በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ለመስኖ ልማትና ለበልግ እርሻ የሚያስፈልግ የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ ማስገባት አለመቻሉን፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት፡፡
ከ2007/2008 የምርት ዘመን በትርፍነት ከቀረ 398,268 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በተጨማሪ፣ ከውጭ ተገዝቶ መቅረብ ያለበት 833,663 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሆነ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ከውጭ ተገዝቶ ለሚገባው ማዳበሪያ 559.2 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡
ከተጠቀሰው መጠን ውስጥ 832,400 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለመስኖና ለበልግ እርሻ ቢያንስ በኅዳር ወር መጀመሪያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የግዥ ውል ቢፈጸምም፣ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡
‹‹እስካሁን 200,000 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ተጓጉዞ አገር ውስጥ መግባት ሲገባው 19.315 ሜትሪክ ቶን ብቻ አገር ውስጥ ገብቷል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ወራት ይህንን ለማካካስ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር የተጠናከረ ክትትል ማድረግ የሚጠይቅ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ለማግኘት ምን ያህል ጥረት እንደተደረገ የፓርላማው አባላት ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድራድ ማንደፍሮ፣ ‹‹እንደ ዘንድሮ የውጭ ምንዛሪ ችግር አጋጥሞን አያውቅም፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ጥረት መደረጉን፣ ከብሔራዊ ባንክም ሆነ ከሌሎች ባንኮች የውጭ ምንዛሪውን ማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁንም የውጭ ምንዛሪው የባንክ መተማመኛ ሰነድ የተከፈተው በተለየ መንገድ ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ወንድራድ፣ የተለየ የተባለው መንገድ ምን እንደሆነ ግን አልገለጹም፡፡
በሌላ በኩል በድርቁ ምክንያት የተፈጠረውን የምርት እጥረት በተመለከተ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በግልጽ አላስቀመጡም፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያደረጉት ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና ከክልሎች ጋር በመሆን በመስክ ላይ ግምገማ መደረጉን ነው፡፡ በዚህም ድርቁ በተጠናከረባቸው አካባቢዎች በሰብል ልማት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደረና የምርት ቅነሳ ያስከተለ መሆኑን፣ በአንፃሩ ደግሞ የዝናብ እጥረት ባልታየባቸው አካባቢዎችና ከፍተኛ ሰብል አምራች በሆኑ አካባቢዎች የተሻለ ምርት እንደሚገኝ መታወቁን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ አጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረው የምርት መጠን የሚታወቀው ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በሚያወጣው መረጃ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡