Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‘በልብ ነው እንጂ በአፍ አይለፈልፉም!’

እነሆ መንገድ። ከሜክሲኮ ወደ አየር ጤና ልንጓዝ ነው። “አልገሩትም ወይ ያንን ፈረስ፣ እዩት በመንገድ ሲፈነደስ። አልገሯትም ወይ ያችንስ በቅሎ፣ ዘር ትቆጥራለች ከገብስ ቆሎ፤’ አለ ያገሬ ሰው። እንዲያው ነው የሚያስለፈልፈን፤” ትላለች ነጭ ሻሽ የጠመጠመች ተሳፋሪ። “ይቅርታ ያልተገመገመ ቅኔ መዝረፍ ክልክል ነው፤” አላት ወያላው ሲነጅሳት። ለካ እየገመገሙ ማዘረፍም አለ እባክህ? ደግሞ ቅኔ በየት አገር ነው የሚገመገመው?” ስትለው፣ “ስለአገር ባላውቅም ስለታክሲዬ ሕግ የማውቀው እኔ መሰለኝ፤” ይላታል። “እግዚኦ ዕውቀት በመሰለኝ የሚደመደምበት ዘመን፤” ማሽሟጠጥ ጀመረች። “ወዳጅ ወዳጁን ጠንቅቆ ሲያውቀው፣ ፍረደኝ ብሎ ሸንጎ ገተረው። ሸንጎው ሲበተን ህሊና ሲቀር፣ የኋላ ኋላ ሀቅ አትቀበር፤’ አልል መሰለህ እኔ ደግሞ። ስማ ልንገርህ፤ ጥጃ በፉጨት ከብት በአሞሌ በሚነዳበት አገሬ ቀርቶ ዓይን ላጠፋ ዓይኑ በሚጠፋባት ባቢሎንም ብኖር ለመከልከል ሕግ አልገዛም፤” ስትለው ወያላው ተጠማዞ ታክሲዋ መሙላቷን አረጋገጠና “የሚናገሩትን አያውቁምና ከክፉ አትቁጠሩባቸው’ ብያለሁ፤” ብሎ በሩን ከረቸመው።

ይኼኔ ደግሞ አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት በመገረም መለስ ብሎ አይቷት፣“በሐሙራቢ ሕግ መሠረት ዓይን ብታጠፊ ዓይንሽን ነው። ዘንድሮ እኮ ቅኔው ሳይሆን ከቅኔው ጀርባ ያሉት ናቸው የሚጠኑት። አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ ሆኗል ጨዋታው እህቴ፤” ብሏት ዝም። “ምነው እናይ የለም እንዴ?” ብትለው “ምኑን?” ቢላት “አንድ አይደለም ሺሕ ሚሊዮን ሕዝብ እየነደደ አንድ እየፈረደ እያየን አይደለም ወይ?” ብላው እርፍ። “ሆሆ ሴትዮ ዛሬ ምን ነክቶሻል? እሱን በምርጫ ካርድ ማስተካከል ነዋ፤” መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ አላስችል ብሎት ገባበት። “ዋ! ብያለሁ። ኋላ ሁለት መቶ ፐርሰት አድርሳችሁት ድሉን እንዳታብሱት፤” ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ቀውላላ ሳቀ። መቶውስ የማን ሆኖ ነው ሰው ለሁለት መቶ ፐርሰት ድል እንዲህ የሚርበተበተው አያስብልም ይኼ? ይገርማል እኮ!

ጉዟችን ተጀምሯል። “እኔ ምለው? አዲስ አበባን የመሬት መንቀጥቀጥ ያሰጋታል ሲባል የሰማሁ መስሎኝ ነበር፤”  ብሎ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ልጅ እግር ጀማውን አደናበረው። “እና ብትሰማስ? ከዚህ የበለጠ የመሬት መንቀጥቀጥ ታይቶ ተሰምቶ ያውቃል?” ባለቡኒ መነጽር ኮስታራ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰች። ተሳፋሪው ግራ ተጋብቶ እርስ በእርሱ ይተያይ ጀመር። “መቼ? ኧረ እኛ የሰማነው ቫይብሬሽን የለም፤” መባባል ሲጀምር ተሳፋሪውሸ “ቆይ አንተ እንዲህ ያለ ጥያቄ የምትጠይቀን ለነውጠኛ አንበገር ብንል በተፈጥሮ ነውጥ የተሳበበ ፀረ ልማታዊ ኃይል ናፍቆህ ነው?” አለው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠው ቀውላላ።

“ኧረ እንደዚያ አይደለም። እንዲያው ይኼ ሁሉ ግንባታና መልሶ የማልማት ሥራ ይኼን ተፈጥሮአዊ ክስተት ታሳቢ ባደረገ መልኩ . . . እ  . . .” ሳይጨርስ ባለመነጽሯ አቋርጣው፣ “ታሳቢ አደረገ አላደረገ። ትናንት ከእኔ አምስት አሥር ብር ሲፈልጥ የነበረ ሎፌ ነበር ለምሳሌ። ይታያችሁ አንድ ዓመት ብቻ ከዓይኔ ርቆ ነበር። ዛሬ ከቤቴ ስወጣ መርቸዲሱን እያሽከረከረ አየሁት። ሥራ ስለጀመረ ተቀየረ ብዬ ሰላም አልኩት። ግቢ ልሸኝሽ አለኝ። ገባሁ። ‘ያኔ ዝም ብለህ ዝርዝሬን ከምታባክን መንጃ ፈቃድ ላውጣ ክፈይልኝ ብትለኝ ኖሮ እኮ’ ምናምን ስል አቋርጦኝ ‘ተቀጥሬ አይደለም። መኪናው የእኔ ነው። አሁን እኮ ኢንቨርስተር ሆኛለሁ’ ብሎ ቀልቤን ገፈፈው። ከዚህ በላይ እንዴት ነው መሬት ልትንቀጠቀጥ የምትችለው? ሰው እንዴት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሦስት ሚሊዮን ብር አውቶሞቢል ይዘውራል?” ብላ ተንተከተከች። “ምስኪን! ሚሊዮን በረከሰበት ዘመን ሚሊዮን ብላችሁ ሰየማችሁን ብለው ስንት ሚሊዮኖች ከወላጆቻቸው እንደተኮራረፉ ምናለበት አንዳችሁ ብትነግሯት?” ያለው ተሳፋሪ ማን እንደሆነ አላየሁትም!

“የእኔ እህት እስኪ ተረጋጊና አጫውቺን። አሁን እንዲህ ያንገበገበሽ አንድ ዜጋ ከተመፅዋችነት ወጥቶ ምርታማ ዜጋ ስለሆነ ነው ወይስ ሽቅብ ማየቱን ትቶ ቅልቁል ስላየሽ ነው?” ብሎ ቀውላላው ቀጠለ። ይኼኔ ያቺ ሴት ዘላ ገብታ፣ “እዚያ ላይ ነው ብዬ ሽቅብ ሽቅብ ሳየው፣ ለካስ ፈጣሪዬ በቁልቁለቱም ነው’ ማለት ይኼኔ ነበር፤” ብላ ቀልባችንን አደናቀፈችው። ወጣቷ ለቀረበላት ደም የሚያፈላ ጥያቄ መነጽሯን አውልቃ፣ “እኔ ይኼው የግል ‘ቢዝነስ’ ከጀመርኩ አሥር ዓመቴ። ውለጅ ብትለኝ ግን አሥር ሺሕ ብር የለኝም፤” ሳትጨርስ፣ “አንቺ እሱን ትያለሽ ይኼው እኔ ሰላሳ ዓመት የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። ምንም እንኳ ከምሠራበት ሰዓት የምገመገምበት ሰዓት አይሏል ተብሎ ደመወዜ ባይቆረጥም የማወርሰው ቀርቶ የምቆናጠጥበት ቤት ንብረት የለኝም፤” ብሎ ታክሲዋን አዳረሳት።

“አሥር ሺሕ ብር ትላለች እንዴ? ከሦስት ሚሊዮን ብር መርቸዲስ የወረደ ሰው ቢያንስ ለአፉ እንኳ ደህና ቁጥር አይጠራም?” ሲባባሉ የምሰማቸው ደግሞ ፋሽን ፋሽኝ የሚሸቱ ጋቢና የተቀመጡ ቆንጂዬዎች ናቸው። “ለማንኛውም” አለ የታክሲዋን ወግ በቁጥጥሩ ሥር ያዋለው ቀውላላ። “ጊዜው የመደራጀት ነው። በነጠላ ደጀ ሰላም እንጂ ሚሊየነርነት አይሳምም፤” ከማለቱ፣ “እንዲያ! የፈራሁት ደረሰ። ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ሳትደራጁ ቅኔ እንዳትቀኙ እንዳትሉን እንጂ ሌላውስ አያሰጋንም፤” ባይዋ ነገር በግጥም ሲሰናኝ ነፍሷ የሚረካው ተሳፋሪ ናት። ይኼኔ ታዲያ ያ ከባለመነጽሯ አጠገብ ተቀምጦ ነገር ያስተኮሰው ልጅ እግር፣ “የሕዝብ አባል ከመሆን በላይ መደራጀት ምንድነው?” ብሎ ቢጠይቅ፣ “ግድየለም! አንተ በደህና ጊዜ በቁም ተኝተሃል። መሬት ሲንቀጠቀጥ እንቀሰቅስሃለን፤” ብሎ ጎልማሳው ጀማውን በሳቅ አሳደመበት። የአዳሚው ብዛት የአሳዳሚው ማነስ!

ጉዟችን ቀጥሏል። “ታክሲዬን የፖለቲካ መድረክ አደረጋችኋት፤” እያለ ወያላው ላፋችሁ ልጓም አብጁ ይል ይዟል። “አቦ ተወና! በነፃ አልተሳፈርን። ደግሞስ እንኳን የአንተ ታክሲ የእምነት ቤቱ መነገጃ፣ የሕዝብ ንብረትና እንባ መቀለጃ ሆኖ የለም እንዴ? ምን ታካብዳለህ?” ብላ ከቀውላላው አጠገብ የተቀመጠች ወይዘሮ ጮኸችበት። “እህ እና የተከፈለበት ሁሉ ይፈነጭበታል እንዴ?” ወያላው አንገቱን ደፍቶ አጉተመተመ። “እንኳን የከፈልክበት ስማ ልንገርህ በእምነት የተሾምክበት አገልግሎትም ላይ ትጨፍራለህ። ምሳሌ አልጠቅስም፤” ብላ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችንን አስከበረች። “አፈር ልብላልሽ! እንዳንቺ ዓይነቱ ሁለት ሦስት ቢሆን ምን ነበረበት? አልናገር ብለን እኮ ነው ደጃዝማችነቱ የሚቀርብን፤” አለ ጎልማሳው። “ካልክስ የቀረብን መቀራመቱና ማከማቸቱ ነው፤” ብላ ከፊል ፈገግ ስትል፣ “እኮ ምን አልል ብለን?”  ጎልማሳው አፋጠጣት።

“ህሊናን ፈርተን!” በአጭሩ መለሰች ወይዘሮዋ። “እኔ ምለው ይኼ ህሊና የሚባል ነገር አዘውትሮ ጠመንጃ አንግቶ አየዋለሁ ልበል?” ቢል ያ ልጅ እግር ከባለመነጽሯ በስተቀኝ የተቀመጡ አዛውንት፣ “ሊያስበላን ነው እንዴ ዛሬ ይኼ ልጅ?” ብለው በአራዶቹ አገላለጽ ፈገግ አሉ። ወዲያው ጋቢና የተቀመጡት ቆንጂዬዎች (ለካስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኖረዋል) ስልክ ስፒከር ላይ አድርገው ተራ በተራ ደንበኛቸውን ያናግራሉ። “ኧረ ተወደደ፤” ትላለች አንደኛዋ። “ካልፈለግክ ተወው። ሌላ የመመረቂያ ጽሑፍ የሚያዘጋጅ ሰው እኮ አላጣንም፤”  ሌላኛዋ። “በቃ እሺ አምስት ሺሕ ብር ላድርግላችሁ፤” ይላል ተደራዳሪው። “ምን? አምስት ሺሕ ብር ላጥ አርጌ ማውጣት ብችል ዩኒቨርሲቲ ምን እሠራለሁ? ደፋር…” ብላ አንዷ ስልኩን ዘጋችው። ተሳፋሪው ተስፋ በቆረጠ መንፈስ ራሱን ሲነቀንቅ ነገ የማይነጋ ይመስል ነበር!

ወደ መጨረሻችን ነን። አዛውንቱ የተሳፋሪውን ቅስም መሰበር አስተውለው “አይዟችሁ። እንዴ! ይህቺ ቀላሏ ናት። ያዕቆብ የነገዶች ሁሉ አባት ሳይቀር አጭበርብሮ ተመርቋል። ባይሳካለትም ቅሉ የኋላ ኋላ በንስሐ ፍሬ ለማፍራት በቃ። እነዚህም ልጆች ነገ ከተፀፀቱ ፍሬ ከማፍራት ምን ያግዳቸዋል?” ብለው በአርምሞ ተሳፋሪውን ሲቃኙ ሳሉ፣ “ምን ነካዎት አባት? እነዚህ ልጆች እኮ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ አይደለም ምርቃታቸውን አጭበርብረው የሚያገኙት። አገር፣ መንግሥት፣ ዓለም ነገ በዕውቀትና በጥበብ በታገዘ ሙያ ፍሬ አፍርተው ለማየት የሚጠብቃቸው ዜጎች ናቸው። ነገ በፀፀት ያበላሹት ሥራ በላቦራቶሪ ምርምር ምናልባትም በመልሶ ማልማት ዕቅድ ላይስተካከል ይችላል። ነገ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በቤተሰብ፣ መንግሥት አስተዳደር እርከን ላይ ተመድበው ሲሠሩ ከትውልድ ትውልድ ዋጋ የሚያስከፍል ቀውስ ቢፈጠር እርስዎ እንደሚያስቡት በንስሐ ብቻ የሚስተካከል ይመስልዎታል?” ብሎ መልስ ሲጠብቅ ጎልማሳው ሾፌራችን ዘሎ ሠርገኛ አውቶሞቢሎች ሠልፍ መሀል ገብቶ ጥሩንባውን ያስጮኸው ጀመር።

“እንዴ?ሰ እንዴ?” ሳንጠራ ትላለች ሻሽ ጠምጣሚዋ። “ዋናው አገባቡን ማወቅ ነው። ‘የተጠሩት ብዙዎች ናቸው የገባቸው ግን ጥቂቶች ናቸው’ የሚል ጥቅስ እኮ ለጥፌያለሁ እዚህ ጋ፤” ሾፌሩ ያለምጣል። “ቢያንስ የክታችንን እንድንለብስ አታስጠነቅቀንም ታዲያ?” አዛውንቱ ከጎልማሳው ማፈናፈኛ የለሽ ጥያቄ ለመሸሽ ይመስላል ያስቀይሳሉ። “ሠርግ እኮ ነው፣ መርዶ ነው እንዴ?” ወያላው ጣልቃ ይገባል። “አገር የተዳረች አስመሰላችሁትሳ?” ሲል ደግሞ ጎልማሳው ቀውላላው ቀበል አድርጎ፣ “ከዚህ በላይ እንዴት ትዳር ወዳጄ። እኛ ነን እንጂ የደስታና የሐዘን ሲቃችን የተቀላቀለብን፤” አለው። “አቤት?!” ሲል ጎልማሳው ለነገር ቸኩሎ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። ከመቅጽበት ቀውላላው ዘሎ ወርዶ ወደ ጎልማሳው ዞረና “ወግ ነው ሲያለሙ ማልቀስ፤” ብሎ በሩጫ ተፈተለከ። ያኛው ደግሞ፣ ‹‹አቤት! አቤት! ቱሪናፋ ሁሉ በልብ ነው እንጂ በአፍ አይለፈልፉም…›› እያለ ሲያንባርቅ ወደ ቀጣዩ ጉዳያችን ዘለቅን፡፡ መልካም ጉዞ!          

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት