Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሼክ አል አሙዲና ተባባሪያቸው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የውኃ ጉድጓዶች ሊያስቆፍሩ ነው

ሼክ አል አሙዲና ተባባሪያቸው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የውኃ ጉድጓዶች ሊያስቆፍሩ ነው

ቀን:

–  ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ዕርዳታ እንዲያቀርብ እየተወተወተ ነው

በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ ሁለት ባለሀብቶች በአፋር ክልል አምስት ትልልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ሊያስቆፍሩ ነው፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ዓሊ አል አሙዲ ከለንደን ካፌ ባለቤት አቶ ኑር ሁሴን በጋራ በመሆን፣ በክልሉ የሚያከናውኑት የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከ1977 ዓ.ም. ድርቅ ወቅት በጣም የከፋ ነው የተባለው የአሁኑ ድርቅ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ያስከተለ በመሆኑ፣ ዘላቂ የሚሆነው መፍትሔ ትልልቅ የውኃ ጉድጓዶችን መቆፈር ነው ተብሏል፡፡ ባለሀብቶቹም እገዛቸውን በዚህ መንገድ ለማከናወን እንደወሰኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

እንደ ምንጮች ገለጻ ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉድጓዶቹን እንዲቆፍር ስምምነት የፈጸመው የኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ የባለሀብቶቹ ተወካዮች፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ሥራው ይጀመራል፡፡ የጉድጓዶቹ ቁፋሮ ወጪ ምን ያህል እንደሚሆን ከመግለጽ የተቆጠቡት ምንጮች፣ የቁፋሮው አጠቃላይ ወጪ ሥራው በሚጀመርበት ዕለት ይገለጻል ብለዋል፡፡

የአፋር ክልል ነዋሪዎች በአመዛኙ አርብቶ አደሮች በመሆናቸው የጉድጓድ ውኃ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሎ ታምኗል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ፣ ባለሀብቶቹ ከዚህ በኋላም ተጨማሪ ጉድጓዶችን በክልሉ ይቆፍራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉድጓዶቹ የሚቆፈሩባቸው ቦታዎች የተመረጡት በክልሉ መንግሥት መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የአሁኑ ድርቅ በመላ አገሪቱ ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለአስቸኳይ ዕርዳታ የዳረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም የኅብረተሰቡ ዋነኛ ችግር ውኃ እጥረት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ከጊዜያዊ ዕርዳታ ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኙ የሚችሉ የጉድጓድ ውኃዎችን መቆፈር አንዱ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሰኞ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫው፣ በአሁኑ ወቅት በእጅ ላይ ያለው የምግብ ዕርዳታ ለተረጂዎች በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ድጋፎች በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጉ አስታውቋል፡፡

ዕርዳታው በአፋጣኝ የማይገኝ ከሆነ በሚያዝያ ወር ምንም ዓይነት የምግብ ዕርዳታ ማቅረብ እንደማይቻልም ገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 በአጠቃላይ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እስከ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከ30 በመቶ በላይ ዕርዳታ እንዳልተገኘ ጠቁሟል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአስቸኳይ ዕርዳታ ማቅረብ እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ሴቭ ዘ ችልድረን በበኩሉ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ባቀረበው ጥሪ፣ በመጪው ነሐሴ 2008 ዓ.ም. ከፍተኛ ድርቅ በተከሰተባቸው ሥፍራዎች 350 ሺሕ ሕፃናት እንደሚወለዱ ስለሚጠበቅ፣ የአፍሪካ መሪዎች ለዚህ ችግር ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይህንን ያህል ሕፃናት እየተወለዱና ከፍተኛ የምግብ እጥረት እያለ፣ በተጨማሪም ለአጥቢ እናቶች በጣም ጠቃሚ የሆኑ እንስሳት በብዛት እየሞቱ በመሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ ማድረጉን፣ የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ጆን ግረሃም ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ ዓይነቱ እጅግ በጣም አፋጣኝ ትኩረት በሚያስፈልገው አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጣም አናሳ ምላሽ አይቼ አላውቅም፤›› ሲሉ ሚስተር ግረሃም ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ባሳለፍኩዋቸው 19 ዓመታት እንዲህ ዓይነት ድርቅ ገጥሞኝ አያውቅም፤›› ብለው፣ በዚህ አስከፊ ድርቅ ምክንያት 2.5 ሚሊዮን ሕፃናት ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ እንደሚችሉም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለውን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መረባረብ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...