Friday, June 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም በፍጥነት ይጠናከር!

ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ በሰው ላይ የሚደርሱ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋዎችን ለመቀነስም ሆነ ለማስቀረት፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ ድንገተኛ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ማለትም የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የሰደድ እሳት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የወረርሽኝ በሽታዎችና የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ ቀድሞ መዘጋጀትና መከላከል ካልተቻለ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውሶች ያጋጥማሉ፡፡ የመከላከልና የዝግጁነት አቅም ሲጠናከር የአደጋዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ዕቅዶችን ለመንደፍ ያስችላል፡፡ ይህንን ለማድረግ አለመቻል ደግሞ ለሰው ልጆች ሞት፣ አካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመትና ለሞራል ልሽቀት ይዳርጋል፡፡ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡

ሰሞኑን በደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማ ሐዋሳ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተከስቷል፡፡ የርዕደ መሬቱ መጠን ዝቅተኛ ሆኖ በሕይወት ላይ የደረሰ አደጋ ባይኖርም፣ በከተማው ነዋሪዎች ላይ ግን ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡ የአገሪቱ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅምን ለጊዜው መፈተን ባይችልም፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱን ደካማነት ግን አሳይቷል፡፡ ሐዋሳ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኝና ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነቷ የታወቀ በመሆኑ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ጠንካራ ቢሆን ኖሮ በየጊዜው ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ሕንፃዎች ይህንን ችግር ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ይደረግ ነበር፡፡ ይህ መጠነኛ ማሳያ ለወደፊቱ ትምህርት ሊቀሰምበት ይገባል፡፡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነትን አስፈላጊነት ማሳያም መሆን አለበት፡፡

በአገሪቱ በግዙፍነቱ ይታወቅ የነበረው የቀድሞው የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ)፣ በኋላም የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን (አመዝኮ) በድርቅ ጊዜም ሆነ በተለያዩ አደጋዎች ወቅት ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው ተቋም ነበር፡፡ ይህ ተቋም ትልልቅ የምግብ እህል መጋዘኖች፣ ጋራዦች፣ ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ አውሮፕላኖች፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል፣ ወዘተ የነበሩት ለአገር የሚጠቅም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንዲታጠፍ ተደርጎ በግብርና ሚኒስቴር ሥር አንድ ዲፓርትመንት ሆኗል፡፡ ተግባሩም ተለውጦ አስተዳደራዊ ሥራዎች ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ይህ ተቋም ይበልጥ ተጠናክሮ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም አጎልብቶ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱን አዘምኖ ቢቀጥል፣ በማንኛውም ጊዜ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመመከት ያስችል ነበር፡፡

ከወር በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ ብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ፀድቆ፣ ኮሚሽኑን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ ‹ከመቅረት መዘግየት› በሚለው ምሳሌ ዕርምጃው ድጋፍ የሚቸረው ቢሆንም፣ አሁንም ኮሚሽኑን በማደራጀት ረገድ ፍጥነትና ምርጥ ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ተሞክሮዎች መቀሰም አለባቸው፡፡ ይህ ኮሚሽን በተለይ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች በመታገዝ በሰው ኃይል፣ በበጀት፣ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶች ሊደራጅ ይገባዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ አጣዳፊ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም መጠናከር ከሚያስፈልግባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ በዓለማችን የተለያዩ ሥፍራዎች የሚከሰቱ አደጋዎች እዚህም ሊደርሱ ይችላሉ የሚለው እሳቤ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአንድ አገር ሰላምና ፀጥታዋ ሲደፈርስ፣ የሽብር ጥቃቶች ሲያጋጥሙ፣ የፋብሪካ ፍንዳታዎች ሲከሰቱ፣ በማሳዎችና በደኖች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ቃጠሎ ሲደርስ፣ እንዳሁኑ የከፋ ድርቅ ሲያጋጥም፣ የአውሎ ንፋስ አደጋ ሲከሰት፣ መሬት ሲንቀጠቀጥ፣ ወዘተ በየፈርጁ የሚደርሱትን አደጋዎች ቀድሞ መከላከል መቻል ያስፈልጋል፡፡ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ መሠረት ዝግጅት ማድረግም እንዲሁ፡፡ በዚህ መሠረት የተደራጀ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን አገርን ካልታሰበ ጥፋት ይከላከላል፡፡ የሕዝብ ሕይወትን፣ አካልን፣ ንብረትንና ሥነ ልቦናን ይታደጋል፡፡

ሁሌም ለአደጋዎች ዝግጁ ለመሆን፣ ለጤናና ተያያዥ ችግሮች ለመሰናዳት፣ አደጋዎች የሚያስከትሉዋቸውን የረጂም ጊዜ ሰቆቃዎች ለማስቀረትና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ የሕዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ በአደጋ ጊዜ በሚፈጠሩ ትርምሶች የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለመቀነስ፣ በግርግር የሚወድሙ ንብረቶችን ለማትረፍ፣ ወዘተ ከፍተኛ የሆኑ ልምምዶችና ሥልጠናዎች የሚቀረፁት በአግባቡ ማቀድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሲኖር ንድፈ ሐሳብንና ተግባርን በማቀናጀት እጅግ በጣም አስፈሪ፣ አውዳሚና ለሕዝብ ሕይወት ጠንቅ የሆኑ ጉዳቶችን በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል ይቻላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊ ሆኗል፡፡ ይህንን ያህል መጠን ያለው ሕዝብ ለመመገብ፣ ከቀዬው እንዳይፈናቀል፣ የሞት ጉዳት እንዳይደርስና ለመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በሚፈለገው መጠን ዕርዳታ እየሰጠ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ከመንግሥት ካዝና እየወጣ ባለ ገንዘብ እስካሁን ጥረት ቢደረግም፣ የረድኤት ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ርብርብ ካልተደረገ ችግሩ አሥጊ ነው በማለት ላይ ናቸው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አይታው የማታውቀው ለረጂም ወራት የዘለቀው የዝናብ መጥፋት ያስከተለው ድርቅ፣ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሲባል በመቋቋም ላይ ያለው ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ ሊከሰት ይችላል የሚባለውን የአደጋ መጠን መቀነስ ይኖርበታል፡፡

ይህንን ዓይነት አስፈሪ ድርቅ ባለበት በዚህ ወቅት ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ቢያጋጥሙ ሰብዓዊ ኪሳራው ከሚገመተው በላይ ይሆናል፡፡ በድርቅ ወቅት ወረርሽኞች ይከሰታሉ፡፡ ሕፃናት አልሚ ምግብ በበቂ መጠን ስለማያገኙ የሰውነታቸው የመከላከል አቅም ይዳከማል፡፡ ጤነኛ የነበሩ ሰዎች የጤና መታወክ ይገጥማቸዋል፡፡ እርጉዞችና አጥቢዎች በቀላሉ ለበሽታዎች ይጋለጣሉ፡፡ ከብቶች መኖና ውኃ ስለማያገኙ ለዕልቂት ይዳረጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለች አገር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅሟ ደካማ ከሆነ መተኪያ የሌለው የሰው ሕይወት ከሞት ጋር ይፋጠጣል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው አቅምን አጠናክሮ ችግሮችን ለመቋቋም ጊዜ መስጠት የማያስፈልገው፡፡

በሐዋሳ ከተማ ያጋጠመው ዓይነት የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምንጊዜም ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ድንገተኛ በመሆናቸውም ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራቸው ከባድ ነው፡፡ ችግሮቹን በፅናት መመከት የሚቻለው ግን ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ዘመናዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ተቋም በመገንባትና በማጠናከር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡ በሚገባ የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ዳጎስ ያለ በጀትና ቴክኖሎጂ በመመደብ ከቅድመ ማስጠንቀቂያ እስከ ዝግጁነትና መከላከል ድረስ መጠናከር የግድ ይላል፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋርም ቅንጅት በመፍጠር ድጋፍ ማግኘትና ልምድ መቅሰም ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ለአገር አስፈላጊ የሆነ አንገብጋቢ ጉዳይ ተግባራዊ ባለማድረግ ብቻ ችግር ቢፈጠር ፀፀቱ የአገር ነው፡፡ ስለዚህም የአገሪቱ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አቅም በፍጥነት ይጠናከር!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የዘሪሁን አስፋው ስሙር ምርምሮች

‹‹…በአንድ ጥራዝ ታትመው እንዲወጡ ያደረግሁት ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ስለደራሲዎችና...

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...