Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕግ የሚሻው የተሽከርካሪዎች መድን ሽፋንና የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ክፍተቶች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ባለሙያዎች ማኅበር ከተቋቋሙ 10ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተበትን 10 ዓመት ባለፈው ቅዳሜ አክብሯል፡፡ ሁሉምን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና 23 ብሮከሮችና ኤጀንቶችን በአባልነት ይዟል፡፡ የኢንሹራንስ ባለሙያዎችና የኢንሹራንስ ኩባንያ መሪዎችም የዚሁ ማኅበር አባላት ናቸው፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ዓላማዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ፣ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠትና ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚለው ይጠቀሳል፡፡

ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ባለፉት አሥር ዓመታት ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ያግዛሉ የተባሉ ከ35 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይት አቅርቧል፡፡ መንግሥት ትኩረት ይሰጥባቸው ያላቸውን ጉዳዮች በመምረጥም ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት አቅርቧል፡፡   

በአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ያስገኛል ያሉትን ሐሳብ ለፖሊሲ አውጪዎች በማቅረብ ኢንዱስትሪው ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲጓዝ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የማኅበሩ መሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት በበላይነት ለሚቆጣጠረው ለብሔራዊ ባንክ ብዙዎቹ ጥናቶች በግብዓትነት ጠቅመዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በሪስክ ማኔጅመንት፣ በሕይወት ኢንሹራንስና በሌሎች የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ዙሪያ የቀረቡት ጥናቶች ለአብነት ያህል ተጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ ግን ማኅበሩም ሆነ የማኅበሩ አባላት በእጅጉ የሚሞግቱት፤ በተለያዩ መድረኮች ላይም ውይይት የተደረገበትና በአገሪቱ የኢንሹራንስ ሕግ ውስጥ መካተት አለበት ብለው የሚያምኑበት የሞተር (የተሽከርካሪ) ኢንሹራንስን የሚመለከተው የመፍትሔ ሐሳባቸው ግን አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አክሳሪ ከሚባሉ የመድን ሽፋኖች ውስጥ በቀዳሚነት የሚቀመጠው የሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ ራሱን የቻለ ሕግ ሊወጣለት ይገባል የሚሉት ደግሞ የአርቦን መጠኑን የሚመለከት ነው፡፡

በማኅበሩ በኩል ከዚህ ቀደም የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍም ሆነ ያነጋገርናቸው የማኅሩ አባላት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ ሊያወጣለት ይገባል ብለው የሚሞግቱት የሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን አነስተኛ ፕሪሚየም (ዋጋ) ተተምኖለት በሕግ መቀመጥ አለበት የሚል ነው፡፡

የማኅበሩ ሪሰርችና ፐፕሊኬሽን ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ እንደሚሉት፣ የሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ ዝቅተኛ የፕሪሚየም ዋጋ ሊተመንለት የሚገባ፤ ነገር ግን በሕግ ያልተተመነለት በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ውድድር ጤናማ እንዳይሆን አድርጐታል፡፡ ከሌሎች የኢንሹራንስ ሽፋን ከሚሰጥባቸው አገልግሎቶች ሁሉ በአክሳሪነቱ የሚጠቀስ በመሆኑ ዘርፉ ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገር ዝቅተኛ የዋጋ ተመን ሊቀመጥለት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሞተር ኢንሹራንስ ዝቅተኛ ዋጋ ተመን በሕግ ይቀመጥ የሚለው እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ግን እስካሁን ምላሽ አላገኘም፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መምጣቱን የሚጠቁሙት የኢንሹራንስ ባለሙያዎች፣ ለሞተር ኢንሹራንስ የሚሰጠው ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱም አሳሳቢ ሆኗል ይላሉ፡፡  

አክሳሪነቱም እየታወቀ ቢሆን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እጅግ የወደቀ ዋጋ እየሰጡ መሄድ ለኢንዱስትሪው ዕድገት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳሳደረም ያምናሉ፡፡

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ አረቦን የሚሰበሰብበት ይህ ዘርፍ አክሳሪ ሆኖ ከቀጠለ ደግሞ ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ደረጃ እንዳያድግ ያደርገዋል የሚለውን አመለካከት ብዙዎች ይጋሩታል፡፡

በ2007 በጀት ዓመት የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከጠቅላላ ከከፈሉት የጉዳት ካሳ ውስጥ ለሞተር ኢንሹራንስ ብቻ የከፈሉት ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነውን መሆኑ ችግሩ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል፡፡

የአልትሜት ኢንሹራንስ ፕሮከርስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ምግባርም፣ የሞተር ኢንሹራንስ ዝቅተኛ የዋጋ ወለል ሊኖረው ይገባል ከሚሉት የኢንሹራንስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ለሞተር ኢንሹራንስ ዝቅተኛ ዋጋ በማስቀመጥ መሥራት በበርካታ አገሮች የተለመደ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ በዘርፉ ያለውን ችግር ተገንዝበው እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ሳይቀሩ ለሞተር ኢንሹራንስ ዝቅተኛ ዋጋ ተመን አውጥተው ኩባንያዎች ይህንን ዋጋ መነሻ አድርገው እየሠሩበት መሆኑ ውጤት እያስገኘላቸው ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ይህንን ችግር መገንዘብ አለበት የሚሉት የኢንሹራንስ ባለሙያዎች፣ ይህ ሕግ ቢወጣ ኢንዱስትሪው በተሻለ ያድጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻም ሕጉ ተቀርጾ ሥራ ላይ ቢውል በሞተር ኢንሹራንስ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይታያሉ የተባሉ ችግሮችንም ያስወግዳል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በሞተር ኢንሹራንስ ጥሩ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም፡፡ አገልግሎቱ በጥሩ ሁኔታ ሊሰጥ ያልቻለበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ለሞተር ኢንሹራንስ ሽፋን በቂ የሆነ የአረቦን መጠን ስለማይሰበሰብ ነው፡፡

የሞተር ኢንሹራንስ እያተረፈ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የሚሰበሰበውን አረቦን እየወሰደ ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ዕድገት እንቅፋት እየሆነ ጭምር ነውም ብለዋል፡፡ የሞተር ኢንሹራንስ ተገቢው ዋጋ ተሰጥቶት ቢሠራበት ግን ደንበኞችም ጥሩ አገልግሎት ሊያገኙበት ይችሉ እንደነበር በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡

አነስተኛ የአረቦን መጠን ማስቀመጡ በቀላሉ ሊተገበር የሚችል ነውም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ባንኮች አነስተኛ የወለድ ክፍያ ተብሎ እንደተቀመጠላቸው ሁሉ ለሞተር ኢንሹራንስም ዝቅተኛ የአረቦን መጠን በማስቀመጥ ኢንዱስትሪውን መታደግ ይቻላልም ተብሏል፡፡

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በሌሎች ችግሮች የታጠረ ስለመሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ማኅበር 10ኛ ክብረ በዓል ላይ የቀረበው አንድ ጥናታዊ ጽሑፍም ይህንኑ የሚያሳይ ሆኗል፡፡

የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በመቃኘት በዕለቱ የጥናት ወረቀታቸውን ያቀረቡት የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ጥበቡ ጥላሁን፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ይታይበታል ያሉትን 13 የሚሆኑ ዋና ዋና ችግሮች በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

እንደ ኢንሹራንስ ባለሙያው ጥናታዊ ጽሑፍ ከሆነ ለኢንዱስትሪው ቀዳሚ ችግር ናቸው ብለው ካስቀመጡዋቸው መካከል የኩባንያዎች የሥራ መሪዎች ብቃት አነስተኛ መሆን አንዱ ነው፡፡ በዘርፉ ዙሪያ ያደረጉት ጥናትም ይህንኑ የሚያሳይና የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ባነጋገሩበት ወቅት የአመራር ብቃት ክፍተት እንዳለባቸው መገንዘባቸውን ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ትልልቅ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፡፡ የኩባንያ መሪዎች በዚህ ዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ባለሙያው፣ የሥራ መሪዎች ኢንዱስትሪውን ሊቀይር የሚችል አቅም ከሌላቸው ኢንዱስትሪው ሊያድግ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በብዙ መለኪያዎች ሲታይ ወደኋላ የቀረ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፣ የኢንሹራንስ ኩባንያ መሪዎችና የቦርድ አመራሮች ራሳቸውን መቀየር እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡

በእርሳቸው ግንዛቤ በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ስለኢንሹራንስ ጥልቅ ዕውቀት አላቸው እንደማይባልና በኢንሹራንስ ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥተው ሥልጠና የሚሰጡ ተቋማት ያለመኖራቸውም ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ተቋም መፈጠር እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኢንሹራንስ ዕውቀት ላይ ክፍተት እንዳለና ይህም መሻሻል ካላሳየ ዘርፉን ማሳደግ እንደማይቻል ያምናሉ፡፡

ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር ሲቀመጥ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ደካማ ነው ያሉት ጉዳይ ደግሞ የደንበኞች አያያዝን የሚመለከት ነው፡፡ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ኋላቀር በመሆኑም በርካታ ደንበኞች ወደ ኢንሹራንሰ ኩባንያዎቹ እንዳይመጡ አድርጓል፡፡ እንደ ጉድለት ከጠቀሱዋቸው ውስጥ ካሳ ክፍያ በፍጥነት ያለመክፈል አንዱ ነው፡፡ ካሳ ክፍያ ብቻ ሳይሆን አንደር ራይቲንግ ላይ ሳይቀር ዘግይተው ምላሽ የሚሰጡ መሆኑ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጣቸው ደካማ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ይህም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደንበኞች እንዲጨምር አያያዙ ማማር አለበትና ኩባንያዎች የአገልግሎት ቻርተር ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ኩባንያዎች ደንበኞቻቸውን በአግባቡ ለመያዝ ውላቸው በጊዜ ገደብ የተቀመጠ መሆን እንዳለበትና ጉዳያችሁ በዚህ ቀን ያልቅላቸዋል ማለት እንደሚኖርባቸው ገልጸው፣ ይህንን የሚያደርጉትን ግን ጥቂት ኩባንያዎች ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰቡ የሚስማሙ የተለያዩ ይዘት ያላቸው አገልግሎቶች ወይም የኢንሹራንስ ሽፋኖች ያለመኖራቸው የኢንዱስትሪው ሌላው ችግር ነው ተብሏል፡፡ በትብብር የመሥራት ባህልና ለመኖሩም እንደ ችግር የሚታይ ነው ያሉት ባለሙያው፣ በጋራ ስለኢንዱስትሪው ማስተማር ያለመቻላቸው ለኢንዱስትሪው ዕድገት አንድ ማነቆ ነው ይላሉ፡፡ የኢንሹራንስ አስፈላጊነት በጋራ ግንዛቤ መስጠት ካልተቻለም ዘርፉን ማሳደግ እንደማይቻልም አሳስበዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክም ቢሆን በሥነ ምግባር ደንብ ላይ ጥብቅ መመርያዎች ሊኖሩት እንደሚገባ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የኤጀንቶችና ፕሮከሮች ሥነ ምግባር ደንብ ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሚተቹበት ጉዳዮች አንዱ በቴክኖሎጂ የዳበሩ አለመሆናቸው ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባህሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከባንክ ጋር ሲነጻጸሩ በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ኋላቀር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ድረ ገጽ የሌላቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ኢንሹራንስን ጨምሮ አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ተከልክሎ መቆየቱም እንደ አንድ ችግር የሚታይ ነው ተብሏል፡፡ የኢንሹራንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያ መከልከሉ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከሌሎች መማር እንዳይችሉ ገድቧል የሚል አስተያየት በጥናት ወረቀቱ ላይ ሰጥተዋል፡፡    

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ 16 የግልና አንድ የመንግሥት የኢንሹራን ኩባንያዎች እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ባለፈው ዓመት ከጠቅላላ የኢንሹራንስ ሽፋን 5.6 ቢሊዮን ብር አረቦን ሲሰበስቡ፣ 2.4 ቢሊዮን ብር ለጉዳት ካሳ ከፍለዋል፡፡  

 

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች