የሸዋው ንጉሥ የነበሩት አፄ ምንሊክ ዋና ከተማቸውን ቀዝቃዛና የአየር ንብረቱ ብዙም ተስማሚ ካልሆነው የእንጦጦ ከፍታ ትንሽ ኪሎ ሜትር ወደ ደቡብ ወረድ ብሎ፣ ከባህር ወለል በላይ 25,000 ሜትር ከፍታ ላይ ወደሚገኘው ረባዳ ሥፍራ አዛወሩ፡፡ ይህንን ሥፍራም ባለቤታቸው የነበሩት እቴጌ ጣይቱ በ1879 ዓ.ም አዲስ አበባ ብለው ሰየሙት፡፡
ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፍፃሜ ጀምሮ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዋና መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ አዲስ አበባ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነገሥታቱ ዋና መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር የአገሪቱ ዋነኛ የንግድ ማዕከል ሆና ታገለግላለች፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ስትቆረቆር 120,000 አካባቢ የሚሆን ሕዝብ ይኖርባት የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን 4.5 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን ሕዝብ መኖሪያ ሆናለች፡፡
አፄ ምንሊክ በወቅቱ በነበረው ድርቅ፣ ጦርነትና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የተነሳ ዜጐች ለከፋ ረሃብና ስቃይ እንዳይዳረጉ ንግድ አንዱ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ፖሊሲ ነደፉ፡፡ በዚህም የተነሳ በወቅቱ የሲራራ ነጋዴ እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ነጋዴዎች ሕጋዊ በሆነ ዘዴ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲያካሂዱ ተደረገ፡፡ በዚህም ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ ተነስተው በሐረር አድርገው ዘይላ ወደብ ድረስ በእግራቸው በመሄድ ይነግዱ ነበር፡፡
እነዚህ ነጋዴዎች ይደርስባቸው ከነበረው ዝርፊያና እንግልት ባሻገር የአገሪቱን ኢኮኖሚ በዘመናዊ መንገድ ለማዘመን የባቡር ሐዲድ እንዲዘረጋ አደረጉ፡፡ በዚህም የተነሳ ንጉሠ ነገሥቱ የባቡር ሐዲድ ግንባታውን ሥራ መጋቢት 1886 ዓ.ም አስጀመሩ፡፡
የሐዲዱ የመጀመሪያ ክፍል ተጠናቆ ሐምሌ ወር 1893 ዓ.ም ሥራ ጀመረ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በፈረንሣይ ካፒታል ቁጥጥር ሥር ያለው የባቡር ሐዲድ እስከ አዲስ አበባ ስለሚዘልቅበት ሁኔታ በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መካከል ድርድር ቀጥሎ፣ በ1909 ዓ.ም የመጀመሪያው ባቡር ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ገባ፡፡
እነዚህ የታሪክ ክንውኖች ከዛሬ ዘጠናና መቶ ዓመታት በፊት የተከወኑ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ የዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሆና በታሪክ ተመዝግባ ትገኛለች፡፡
ይህ ከላይ ሰፋ ያለ መነሻ ሐሳቤን “የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን” በሚል ርዕስ በአንድርዜይ ባርትኒስኪና ዮዓና ማንቲስ ኒየችኮ ተጽፎ በዓለማየሁ አበበ ተተርጐሞ ከቀረበልን መጽሐፍ የወሰድሁት ነው፡፡
ከላይ የተነበበውን ሐሳብ ለመጥቀስ የፈለግሁት ሰሞኑን “KTN TV” የተሰኘው የኬንያ የቴሌቪዥን ጣቢያ “ኢትዮጵያ ለምን ከምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛዋ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሆነች?” የሚል በድረ ገጹ ላይ ለጥፎ ብዙ ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን በሰጡት የተሸራረፈ አስተያየትና ሐሳብ ላይ የራሴን ሐሳብ ለመስጠት ይረዳኝ ዘንድ በአባሪነት የተጠቀምኩት ነው፡፡
ድረ ገጹ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንደሆነችና በኢኮኖሚያቸው የተሻለ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ይጠቅሳል፡፡ የአዲስ አበባን ቀላል ባቡር በፊት ገጹ ላይ ለጥፎ ብዙ ሐሳቦችን ያሠፈረው ይህ ድረ ገጽ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረንን ተሰሚነትና ኃያልነት እንዲሁም ወደፊት ሊኖረን ስለሚችል ዕጣ ፈንታ ሰፋ ያለ ዘገባ አቅርቧል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባን የቀላል ባቡር ትራንስፖርት በሰፊው በመቃኘት፡፡
ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ተዘርግቶ የነበረው የባቡር ሐዲዳችን ከሞተበት ተነስቶ ዳዴ ማለት ከጀመረ ዓመት ያልሞላው ገና ሕፃን ልጅ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሚዲያዎች ብዙ እየተወራለት ይገኛል፡፡ ይህንን የተጋነነ ዜናና መረጃ በተለያዩ ሚዲያዎች ስሰማ “ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መፍለቂያ፣ የአክሱምና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ፣ የፋሲለደስና የጀጐል ግንብ የኪነ ሕንፃ ቱሩፋት ውጤቶች ባለቤት፣ ወዘተ መሆኗን ዕውን ያውቁ ይሆን? ብየ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ይህ የትራንስፖርት ዘዴ ለአገራችን አዲስ አይደለምና፡፡
ከተለጠፈው መረጃ ወረድ ብሎ ብዙ ግለሰቦች ስለ ባቡራችን ሐሳብና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሐሳቦቹና አስተያየቶቹ ብዙ ሐሳብ የረገጡና አንዳንዶቹ ረብ የሌላቸው ቢሆንም፣ እኔ ግን የሁሉንም ሐሳብና አስተያየት ጠቅለል አድርጌና ወደ አንድ ጐራ አምጥቼ የራሴን ዕይታ ለማስቀመጥ ወደድሁ፡፡ ከዚያም ብዕሬንና ወረቀቴን አዋደድሁ፡፡
ብዙኃኑን ያስማማ የሚመሰለው ሐሳብና አስተያየት፣ “ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ ሥር ነቀል የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ሊያስገኙ በሚችሉና ለታይታ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተጠመደች ነች፤” የሚል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱት የአገሪቱን ሠራዊት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ በስፋት በማሳተፍ በአካባቢው ያላትን የጂኦ ፖለቲካል ኃያልነት ከፍ ማድረግ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል በአገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ ለውጥ ሊያመጣ እንዳልቻለና ወደፊትም እንደማይችል ያብራራሉ፡፡ ባቡራችንንም ለሚዲያና ለፖለቲካ እንጂ ረብ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል በመጥቀስ፡፡
አገራችን በፖለቲካዊ አቅሟ ኃያል ተብላ ትጠራ የነበረበት ጊዜ እንደነበር ታሪክ ምስክርነቱን አይክድም፡፡ ለምሳሌ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስምብሩተስ የተባለው የአክሱም መሪ ሜሮኤን (ዛሬ መሀል ሱዳን እየተባለ የሚጠራው) እና ሶማሊያን ያስገብር እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
ይህ ደግሞ አገራችን በወቅቱ ምን ያህል ኃያልና በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅሟ ጡንቻዋ የፈረጠመ እንደነበረ እንረዳለን፡፡
ነገር ግን ትናንት በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅሟ ኃያል የነበረች አገር ዛሬ የድህነት ተምሳሌት ሆነች፡፡ አንድ ለየት ያለ ነገር ስንሠራ እንደ አዲስ በመቁጠር የዓለም ዓይንና ጆሮ መሆን ጀመረ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በኮሪያ ልሳነ ምድር ተሳትፎ ከነበረው ከቃኘው ጦር አንስቶ እስከ አሁኑ በአሚሶም ሥር ሆኖ አልሸባብን በመዋጋት ከፍተኛ ድል እያስመዘገበ ስላለው የጦር ሠራዊታችን ብዙ ብለዋል፡፡
ስለባቡራችን አንስተን በአስተያየት ሰጪዎች ዘዋሪነት ሐሳባችንን ፊቱን በማዞር አገራችን በዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ግዴታዎች ላይ ስላላት ርዕሰ ጉዳይ ትንሽ እንድንል ተገደድን፡፡
እንደነዚህ ዓይነት ዓለም አቀፋዊ ግዳጆች ላይ መሳተፍ የቆየ ኃያልነትንና ቅቡልነትን ጠብቆ ለማቆየት የራሱ ዋጋ ቢኖረውም፣ እንደ አስተያየት ሰጪዎች (እኔም እጋራዋለሁ) እንደ ኬንያ አንገታችንን ደፍተን ለሕዝባችን ኑሮ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር የተሻለ ነው፡፡ ኅብረተሰባችንን ከጫፍ ጫፍ በማንቀሳቀስና በአንድ ጎን እንዲሠለፍ በማድረግ እንደ ጎረቤት አገራችን ኬንያ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡
ቅድሚያ በልተን ማደር አለብን፡፡ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ጊዜያችንና ጉልበታችን ከማባከን ወጥተን የድህነት ቀንበርን ለመስበር መሠለፍ አለብን፡፡
ከድህነትና ኋላቀርነት ያልተላቀቀውን አርሶ አደር ወገናችንን ከጎናችን አሠልፈን ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ለውጥ ለምናደርገው ሽግግር ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ ከደሃ አገሮች የአለቅነት አባዜ ወጥተን ራሳችን ለራሳችን መሆን አለብን፡፡
በምሥራቅ አፍሪካ ያለንን ጂኦ ፖለቲካዊ አቅም በኢኮኖሚውም መድገም አለብን፡፡ ኬንያውን አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉን በስደት ሳይሆን በብልፅግና እንድንታወቅ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ‹‹KTN TV›› እንዳለው የአዲስ አበባችን የቀላል ባቡር ትራንስፖርት ብቸኛው የምሥራቅ አፍሪካ እንደሆነው ሁሉ በብልፅግናም ብቸኛ መሆን አለብን፡፡ ከዘጠናና መቶ ዓመታት በኋላ ያገኘነውን ባቡር ለሚዲያና ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን ተጨባጭ የኅብረተሰቡን ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ መቃኘት አለበት፡፡ አሠራሩ ቀልጣፋና ኅብረተሰብ ተኮር መሆን አለበት፡፡ ያኔ እንደ ጃፓን ከውድቀት እንነሳለን፡፡ እንደ አሜሪካና ጀርመን እውነተኛ ኃያል አገር እንሆናለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡