማደር

የተራበ ነብር ከሩቅ ተመልክታ

ሚዳቋ ፀለየች …

‹‹አውጣኝ አውጣኝ›› አለች ለፈጠራት ጌታ

ነብሩም ተርቦ

ወደ አምላኩ ቀርቦ

ሚዳቆዋን አይቶ –

አንጀቱ ከሆዱ እንደተጣበቀ

ፈቅዶ እንዲሰጠው – አምላኩን ጠየቀ

የሁላችን ሠሪ ፀሎታቸውንም – ሰማቸውም ፈጣሪ

አምላክም በድምፁ – ሚዳቆዋን አላት

‹‹እሩጠሽ አምልጪ – ከበረታው ጠላት››

      ነብሩንም አለው – ‹‹እሩጥ ተከተላት

      ምግብ አድርገህም ብላት››

      ሚዳቆዋ ስትሮጥ

      ከነብር ለማምለጥ

      ነብሩም ሲከተላት

      ሆዱን ሊሞላባት

ቋጥኙን ስትዘል እግሯ ተስንፈንጥሮ

ሆዱን ብትረግጠው የተኛው ከርከሮ

ከእንቅልፉ ሲነቃ ልክ ሲደነብር

ጉሮሮውን ያዘው የፀለየው ነብር

አውጣኝ ያለው ወቶ – አብላኝ ያለው በላ

ሳይፀልይ ያደረው ከርከሮ ተበላ

  • ገጣሚ በረከት በላይነህ

****

ለአንድ ስኒ ሻይ እጥፍ ዋጋ የተጠየቀው በተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ተጎዳ

በቱርክ ከኢስታንቡል አቅራቢያ በምትገኘው ኮቺሊ ከተማ በሚገኝ ሻይ ቤት ለአንድ ስኒ ሻይ እጥፍ ዋጋ የተጠየቀው ተስተናጋጅ በተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ተጎዳ፡፡

በሻይ መጠጣት ባህል በምትታወቀው ቱርክ፣ በአብዛኛው ሻይ ቤቶች የአንድ ስኒ ዋጋ 30 የአሜሪካ ሳንቲም ሲሆን፣ ሰውየው የገባበት ቤት ግን የሚያስከፍለው 65 የአሜሪካ ሳንቲም ነው፡፡

የተጠየቀውን ዋጋ ክፈል አልከፍልም በሚል ከሻይ ቤቱ ባለቤት ጋር ግብግብ የገጠመው ተስተናጋጅ፣ በጓደኞቹ ገላጋይነት ከሻይ ቤቱ ቢወጣም፣ መኪናው ውስጥ ሆኖ አራት ጊዜ ወደ ሻይ ቤቱ በመተኮሱ አንድ ተስተናጋጅ ተጐድቷል፡፡ ተጠርጣሪውም በፖሊስ እየተፈለገ ነው፡፡

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በግሪክ ባህል ጥቁር ሻይ የሚቀርበው ቱሊፕ ቅርፅ ባለው (ከወገቡ ገባ ብሎ አፉ ጋር የሚሰፋ) የሻይ ስኒ ነው፡፡ ሻይ በቱርክ ባህል ታዋቂ ትኩስ መጠጥ ሲሆን የባህል መገለጫም ነው፡፡ በቱርክ አንድ ሰው በዓመት አንድ ሺሕ ስኒ ሻይ ይጠጣል ተብሎ ይገመታል፡፡ 

* * * * *

አወዛጋቢው የድንግሎች ነፃ ትምህርት ዕድል

የደቡብ አፍሪካዋ ክዋዙሉ ናታል ግዛት ከንቲባ ለ16 የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ድንግል ሴቶች ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት የተያዘውን ዕቅድ እንደሚደግፉ አስታወቁ፡፡ ቢቢሲ ከንቲባውን ዱቡ ሚዚቡኮን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ውሳኔው የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭትና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ይረዳል፡፡ ከንቲባው እንደተናገሩት፣ ሴቶቹ ስለድንግልናቸው ማረጋገጫ ምርመራ ማካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡

የከንቲባውን ውሳኔ የደገፉ የነቀፉም ያሉ ሲሆን፣ በግዛቱ መጠነኛ ውዝግብ አስነስቷል፡፡ ከደገፉት አንዷ የከንቲባው ባለቤት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪካው ፒፕል ኦፖዚንግ ውሜን አብዩዝ (ፒኦደብሊውኤ) በበኩሉ ነፃ የትምህርት ዕድሉን ለማግኘት የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የሴቶችን መብት የሚጋፋና ክብራቸውን ዝቅ የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡ የድንግልና ምርመራ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መፍትሔ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት የሚደገፈው ኮሚሽን ፎር ጄንደር ኢኳሊቲም አቋሙን ተችቷል፡፡ የከንቲባው ዓላማ መልካም ቢሆንም አካሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወደ 6.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እንደሆኑና ከአሥር ሰዎች ቢያንስ አንዱ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር ይገመታል፡፡ ውሳኔው የተላለፈበት ግዛት ከአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የበሽታው ስርጭት የሚታይበት ነው፡፡ ከንቲባው ሴቶቹ የድንግልና ምርመራ የሚደረግላቸው በዩኒቨርሲቲው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ዓመታዊ የዙሉ በዓል ላይ ድንግል ሴቶች ለንጉሥ ጉድዊል ዝዌልተኒ ለመደነስ በሚመረጡበት አጋጣሚ የሚመረመሩ ይሆናል፡፡

* * *

ውሻዋ ሰባተኛ ሆና ግማሽ ማራቶን ጨረሰች

ካናዳ አላባማ ውስጥ በአሳዳሪዎቹ ለሽንት የተለቀቀችው ውሻ ድንገት የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድርን ተቀላቅላ ሰባተኛ ሆና መጨረሷን ዘ አንዲፔንደንት ዘገበ፡፡ የሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜ ያላት ውሻዋ ሉዲቫን ድንገት የሩጫ ውድድሩን መቀላቀሏ ብዙዎችን ያስደነቀ ክስተት ነበር፡፡ የውድድሩን መጀመር የሚያበስረው ጥይት መተኮስን ተከትሎ ውሻዋ እንደ ሯጮቹ ተንቀሳቀሰች፡፡ 13.3 ማይል የሆነውን የውድድሩን ዙር በመሮጥ በአንድ ሰዓት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሩጫውን ልትጨርስም ቻለች፡፡ ውሻዋ ሩጫውን እንዲህ ያጠናቀቀችው በመንገዷ ያጋጠማትን የሞተ ጥንቸል ለማየት፣ መስክ ላይ ተሰማርተው ከነበሩ ላሞች ጋርም ቆም ብላ ለመጫወት ሁሉ ደቂቃዎችን አጥፍታ ነው፡፡ የውሻዋ አሳዳሪ ሚስ ሀምሊን የውሻቸውን ገድል የሰሙት የውሻቸው ድልን የሚመለከቱ መልዕክተኞችና ፎቶግራፎች ሞባይል ስልካቸው ላይ ሲላክላቸው ነበር፡፡ ውድድሩን አራተኛ ሆኖ የጨረሰው ጂም ሴልመንስ ውሻዋ በመሀል አቋርጣ ትወጣለች የሚል እምነት እንደነበረው ነገር ግን ከኋላ ድምጿን በሰማ ቁጥር ይገረም እንደነበር ገልጿል፡፡ 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች