Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ደጃዝማች ሊኦንትየቭ

በአምባቸው ከበደ (ዶ/ር)

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌ ላቭሮቭ የሁለቱ መንግሥታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተመሠረተበት 120ኛ ዓመት በሚከበርበት በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የኢትዮጵያን አቻቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ይህ ከላይ የሚታየውን በለማ ጉያ የተሣለውን ሥዕል አበርክተውላቸዋል፡፡ ስጦታውም የሁለቱን አገሮች የቆየ የወዳጅነት ግንኙነት የሚያንፀባርቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሥዕል ላይ የሚታየው ግለሰብ ሁለቱ መንግሥታት እንዲቀራረቡና አገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር ከቅኝ ገዥዎች ጋር መራራ ትግል በምታካሄድበት ወቅት ከጎናቸን የቆመ ነው፡፡ ይህም አገራችን ወራሪዎችን ተቋቁማ ሕልውናዋን መታደግ እንድትችል ዕድል ሰጥቷታል ብንል ከሐቁ ብዙም አንርቅም፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሩሲያንና ፈረንሳይን የመሳሰሉ ወዳጆች በዚያን ጊዜ ለማግኘት ባትችል ኖሮ ይህን ፀረ ኢምፔሪያሊስት ትግል በድል ታገባድድ ነበር ብሎ ለመናገር በጣም ያስቸግራል፡፡ ይህም ሰው በዘመኑ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲው መድረክ ላይም የታወቀ ነበር፡፡ ግን ይህ ግለሰብ ማን እንደሆነና ከአገራችን ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደነበረው በአሁኑ ጊዜ የምናውቀው ስንታችን ነን?

ይህን ጥያቄ በማሰላሰል ብዙ እንድትጨነቁ አንፈልግም፤ በሥዕሉ ላይ የሚታየው ኮንት ኒኮላይ ስቴፓኖቪች ሊኦንትየቭ ይባላል፡፡

ይህ ሩሲያዊ እ.ኤ.አ. በ1862  የተወለደ ሲሆን የጦር ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በክብር ዘበኛ ጦር ውስጥ ማገልገል ጀመረ፡፡ ዳሩ ግን ወጣቱ መኮንን ከልጅነቱ ጀምሮ ተጓዥ ለመሆን ምኞቱ ስለነበር ከጥቂት ጊዜ በኋላ በገዛ ፈቃዱ ከሠራዊቱ ተስናብቶ ወደ ፋርስ አፍጋኒስታንና ህንድ ይጓዛል፡፡

ወቅቱ ኢትዮጵያና ሩሲያ ለመቀራረብ ጥረት የሚያደርጉበት ነበር፡፡ ስለዚህም በ1894 የሩሲያ የጂዮግራፊ ማኅበር በታወቀው ሳይንቲስትና በአገር መርማሪ በየሊሴየቭ የሚመራ አንድ የጥናት ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በጥናት ሽፋን ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚመሠረትበትን መንገድ ለማመቻቸት በመሆኑ አፄ ምኒልክ ወደ ሩሲያ መልዕክተኛ እንዲልኩ የሩሲያ መንግሥት የላከውን ደብዳቤ ይዞ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ ባለታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የዚህ ቡድን አባል  ሆኖ ነበር፡፡ በኋላም የቡድኑ መሪ የሊሴየቭ ስለታመመ ሊኦንትየቭ መሪነቱን ተረከበ፡፡

ሊኦንትየቭ በ1895 እ.ኤ.አ. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የመጣ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም የንጉሠ ነገሥቱን አመኔታ አግኝቶ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ዕድል አገኘ፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው አፄ ምኒልክ መልክተኞች ወደ አገሩ እንዲላኩ የሩሲያ መንግሥት ጥሪ አስተላልፎላቸው ነበር፡፡ ንጉሡም ሐሳቡን በበጎ ስለተመለከቱት በፊታውራሪ ዳምጠው የሚመራ አንድ የመልክተኛ ቡድን ወደ ሩሲያ ላኩ፡፡ በቡድኑ ውስጥም የምኒልክ የቅርብ ባለሟሎች የሆኑት ቀኛዝማች ገነሜ፣ መምህር ገብረ እግዚአብሔር፣ ልጅ በላቸውና አቶ ዮሴፍ የነበሩ ሲሆን ይዟቸው እንዲሄድም ሊኦንትየቭ ተመደበ፡፡ ንጉሡ ለዚህ የውጭ አገር ሰው ይህን የመሰለ ኃላፊነት መስጠታቸው በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው፡፡ እሱም እንግዶቹ በሩሲያ ከአርባ ቀናት በላይ በቆዩበት ወቅት አንድም ቀን ሳይለያቸው ንጉሡ የጣሉበትን አደራ በሚገባ ተወጥቷል፡፡ የልዑካኑ ተልዕኮ ከታሰበው በላይ የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለቡድኑ የሩሲያ ሕዝብና መንግሥት ደማቅ አቀባበል ያደረገለት ሲሆን ራሱ የሩሲያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ኒኮላይም መልዕክተኞቹን ተቀብሎ አነጋግሯቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ እንግዶች የተደረገው ዓይነት መስተንግዶ ለማንም የውጭ አገር መልክተኛ እንዳልተደረገ በወቅቱ የሚወጡ የሩሲያ ጋዜጦችና መጽሔቶች ዘግበውታል፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት ሁለቱ መንግሥታት ውል ባይፈራረሙም ጣሊያን ኢትዮጵያ ጥገኛዬ ነች እያለች በምትደነፋበት ወቅት የኢትዮጵያ መልክተኞች ሩሲያን መጎብኘታቸው በራሱ ብቻ ለአፄ ምኒልክ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነበር፡፡ ዳሩ ግን የጉብኝቱ ውጤት በዚህ ተወስኖ የቀረ ሳይሆን ከፍተኛ ቁሳዊና የገንዘብ ዕርዳታም የተገኘበት መሆኑን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ በመልዕክተኛው ቡድን በኩል የሩሲያ መንግሥት ሠላሳ ሰባት ሺሕ ጠመንጃዎች፣ አምስት ሺሕ ጎራዴዎችና አራት መቶ ሺሕ ሩብል በዕርዳታ መልክ ለአገራችን ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የሊኦንትየቭ ድርሻ ቀላል እንዳልነበር መገመት ይቻላል፡፡

ሊኦንትየቭ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጠብ ወደ ጦርነት በማምራት ላይ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ከቆሙ ጥቂት የውጭ አገር ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ቅኝ ገዥዎች በተለይም ጣሊያኖች ስሙን ሲያጎድፉት ማየት የተለመደ ነው፡፡ እነሱም ይህን ሰው ጀብደኛና ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል ሁኔታዎችን እንዲያመቻችለት የሩሲያ መንግሥት የመደበው ሰላይ ነው ብለው ፕሮፓጋንዳችውን ይነዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ መረጃዎች ስለሌሉን ሊኦንትየቭ የሩሲያ መንግሥት ሰላይ ነው ወይ አይደለም ብለን ለመደምደም አንችልም፤ ደግሞም ይህ ጥያቄ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ብዙም ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ዋናው ጉዳይ በ19ኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ ላይ ሁለቱ አገሮች በቀይ ባሕር አካባቢ አንድ ዓይነት አቋም ያላቸው መሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህም የሊኦንትየቭን እንቅስቃሴ እነ አፄ ምኒልክም ቢሆኑ ከሩሲያ መንግሥት ፍላጎት ውጭ ነው ብለው እንደማያምኑ ግልጽ ነበር፡፡ ግን ይህም ተባለ ያ ሊኦንትየቭ ለኢትዮጵያ ነጻነት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርገ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ እሱም በአጭር ጊዜ ውስጥ የንጉሡን አመኔታ ለማግኘት በመቻሉ ዋና የጦር አማካሪያቸው ሆኖ ነበር፡፡ ንጉሡም ስለጦርነቱ ዕቅድ ከእሱ ጋር ይመካከሩ፣ ከአበጋዞቻቸው ጋር በሚያደርጓቸው አንዳንድ የጦር ሸንጎዎች ላይ እንዲሳተፍ ይፈቅዱለትና እሱም ሐሳቡን ለመግለፅ ወደኋላ የማይል እንደነበር ከደረሱን መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ይህን በመሰለ በአንድ ሸንጎ ላይ የሩሲያ ሠራዊት በናፓሊዮን ጦርነት ወቅት የተጠቀመበትን የጦር ስልት እንዲከተሉ፣ ማለትም የጣሊያንን ጦር እያታለሉ በጥልቅት ወደ መሀል አገር እንዲገባ  ካደረጉ ከኋላ በደፈጣ ውጊያ በማዋከብ በመጨረሻ እንዲደመስሱ፣ ምሽጎችንና የተጠናከሩ መከላከያዎችን እንዲያጠቁ ሐሳብ  ማቅረቡ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ይህን ምክር ምን ያህል ከግምት ውስጥ አስገብተውት እንደነበር አሁን መናገር አስቸጋሪ ነው፣ ዳሩ ግን በተለይም ከመቐለው ከበባ በኋላ አፄ ምኒልክ ጣሊያኖችን ምሽጋቸው ድረስ ሄደው ለማጥቃት ፍላጎት ያላሳዩት የኋላ ኋላ የዚህን ምክር ትክክለኛነት ተረድተውት ይሆን ወይስ ከመቐለው ተሞክሮ ትምህርት ቀስመው?

ሊኦንትየቭ ለኢትዮጵያ ጦር ያደረገው ዕርዳታ በምክር ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ እሱም ወደ ሩሲያና ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በተደጋጋሚ በመሄድ በቀላሉ የማይገመት ብዛት ያለው የጦር መሣሪያዎችን እየገዛ ወደ ኢትዮጵያ አምጥቷል፡፡ የአውሮፓ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ወደ አፍሪካ የጦር መሣሪያ እንዳይገባ በዓይነ ቁራኛ በሚቆጣጠሩበት ጊዜ ይህን ማድረግ ቀላል ስላልነበር ሊኦንትየቭ ራሱን ለታላቅ አደጋ አጋልጦ ነበር ማለት ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ያለ ዘመናዊ ሥልጠና ዋጋ ስለሌለው ሊኦንትየቭ ዘመናዊ የጦር ማሠልጠኛ አቋቁም የኢትዮጵያ ተዋጊዎች መሠረታዊ የጦር ትምህርት እንዲቀስሙና ከአዳዲስ የጦር መሣሪያዎች ጋር እንዲተዋወቁ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ይህ ሥልጠናም በደንብ የታሰበበት ለመሆኑ ለማሠልጠኛ እንዲሆን ‹‹የኢትዮጵያ የጦር ኃይል›› በሚል ርዕስ ራሱ የጻፈውና ያሳተመው መጽሐፍ ጥሩ ምስክር ነው፡፡ በመጨረሻም ሊኦንትየቭ በዓድዋ ጦርነት ላይ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን በመሠለፍ ለአገራችን ነፃነት መከበር የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ይህ ሩሲያዊ መኮንን ከጦርነቱ በኋላም ለኢትዮጵያ መንግሥት ማገልገሉን አላቆመም፡፡ በዚህ ወቅት በዲፕሎማሲው መስክ የፈጸመው ተግባር በተለይ የሚጠቀስ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከጦርነቱ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ትኩረት ለኢትዮጵያ በሚበጅ መልኩ የሰላሙን ውል ተፈራርሞ ጦርነቱን ማብቃት ነበር፡፡ አፄ ምኒልክም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም ለአውሮፓ መንግሥታት እንዲያስታውቅላቸው ሊኦንትየቭን ወደ ሳንፒተርቡርግና ሮም ልከውት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በእሳቸው ትዕዛዝም ወደ ኮንስታንቲኖፕል ሂዶ በኢየሩሳሌም ስለሚገኙት የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ከቱርኩ ሡልጣን ጋር ተነጋግሮ ተመልሷል፡፡ እንደዚሁም የዳግማዊ ኒኮላይን የዘውድ በዓል ምክንያት በማድረግ አፄ ምኒልክ የለቀቋቸውን ሃምሳ የጣሊያን ምርኮኞች ከአዲስ አበባ ይዞ ሄደ ለጣሊያን መንግሥት ተወካይ በጅቡቲ ያስረከበው ሊኦንትየቭ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

ከዚህም ሌላ ሊኦንትየቭ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ጎዳና ወደፊት እንድትራመድ ፍላጎት ያለው ሰው ስለነበር ትምህርት እንዲማሩ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገሩ የወሰደ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቀደምት ዘመናዊ የኢትዮጵያ ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ለትምህርት ወደ መስኮብ የወሰዳቸው ሊኦንትየቭ እንደሆነ ከሞቱ በኋላ በወጣው ኦቶባዮግራፊ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጽውታል፡፡ ተክለሐዋርያት እንደ ዕድል ሆኖ ሌላ አሳዳጊ አገኙ እንጂ የወሰዳቸውን አብዛኞቹን ተማሪዎች የሚያስተምራቸው በራሱ ወጪ ሊኦንትየቭ ነበር፡፡

እንደምናየው ሊኦንትየቭ አገራችንና ሕዝቧን ለመርዳት የፈጸመው ተግባር ወደር አይገኝለትም፡፡ በዚያ ከባድ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ እሱን የመሰለ ለአፍሪካውያን ቀና አስተያየት ያለው ሰው ማግኘቷ ዕድለኛ ነበረች ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዚህ ሰውም አፄ ምኒልክም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት ነበራቸው፡፡ ንጉሡም ለዚህ የአገራችን ወዳጅ የኢትዮጵያን ከፍተኛ ማዕረጎችና ሸልማቶች ሰጥተውታል፡፡ የዓድዋ ጦርነት ከተፈጸመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አፄ ምኒልክ በአገራችን  ያልተለመደውን ‹‹ኮንት›› የተባለውን ማዕረግ ለሊኦንትየቭ ሰጥተውታል፡፡ የሹመት ደብዳቤውም ‹‹ከመስኮብ መንግሥት ተልዕኮ መጥቶ የእኔን መንግሥት በመልካም ስላገለገለን ወዳጃችንን ሙሴ ሊዎንቴፍን ማገልገሉንም በንሻናችን አክብረን የገለጥንለት በዚህ ደብዳቤ ስለማገልገሉ ኮንት ብለነዋል፤›› ይላል፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ. ግንቦት 26 ቀን 1899  ደጃዝማች ተብሎ አንድ በደቡብ  ኢትዮጵያ የሚገኝ ግዛት ተሰጠው፡፡ ይህ ግዛት ጎፋ እንደሆን በአንዳንድ የኢትዮጵያ ምንጮች ተጠቅሶ ይገኛል፡፡

ሊኦንትየቭ የሩሲያና የጃፓን ጦርነት ሲጀመር ወደ አገሩ ተመልሶ ከጦር ኃይሏ ጎን በመሠለፍ ተዋግቷል፡፡ ከዚያም በፓሪስ ሲኖር እ.ኤ.አ. በ1910  ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን አስከሬኑም ወደ አገሩ ተወስዶ በክብር አርፏል፡፡

በአጠቃላይ ሊኦንትየቭ ኢትዮጵያ አገራችን በ19ኛ ምዕት ዓመት መጨረሻ ላይ ከባድ ችግር በደረሰባት ጊዜ መጠነ ሰፊ ዕርዳታ ያደረገላት እውነተኛ ወዳጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ዶ/ር አምባቸው ከበደ ደስታ በሞስኮ እስቴት ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ፔችዲ አግኝተው በባህል ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ አገልግለዋል፡፡ ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles