Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበርዕደ መሬቱ የተደናገጡ የሐዋሳ ነዋሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በእምነት ተቋማት ለመጠለል ተገደዋል

በርዕደ መሬቱ የተደናገጡ የሐዋሳ ነዋሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በእምነት ተቋማት ለመጠለል ተገደዋል

ቀን:

በሐዋሳ ከተማና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች ጥር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ ለሁለት ጊዜ፣ በማግሥቱ ሰኞ ጠዋት በሦስት ሰዓት ተኩል ለሦስተኛ ጊዜ የተከሰተው ርዕደ መሬት (የመሬት መንቀጥቀጥ) ሥጋት በመፍጠሩ፣ ነዋሪዎችና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምሽቱን በእምነት ተቋማት ውስጥ በመጠለል እያሳለፉ መሆኑን ገለጹ፡፡ እንዲሁም በከተማዋ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ከቤታቸው በመውጣት በጋራ መኖሪያ አካባቢ ባሉ ቦታዎች ድንኳን በመጣል መጠለላቸውን ሪፖርተር በስፍራው ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

የሪፖርተር ዘጋቢ ወደ ሐዋሳ ከተማ ባቀናበት ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የከተማው ባጃጆች ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን አስተውሏል፡፡ ለወትሮው በእግር እንቅስቃሴ የሚስተዋልባት ሐዋሳ ጭር ብላም ታይታለች፡፡ አደጋው ከተከሰተ በኋላ ቤታቸውን ቆልፈው ያልተመለሱ በርካታ ነዋሪዎች መኖራቸውን ሪፖርተር ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

አክሊሉ ግዛው የባጃጅ ሾፌር ሲሆን የዛሬ 15 ዓመት ተመሳሳይ ነገር መከሰቱን ያስታውሳል፡፡ ሪፖርተር በከተማው ያገኛቸው ወጣት ትዕግሥት ዓለሙ፣ ወይዘሮ ኤልሳ አበበ፣ ወጣት ፅዮን ሰለሞን አደጋው ጭንቀትና ድንጋጤ እንደፈጠረባቸውና እስካሁንም ከውስጣቸው እንዳልጠፋ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሐዋሳ ከተማ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሰው ርዕደ መሬት ንዝረቱ ሐዋሳ፣ ሻሸመኔና ዲላ ከተማን ጨምሮ በዙርያው ያሉ አካባቢዎችን አዳርሷል፡፡

የዚሁ ርዕደ መሬት ክስተት ያስደነገጣቸው ተማሪዎች በመኝታ ክፍላቸው ማደር ባደረባቸው ሥጋት የተወሰኑት በግቢው ውስጥ ባለ ገላጣ ቦታ ለማደር ሲገደዱ፣ ሌሎች ደግሞ በከተማዋ ወደሚገኙት የእምነት ተቋማት በመሄድ ተጠልለው ለማደር መገደዳቸውን አንድ የሁለተኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ በሚገኘው የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ግቢ በርከት ያሉ ተማሪዎች ተጠልለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራት ሌላ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እንደገለጸችው፣ የመሬት መንቀጥቀጡ በራሱ ካሳደረባት ድንጋጤ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተማሪዎች ሕንፃዎች ውስጥ ባያድሩ እንደሚመከር ከተናገረ በኋላ ግቢውን በመልቀቅ የቅርብ ዘመዶች በሆኑ የሐዋሳ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ለማሳለፍ መሄዷን ጠቁማለች፡፡

በሕይወት ላይ የከፋ አደጋ ባያስከትልም ቁጥራቸው ከ80 እስከ 90 የሚደርሱ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ አነስተኛ ጉዳት ማድረሱን፣ 12 ተማሪዎች በሆስፒታል ተጨማሪ ሕክምና የተደረገላቸው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞ  ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ የፈተና ወቅት በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ያጠኑ ስለነበረ፣ እሑድ ምሽት በተፈጠረው የመጀመሪያው ርዕደ መሬት በፈጠረባቸው መደናገጥ ጥቂቶች በመስኮት ሲዘሉ፣ ሌሎች በበር በኩል ክፍሉን ለቀው ሲወጡ በደረጃ መውረጃ ላይ በተፈጠረው መገፋፋት ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡

የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ተማሪዎች በሐዋሳ ሆስፒታልና በዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና ተደርጎላቸው ተመልሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመንፈቀ ዓመቱ ፈተና ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚጀመር አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፣ በተፈጠረው ክስተት ፈተናው መውሰጃ ጊዜውን ማራዘሙን የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ አታክልቲ ኢሳይያስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ርዕደ መሬቱ የሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በዙሪያው ያሉ አካባቢዎች የተስተዋለ ሲሆን፣ አስደንጋጭነቱም ሆነ ንዝረቱን ተከትሎ በተፈጠረው መደናገጥ ጎልቶ የተስተዋለው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሚገኙ ተማሪዎች ላይ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በተለያዩ ካምፓሶች ከ35 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እያስተዳደረ ባለው ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 ሰዓት አካባቢ በድንገት የተከሰተው የመሬት ንዝረት፣ በቤተ መጻሕፍት በነበሩ ተማሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

‹‹ወቅቱ የፈተና በመሆኑ ብዛት ያላቸው ተማሪዎቻችን በተለይም በዋናው ካምፓስ በሚገኘው ቴክኖ ላይብረሪ ውስጥ ተሰብስበው በነበረበት ሰዓት ነበር የመጀመሪያው መንቀጥቀጥ የተሰማው፡፡ በዚህም የተደናገጡት ተማሪዎች ወደ ውጭ ለማምለጥ ሲሞክሩ ከአንደኛው ወለል ላይና በደረጃ ለመውረድ ሲተፋፈጉ በተወሰኑት ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ጥቂት ተማሪዎች ወደ ታችኛው ወለል ላይ ለመዝለል ሲሞክሩ ሌሎች ደግሞ በመስኮት ወደ ውጭ ለመወርወር ሲጥሩ፣ በመስታወት የመቆረጥ አጋጣሚም ደርሶባቸዋል፤›› ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

ከተማሪዎች መካከል በድንጋጤ ባሉበት ራሳቸውን ስተው የወደቁም እንደነበሩ ፕሮፌሰር ዮሴፍ ገልጸዋል፡፡ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የተከሰተው ግን የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይሆን የመሬት ንዝረት የሚባል ዓይነት መሆኑን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች መረዳታቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አመልክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኙ ሕንፃዎችና የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ውስጥ የተወሰኑ ግድግዳዎች መሰንጠቃቸው ተገልጿል፡፡ ከአንድ ሕንፃ በስተቀር በአብዛኛው ላይ ለአደጋ የዳረገ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የዩኒቨርሲቲው መሐንዲሶች አረጋግጠዋልም ተብሏል፡፡

ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ምሽት የማደሪያ ክፍሎችን በመሸሽ ከሕንፃዎቹ ውጭ ባሉ አረንጓዴ መስኮች ላይ ለማደር መገደዳቸውን ተማሪዎች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ ፕሬዚዳንቱ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደርና የትምህርት ዘርፍ ኃላፊዎችን ስብሰባ ጠርተው ነበር፡፡ አካባቢው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ስለሆነ ትኩስ የእሳት ገሞራ አመላካቾች ያሉበት በመሆኑ፣ የመሬትን የውስጥ ለውስጥ ዕምቅ የእሳተ ጎሞራ ኃይል የሚያጠና የትምህርት መስክ ሊከፈት እንደሚገባው ፕሬዚዳንቱ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ፣ የህዋና የሥነ ክዋክብት ተቋም ውስጥ የሚያስተምሩና በመስኩ ተመራማሪነታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፣ በሐዋሳ አካባቢ ለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ግዝፈትና ዓይነት ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ በሬክተር ስኬል መለኪያ 4.3 እንደሚሆንና በአካባቢው ካለው ሁኔታ ክስተቱ ብዙም አዲስ የማይባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የሐዋሳ ከተማ ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት በመሆኑ ክስተቱ በአብዛኛው አስደንጋጭ መሆኑ እንጂ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢውና ራቅ ባሉ አካባቢዎች የተለመደ ነው፡፡ ምናልባትም ለአብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የተጋነነ ቢመስልም፣ በባለሙያዎቹ ግን ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ ይገመታል፤›› ሲሉ ፕሮፌሰር አታላይ ገልጸዋል፡፡

ዮናስ ዓብይ እና ታምራት ጌታቸው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...