Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድርቁ ምንክያት ግድቦች ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው የ500 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት...

በድርቁ ምንክያት ግድቦች ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው የ500 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ተፈጠረ

ቀን:

– ጊቤ ሦስት በሁለት ሳምንት ውስጥ እንዲጀምር ታዘዘ

በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው፣ የ500 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት አጋጠመ፡፡

በአሁኑ ወቅት 460 ሜጋ ዋት ከሚያመነጨው ጣና በለስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በስተቀር፣ በአገሪቱ የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚያመነጩት ኃይል አገልግሎት ዝቅተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ ውኃ ካጠራቸው ግድቦች መካከል ተከዜ፣ ቆቃ፣ ፊንጫ አመርቲነሽና ጊቤ አንድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በመላው አገሪቱ ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ከመከሰቱም በላይ፣ ፋብሪካዎች በቀን ለስድስት ሰዓታት ብቻ ኤሌክትሪክ እያገኙ መሆኑን ሪፖርተር ከተለያዩ የፋብሪካ ሥራ አስኪያጆች ያሰባሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ ችግር ምክንያት ኅብረተሰቡና የንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ ሲሆን፣ ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙ አካላት ባገኙት አጋጣሚ መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ እየጠየቁ ይገኛል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመርያ በፋይናንስ ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የኤሌክትሪክ ቦርድ ተሰብስቦ የጊቤ ሦስት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ላይ ያሉ ማነቆዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ጣቢያው የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ኃይል ቋት እንዲገባ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ግንባታው 99 በመቶ የተጠናቀቀው ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት እያንዳንዳቸው 187 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ማመንጨት ከሚችሉ አሥር ተርባይኖች ውስጥ አራት ያህሉ ማመንጨት እንደሚችሉ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ ኃይል ማሰራጫ መስመር ለማስገባት ማነቆ መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሚመነጨው ኃይል ወደኋላ ተመልሶ ጥፋት እንዳያደርስ የሚያደርጉ መሣሪያዎች ተከላ ዘግይቶ በመስከረም 2008 ዓ.ም. በመጀመሩ፣ ኢኮኖሚውን ሊረዳ የሚችለው ጊቤ ሦስት በሚፈለገው መጠን አገልግሎት መስጠት ሳይችል እንደቀረም ተመልክቷል፡፡  

የኤሌክትሪክ ቦርድ በሰጠው መመርያ አስፈላጊ የተባሉ ሥራዎችና መሣሪያዎች ሳይቀሩ ከሌሎች ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በውሰት ወደ ጊቤ ሦስት እንደሚሄዱም ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ሥራዎች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ግልገል ጊቤ ሦስት ወደ ብሔራዊ መስመር እንዲገባ ቦርዱ ትዕዛዝ ማስተላለፉም ተጠቁሟል፡፡

በደቡብ ክልል 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዳውሮና ወላይታ ዞኖች መካከል የተገነባው ጊቤ ሦስት 1.5 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ግንባታውን በዋናነት የጣሊያኑ ሳሊኒና የቻይናው ዳንግፋንግ ያከናወኑት ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተገነቡ ግዙፍ ግድቦች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

ከኃይል ማመንጫ ጣቢያው በተጨማሪ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ባለ400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና በወላይታ ሶዶና በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ተገንብቷል፡፡

በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ አልፎ በአብዛኛው የተጠናቀቀው ጊቤ ሦስት 1,870 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ2,000 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እያመነጨች ትገኛለች፡፡ ይሁንና የማመንጨት አቅሟ ከ10,000 ሜጋ ዋት በላይ ነው፡፡ ነገር ግን በድርቁና በተለያዩ ችግሮች ያቀደችውን ያህል መጠን ማምረት ላልቻለችው ኢትዮጵያ፣ የጊቤ ሦስት ፕሮጀክት ሥራ መጀመር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡

ጊቤ ሦስት የተገነባው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከሚመዘገብባቸው ደቡብ ምዕራብ ከፍተኛ ቦታዎች በሚፈሱት ጊቤና ጎጀብ ወንዞች ላይ ነው፡፡ የወንዞቹ የፍሰት መጠን የተሻለ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የጊቤ ሦስት ግድብ ከስድስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውኃ መያዙ ታውቋል፡፡ ጣቢያው ካሉት ተርባይኖች አራቱ በተጠቀሰው ጊዜ መሥራት ቢጀምሩ 748 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኝ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጊቤ ሦስት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እየተነገረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙንት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...