የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ባንኮች እንዲወያዩበት የውጭ ምንዛሪ ንግድ ላይ ግልጽነትን ለማስፈን የሚያስችል መመርያ ረቂቅ አወጣ፡፡
ረቂቅ መመርያው በዋናነት በውጭ የምንዛሪ ንግድ ዙሪያ ለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በር ይከፍታሉ ያላቸውን የንግድ ሥርዓቶችን መልክ ለማስያዝ የተዘጋጀ ስለመሆኑ በስፋት ያትታል፡፡ የባንክ የሥራ አመራር ቦርድ፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላትና የውስጣዊ ኦዲት አካላቱ የቁጥጥር ሥርዓታቸውን የሚያጠብቁበትን መንገድ ያስቀምጣል፡፡
መመርያው የሥራ አመራር ቦርዱ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ንግድ እንቅስቃሴን የሚያስተዳድር መመርያ እንዲያዘጋጅና ሥራ ላይ እንዲያውል የሚያዝ ሲሆን፣ ይህ መመርያ በጥብቅ እየተተገበረ መሆኑንና ከብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ጋርም የማይጣረስ መሆኑን እንዲቆጣጠር ያሳስባል፡፡ በተጨማሪም ቦርዱ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ ወቅታዊ ሚዛን በየጊዜው እንዲቆጣጠር፣ ብሎም ይህ ሚዛን በብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠው የባንኩ 15 በመቶ ካፒታል የበለጠ ምጣኔ የሌለው መሆኑን መቆጣጠር ኃላፊነትን ይሰጣል፡፡
የባንኮችን የሥራ አስፈጻሚዎች በተመለከተ መመርያው በዋናነት በቦርድ ተቀምጠው በብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ከተሰጣቸው የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ንግድ ፖሊሲዎች ጋር የሚጣጣም፣ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭና ግዥ መኖሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው ይላል፡፡ በተጨማሪም የሥራ አስፈጻሚው ወቅታዊ የባንኩን የውጭ ምንዛሪ ሚዛን መቆጣጠርና እንደ ሥራ አመራር ቦርድና ብሔራዊ ባንክ ላሉ ከፍተኛ ተቆጣጣሪ አካላት ወቅታዊ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት ያትታል፡፡
መመርያው የሥራ አስፈጻሚው በዕለታዊ የምንዛሪ ሽያጭና ግዥ ደረጃ ወርዶ መቆጣጠርና ሊከሰቱ የሚችሉ የምንዛሪ ሥጋቶችን ቀድሞ ለመተንበይ የሚያስችሉ መረጃዎችን መሰብሰብ እንዳለበት በጥብቅ ያዛል፡፡ መረጃ አሰባሰብና ሪፖርት ማድረግን በተመለከተ መመርያው ጠንከር ያለ ኃላፊነትን ለሥራ አስፈጻሚው የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ምንዛሪ የግዥ ጥያቄዎችን፣ የውጭ ምንዛሪ ዕለታዊ ዋጋና የምንዛሪ ድልድል የሚያደርገውን የባንኩን ኮሚቴ ቃለ ጉባዔ ጭምር በጥንቃቄ እንዲመዘግብ ያዛል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ መመርያው የቁጥጥር ሥርዓቱ የውስጥ የኦዲት ተቋምን የሚጨምር መሆን አለበት በማለት፣ ይህ ተቋም በገለልተኛነት ቢያንስ በዓመት አራት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ንግዱ በተቀመጠው የባንኩና የብሔራዊ ባንኩ መመርያዎች መሠረት እየተከናወነ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ያዛል፡፡ በተጨማሪም የዚህ ምርመራ ውጤት ለባንኩ ቦርድና ለብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥርና መጠባበቂያ አስተዳደር ክፍል ማቅረብ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡
በጥቅሉ ብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ሥርዓቱን አንድ መስመር ለማስያዝ ያመጣው መመርያ ሲሆን፣ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው በተለይ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ ቅርብ ለሆኑ ለደንበኞቻቸው የሚሰጡበትን ሥርዓት ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያ እንደሚሉት መመርያው የመጫወቻ ሜዳውን በእጅጉ የሚያስተካክል ነው፡፡ በቅድሚያ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ሥርዓት በየባንኮቹ የውስጥ አሠራርና ቅድሚያ አሰጣጥ ፖሊሲ የሚመራ ነው፡፡ መመርያው ግን የውጭ ምንዛሪ ድልድሉ ‹‹በቅድሚያ የመጣ በቅድሚያ ያገኛል›› በሚለው መርሆ መሠረት መመራት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
ነገር ግን በዚሁ መርሆ ውስጥ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት፣ ማሽኖች፣ መለዋወጫዎች፣ ጥሬ ዕቃና የመሳሰሉ ዕቃዎች ቅድሚያ እንዲሰጥም ያስገድዳል፡፡ በሌላ በኩል በጭነትና በጉዞ ላይ ላሉ የገቢ ዕቃዎች፣ በብሔራዊ ባንክ ለተፈቀደ እንደ የውጭ ብድር፣ ወለድ፣ ትርፍ እንዲሁም ለውጭ ዜጐች የሚከፈል ደመወዝንም ጭምር ቅድሚያ ሊያገኙ ይገባል ይላል፡፡
በመመርያው ሌላ የተሰመረበት ባንኮች በወጪ ንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቻቸው የሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት አንድ የውጭ ንግድ የሚያከናውን ደንበኛ ወደ ባንኩ ካስገባው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ አሥር በመቶውን የመጠቀም መብት ያለው ሲሆን፣ ቀሪው ግን የባንኩ ንብረት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የባንኮች አሠራር ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባንክ ባለሙያ ይህን ያረጋግጣሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ በኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ውስጥ የወጪ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ደንበኞች በመብራት ነው የሚፈለጉት፡፡ ‹‹የብሔራዊ ባንክ መመርያን አስተገብራለሁ ያለ ባንክ ዶላር አምጪ ደንበኞችን ለማጣት ይገደዳል፤›› ያሉት የባንኩ ባለሙያው፣ ከደንበኛው የሦስት በመቶ የባንክ መተማመኛ ሰነድ ኮሚሽን ከዶላር ከሚገኘው ትርፍ ጋር ተዳምሮ ደንበኛው ወደ ሌላ ባንክ ቢሄድ፣ የትኛውም ባንክ ይህንን ደንበኛ ለመቀበል ዓይኑን አያሽም ይላሉ፡፡ ነገር ግን መመርያው ደንበኛው ለባንኩ ካመጣው ዶላር አሥር በመቶ በላይ ያለው ምንዛሪ በተቀመጠው የቅድሚያ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት መከፋፈል እንዳለበት በጥብቅ ማስጠንቀቁ ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል የነበረው አሠራር ባንኮች ኮሚሽን በመሰብሰብ የአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል ሲሉ ባለሙያው ይተቻሉ፡፡
እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የተመቻቸላቸው የወጪ ንግድን የሚያከናውኑ ደንበኞች ወደ የገቢ ንግድ ሥራ እየገቡ መሆኑንም የባንክ ባለሙያው አያይዘው ያመለክታሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ይህ በተለይ በወጪ ንግድ ላይ የሚያደርጉትን ትኩረትና ጥንቃቄ በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን፣ ምክንያቱም ከገቢ ንግድ የሚገኘው ትርፍ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡
‹‹ብዙዎቹ ኤክስፖርተሮች ወደ አስመጪነት እየገቡ ስለሆነ፣ የአስመጪነት ሥራ ደግሞ በእጅጉ አትራፊ በመሆኑ ከኤክስፖርት የሚያገኙት ትርፍ አያሳስባቸውም፡፡ ይልቁንም ከኤክስፖርት ንግድ እየከሰሩ ከአስመጪነት ከፍተኛ ትርፍ ስለሚያገኙ በዚያው መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ ይህም አገሪቱን በጣም እየጎዳት ነው፤›› ሲሉ የሚገልጹት ደግሞ ሌላ የባንክ ባለሙያ ናቸው፡፡ ‹‹ይኼ ለመመርያው መውጣት አንድ ዋነኛ ምክንያት ነው ብዬ እገምታለሁ፤›› ያሉት ባለሙያው፣ መመርያው ይህንን ችግር በአጭር ጊዜ እንደሚቀርፍ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም መመርያው በተለይ በ‘‘CAD’’ (Cash Against Document) ወይም በሰነዱ ከቀረበው የገንዘብ መጠን አኳያ አሠራር ሥርዓት መሠረት ባንኩ የገቢ ዕቃን ግዥ ማፅደቅና የዕቃዎቹን ሰነድ ለገዥው ማስረከብ ያለበት፣ የዕቃዎች ክፍያ ሙሉ በሙሉ ለሻጭ በውጭ ምንዛሪ ከተከፈለ በኋላና ገዥው በብር ይህንኑ ክፍያ ከፈጸመ በኋላ መሆን እንዳለበት ያረጋግጣል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓርብ ከቀትር በኋላ እስከ ምሽት ድረስ ከባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በረቂቅ መመርያው ላይ ውይይት ማካሄዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ከባንኮች የሚቀርቡለትን አስተያየቶች አሰባስቦ ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን፣ ከማኅበሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡