Wednesday, February 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከከንፈር ጤዛ ሥር

በመዝገበቃል አየለ ገላጋይ

ተፈጥሮ የውበት መዳፏን የዘረጋችለትና የተወለደበት ሁሉ የሚያምርለት የታደለ አካባቢ ነው፡፡ የመጠሪያ ስሙ ሥርወ መነሻ የኦሮምኛ ቃል እንደሆነ የሚነገርለት ቃሉ፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን የኮምቦልቻ ከተማ ኩታገጠም ነው፡፡ የዚህ አካባቢ ኮረዳዎች ውበት የተመልካችን ልብ ያነሆልላል፡፡ ለመምጠቅ እንደተዘጋጀ «ሮኬት» የተወደሩት ጡቶቻቸው አንገት እንዳይደፉ በአሥራ ሁለት ቁጥር ሚስማር ግራ ቀኝ ደረታችው ላይ የተቸነከሩ ይመስላሉ፡፡ ከመለሎ አንገታቸው ላይ የተሰካው መልክዐ ገጻችው ከተቦካ የቸኮላት ከረሜላ ሊጥ የተሠራ ይመስላል፡፡

አብዛኞቹ ጫማ መጫማት አያዘወትሩም፡፡ ከጥፍር ቀለም ጋርም አይተዋወቁም፡፡ እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የሚያስጌጡት በጉርሽጥ ወይም በእንሶስላ ነው፡፡ የሰውነታቸውን ጠረን ለመጠበቅ ብዙ ገንዘብ አውጥተው ሽቶ መግዛት አይጠበቅባቸውም፡፡ ከዕፀዋት ሥራ ሥር የተሠራ ቦለቅያ ወይም ወይባ ይሞቃሉ እንጂ፡፡

የንብ አውራ ወገብ ከመሰለው ለግላጋ ሽንጣቸው በታች ከሽብሽቧቸው (ከቀሚሳቸው) ሥር የሚውለው ዳሌያቸው ማዕበል እንደተነሳበት የውቅያኖስ ውኃ እየተላጋ ሲወዛወዝ ኑ ወዲህ እያለ ከሩቁ ይጣራል፡፡ ጋሜ፣ ቃሬሳ፣ ቆንዳላ… እየተባለ የሚጠራው ዞማ ፀጉራቸው ከትከሻቸው ላይ ወርዶ ሲዘናፈል የንብ መንጋ የሰፈረባቸው ይመስላሉ፡፡ የልብ ቅርፅ ያላቸው ከንፈሮቻቸው በምጥን ፈገግታ ፈሽረክ ሲሉ በውቅራት (በንቅሳት) የሞገሰው ጥርሳቸው የተቃራኒ ፆታ ልብን አሸንፎ በማነሁለል ይማርካል፡፡

የቃሉ ጎረምሳዎችና ኮረዳዎች የውስጥ ስሜታቸውን በዜማና በግጥም ለመግለፅ የታደሉ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የሚያዜሟቸው ዜማዎች የፍቅር ዜማዎች ሲሆኑ የዓመት በዓላት፣ የሠርግ ጊዜያት፣ እንጨት ሰበራና ወፍ ጥበቃ የመሳሰሉት ተግባራት ለከንፈር ወዳጆቻቸው ስሜታቸውን በዘፈን ለመግለፅ የሚጠቀሙባቸው መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ፉከራ፣ ዘከን በአጠቃላይ ዜማና ሙዚቃ፣ ለቃሉ ወጣቶች እንደሚተነፍሱት የኦክስጅን አየር ነው፡፡ በተመሳሳይ አካባቢ የሚገኙ ጎረምሳዎችና ኮረዳዎች ተጠራርተው በአውላላው ሜዳው ላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያዜሙ፣ የአገሩ እንግዳ የሰዉ ባዳ የሆነ መንገደኛ ስሜትን በመፈታተን ከጉዞው ያስቆሙታል፡፡ ጎረምሳዎቹ ዱላቸውን ከመሬት ላይ ወድረው እያስገመገሙ በኅብረት ሲጨፍሩ የኮረዳዎቹን ልብ ያሸፍታሉ፡፡ እነዚህን የመገናኛ አጋጣሚዎች በመጠቀም ግጥማቸውን እየደረደሩ፣ ዜማቸውን እያንቆረቆሩና ክብ ሠርተው እየሾሩ በመጨፈር የአንጀታቸውን ይተነፍሳሉ፡፡ እንዲህ ሲሉ ቃሉዎች፡፡

«አንተ ላይ ደመና አንተ ላይ ሰማይ፣

ጠይም ዘለግ ያለ አላየህም ወይ፡፡

እዩት ከዚያ ማዶ ከገደሉ ሥር፣

ጠይም ልጅ ይፈልቃል ውኃ ይመስል፡፡

ጠይም ዘለግ ያለ ጎራዴ ታጣቂ፣

ቁጭ ሲል አጫዋች ሲሄድ አስጨናቂ፤

ዓይንም በኩል ያምራል ጥርስም በንቅሳት፣

እየመራረጡ ሸጋ ሸጋ መብላት፡፡

እሄድ እሄድና እላለሁ ታከተኝ፣

ፍቅሩ በጎራዴ እያነካከተኝ፡፡

በጎራዴም አይደል በጉዶ በጉዶ፣

እንዴት ሰው ይሞታል ጠይም ሸጋ ወዶ፡፡

ጠይሙ ጠይሙ ጠይሙ ሸጋው፣

ከ’ናቱ ቤት ያለው ሚስት ያላገባው፣

ዓመት ከስድስት ወር ፈጭቼ ላብላው፣

እጄ ብጉር ያውጣ ላልመረረው፡፡»

ያነጋገር ቅላፄያቸው ይማርካል፡፡ ቅብጠት አይጨመርበትም፡፡ ምንጊዜም ራሳቸውን ነው የሚሆኑት፡፡ የሚያደረጉት ነገር ሁሉ መዓዛው እነሱን እነሱን ይላል፡፡ ኮረዳዎችና ጎረምሳዎች ተገናኝተው ከሚጨፍሩባቸው አጋጣሚዎች መካከል የሠርግ ዋዜማ ይገኝበታል፡፡ ኮረዳዎች ከሙሽሪት ቤት ተገናኝተው ከሚጨፍሩባቸው አጋጣሚዎች መካከል የሠርግ ዋዜማ ይገኝበታል፡፡ ከሙሽሪት ቤት ተገኝተው ሙሽሪትን ጉሽርጥ ወይም እንሶስላ ያሞቃሉ፡፡ ጎረምሳዎች ከወንዱ ሙሽራ ቤት ተገኝተው ጫጉላ ይሠራሉ፡፡ ሙሽሪትን እንሶስላ አሙቆና ጫጉላ ሠርቶ መበታተን ግን አይታሰብም፡፡ ጭፈራው ይጀመራል፤ የዘፈኑም ሐድራ ይደራል፡፡ አልፎ አልፎ የሙሽሪትና የሙሽራው አካባቢ ሊራራቅ ቢችልም፣ ኮረዳዎችና ጎረምሳዎች ግን ተገናኝተው በጥምረት መጨፈራቸው አያጠራጥርም፡፡ አጀማመራቸው ከሁለቱ መካከል በአንደኛቸው ሊሆን ይችላል፡፡

በቃሉ፣ ከጋብቻ በፊት የከንፈር ወዳጅ መያዝ የተለመደ ባህል ነው፡፡ ወደሌላው ቅብጠት ግን አይሸጋገሩም፡፡ በሠርጉ ዋዜማ ከተሰበሰቡት ጎረምሳዎች መካከል የአንዱ የከንፈር ወዳጅ ልትሆን ትችላለች  ሙሽሪት፡፡ የከንፈር ወዳጁ ማግባት ከሆዱ ውኃ የጨመረበትና ልቡን ባር ባር ያለው ጎረምሳ ታዲያ እንዲህ ሲል ያንጎራጉራል፡፡

“አበሐው ትንቧለል አበሐው ትንቧለል፣

የ’ሷ ቤት ተሠራ እኔ ስንቀዋለል፡፡

ተኩቤ አገር በታች ስሙ ነው ገደሮ፣

ወዳጁን ያልዳረ አለወይ ዘንድሮ?

የትንቧለል ቀሚስ ካልባው ላይ ያለው፣

እምቢ አለብስም አለች ሽቶ ካልነካው፡፡

ካ’ፋር አገር በታች አፋር አለ ወይ፣

ሞትና መለየት አንድ አይደሉም ወይ፡፡

ሞትና መለየት አንድ አይደል መንገዱ፤

ሞት አይሻልም ወይ ቁርጥ ያለው ሆዱ፡፡”

ከተሰበሰቡት ጎረምሳዎች መካከል አንዱ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የወንዱ ሙሽራ ዘመድ፣ ወንድም አልያም የቅርብ ጓደኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከላይ ብሶቱን በእንጉርጉሮ የገለፀውን ጎረምሳ ፀጥ ብለው ካደመጡት በኋላ ከመካከላቸው አንደኛው ተራውን ጠብቆ እንዲህ ሲል ይመልስለታል፡፡

“ከጎድጓዳ ስፍራ ከንፈር የሳመ ሰው፣

ከረጅም ማማ ላይ ወፍ የጠበቀ ሰው፣

አወይ ጣም አወይ ጣም ለደጋገመው ሰው፣

እንኳን ሽማግሌ ዳኛም አይመልሰው፡፡

ይኼ ፍቅር ማለት ሞኝ ነው ጨርሶ፣

ያዙኝ ያዙኝ ይላል በሰው ገንዘብ ደርሶ፡፡”

ከሙሽሪትና ከሙሽራው ቤት የሠርጉን ዝግጅት ለማሰናዳትና በምክር ለማገዝ የመጡት አረጋዊያንና አረጋዊያት የወጣቶችን ለዛ ያለው ጨዋታ እያዳመጡ መለስ ብለው የቀድሞ የወጣትነት ጊዜያቸውን በማስታወስ በፈገግታ ይዋጣሉ፡፡ ነገሩ አልፎ አልፎ ከረር ካለ ግጭትም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ታዲያ ካጠገባቸው ጨዋታቸውን የሚከታተሉት ሽማግሌዎች ነገሩ አላምራቸው ሲል ከወዲሁ በብልሃት ለመቅጨት፣

‹‹እንጫወት እንጂ ጨዋታ ገርገሩን፣

አሁን ምን አመጣው ክፉ ንግግሩን፡፡”

በማለት ይገስፁና ጭፈራውን በጎ ጎን እንዲይዝ ያደርጉታል፡፡ የሽማግሌዎቹ አባባል ምን ለማለት እንደሆነ የገባቸው ወጣቶችም ወዲያውኑ ጭፈራውን ወደ ፍቅር ይቀይሩታል፡፡ የአካባቢው ሽማግሌዎች ማንኛውንም ልጅ ወልጀዋለሁ አልወለድኩትም የሚለው አያስጨንቃቸውም፡፡ ማንኛውንም ጥፋተኛ ልጅ ይመክራሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ይገስፃሉ፤ ይቆነጥጣሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ከወላጆቻቸው ወቀሳ ከሰሳ አይደርስባቸውም፡፡ ለቃሉዎች የአካባቢው ልጆች የጋራ ልጆቻቸው ናቸውና፡፡

በቃሉ፣ ለሁለት ወጣቶች ፍቅር የትዳር መብቃት የቤተሰቦቻቸው ፈቃደኝነት ካልተጨመረበት በራሳቸው መጋባቱ የባህል ተፅእኖ አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የወደዳትን እንዳያገባ የቤተሰብ ፈቃድ የተነፈገው አፍቃሪ ወጣት፣

‹‹የቀይ ልጅና የጥድ አበቃቀል፣

ከማይመቸው ላይ ከገደል መካከል፡፡

አንቺ እንደ ስድስቶ ከዚያ ላይ ሁነሽ፣

የሰው ልጅ በናፍቆት ትገሊኛለሽ፡፡

ባርማሽላ በላሁ በብር ገዝቼ፣

እኛ ብንዋደድ ስፍራው መች ተመቼ፡፡

እናትና አባትሽ በፍቅር አረጁ፣

ምነው የ’ኛ ጊዜ ሰንሰለት አበጁ?››

በማለት ብሶቱን ይገልጻል፡፡ በቃሉ፣ ሁለት ቤተሰቦች ቀረቤታቸው እየጠነከረ ከመጣ በመካከላቸው ያለው መልካም ግንኙነት ለሁልጊዜም ፀንቶ እንዲኖር ከማሰብ ጋር በተያያዘ ልጆቻቸው ገና ከማደጋቸው በፊት በሕጻንነታቸው ልጅህን ለልጄ ልጄን ለልጅህ በማለት አስቀድመው ለግቢነት ቃል ይገባባሉ፡፡ ልጆቹም ሲያፍሩ ሲፈሩ በዱር በሜዳው በአሻጋሪ እየተያዩ አብረው ያድጋሉ፡፡ ታዲያ የጓደኞቿን መዳር አይታ ይህ ዕድል የእሷም ትሩፋት እንዲሆንላት የተመኘችው ልጃገረድ ፍቅሯ ገሀድ ወጥቶ የፍቅሩ ተቋዳሽ እንድትሆን የፈለገች መሆኗንና ውስጧ ለጋብቻ መዘጋጀቱን ለመግለፅ፣

‹‹አፋፍ ላ’ፋፍ ስሄድ አገኘሁ ሸምበቆ፣

አልቀጨኝ አለ ልጅነቴን አውቆ፡፡

አፋፍ ላ’ፋፍ ስሄድ አገኘሁ አለንጋ፣

እኔም አደኩልህ አንተም ልብህ ይርጋ፡፡”

በማለት ፈቃደኛ መሆኗን በዜማ ወንጭፏ ትወረውርለታለች፡፡ አያይዛም በጭፈራው ከታደሙት ሰዎች ፊት አሸርጣ እየተወዛወዘች ለፍቅረኛዋ ያላትን ፅኑ ፍቅር በዜማና በግጥም እያሞጋገሰች ትገልጽለታለች፡፡ ውስጧ በሀሴት ይሞላል፡፡ ከእሱ ጋር ወደፊት የሚኖራትን የፍቅር ሕይወት እያሰበች እና በህሊናዋ መነጽር እየተመለከተች፣

‹‹ስሙ የተጻፈው በቀለመ ህንድ፣

በአባ ሼህ አብደላ በአባ ሼህ ሰይድ፣

አባ ሼህ አብደላ እንጠይቀወት፣

ጠይም የወደደ ያጣል ወይ ጀነት?

ጠይም የወደደ ለ’ሳት ነው ካላችሁ፣

ለምን ሴደቃውን ትበሉታላችሁ?››

ስትል ፍቅሯን ለፍቅረኛዋ ታንፀባርቃለች፡፡ ያን ጊዜ እሱም ህዋሳቱ እየተፍታቱ፣ የደሙ ሙቀት እየተሰማውና አሻግሮ በስስት እየተመለከተ ብቻ ዝም አይላትም፡፡ ይልቁንስ እንዲህ ሲል ይመልስላታል፡፡

‹‹ልብ አስደንግጥ አላት እንደ’ባብ ሬሳ፣

ኑራም አትጠገብ ታይታም አትረሳ፡፡

ከበኬ ሜዳ ላይ አይበቅልም እንጉዳይ፣

በጥርሷ ሰላሳ በዓይኗ መቶ ገዳይ፡፡

በጥርሷ ሰላሳ በዓይኗ መቶ ገላ፣

እኛም አይተነዋል ሴደቃው ሲበላ፡፡››

በቃሉ፣ አንዲት ልጃገረድ ከታጨች በኋላ እስከ ክብሯ በባሏ ቤት እንድትገኝ ቤተሰብ ይቆጣጠራታል፡፡ ከቀድሞ የከንፈር ወዳጇ ጋራ ያላትንም ግንኙነት እንድታቆም ቤተሰባዊ ምክር ይሰጣታል፡፡ በዚህ ምክንያት መለዬት እጣ ፈንታው የሆነበት የቀድሞ ወዳጇ እሷ በምትገኝበት አካባቢ ጠብቆ እየተንጎማለለ፣

‹‹አልብኮ በግራ በትሆ በቀኝ፣

እንኳን ንግግሯ ጠቧ ናፈቀኝ፡፡

ጀንበሪቱ ገብታ ካልጨለመ በቀር፣

ዓይኑ አይነቀልም ሰው ከወዳጁ አገር፡፡

ሽንኩርት አንዱን በሉት ደገሙት አፍ ገማ፣

ነውር አይደለሞይ ታምቶ መቅረትማ፡፡››

እያለ ናፍቆትና ሰቀቀኑን በዜማ ወንጭፍ ይወረውርላታል፡፡ ከትዝታ ውቅያኖስ ውስጥ ዘላ እንድትዘፈቅ ያደርጋታል፡፡ የኋሊዮሽ ተመልሳ በትዝታ ትሸመጥጣለች፡፡ በሀሳቧ ወገቡ ላይ ትጠመጠማለች፡፡ ደረቱ ላይ ተለጥፋ ታንሾካሹካለች፡፡ ነጠላ ኩታዋን አከናንባና ተከናንባ ከንፈሯን በከንፈሩ ላይታርመሰምሳለች፡፡ ከዚያም ለብዙ ዓመታት አብሯት በፍቅር የቆየውን የከንፈር ወዳጇን ለማግኜት ትጓጓለች፡፡ በዚህ ብቻ አታቆምም፡፡ ያለባትን የቤተሰብ ጥብቅ ቁጥጥር አልፋ በመሄድ እንደሚገናኙ ለማብሰር፣

‹‹ቦርከና ቢሞላ ቢነካ ሰማይ፣

ዘንዶ ቢጠመጠም ከጉልበቴ ላይ፣

ሸጋ ልጅ ሰው ልኮ መቅረት አለ ወይ?

ሕልም አየሁኝ እኔ ሕልም አየህ ወይ አንተ፣

ነፋስ አውለብልቦ ሲጥለኝ ወደ አንተ፡፡

አባቴም ይላሉ የታባሽ ፍትልክ፣

እናቴም ይላሉ የታባሽ ፍትልክ፣

እኔ ግን በዘዴ በአጥሪቱ ሹልክ፡፡

በጥቃቋቁር በሬ ይታረሳል እርሻ፣

እንዴት ነው ሸለቆ ፍቅር መጨረሻ፡፡››

በማለት ቤተሰቦቿ ሳያዩዋት ተሾልካ በመምጣት ቀድሞ የከንፈር ወዳጅነታቸውን ከሚተገብሩበት የተለመደ ቦታ እንዲገናኙ ዜማዋን እያንቆረቆረች ታሰማዋለች፡፡ ድምድም ጎፈሬውን ነቅሶ፣ ዓይኑን በቀጫጭን ተኳኩሎ፣ መሟጫውን ከጥርሱና ሚዶውን ከጎፈሬው ሰክቶ ለወዳጁ እጅ መንሻ የሚሆን ማርዳ፣ መስቀል፣ አምባር፣ ዲኮት፣ ጉትቻ፣ ያንገት ቁርጥ፣ የእግር አልቦና ከመሳሰሉት የተለመዱ የከንፈር ወዳጅ ስጦታዎች መካከል አቅሙ የፈቀደለትን ይዞ በመምጣት በፍቅር ያበረክትላታል፡፡ በአካባቢው ከሚገኘው እሾህ አልባ ተክል ቅጠል ዘንጥፎ ወይም ሳር አጭዶ ከጎዘጎዘ በኋላ አክብሮ ያስቀምጣታል፡፡ አልያም ከጭኖቹ ላይ አሳርፎ በፍቅር ይንከባከባታል፡፡ ዓይኖቹን አጥቢያ ኮከብ ከሚመስሉት ከዓይኖቿ ላይ እያንከራተተ በስስት ይመለከታታል፡፡ እወድሀለሁ ወይም እውድሻለሁ ለማለት ቃላት መፍጠር አይጠበቅባቸውም፡፡ ቋንቋም አያባክኑም፡፡ በትልቁ ፀጥታቸው ውስጥ ህዋሳታቸው እርስ በርሳቸው ይነጋገራሉ፡፡ ከንፈሮቻቸው እርስ በርሳቸው ይሳሳባሉ፡፡ መተፋፈር አይታሰብም፡፡ የከንፈር ወዳጅ ይሉታል ብሂል ከዚህ ላይ በተግባር ይፈተናል፡፡ ታዲያ ልታገባ መታጨቷን ከማወቁ ጋር ተያይዞ እልሁ ይተናነቀዋል፡፡ ፍቅሩም የበለጠ ይጨምርበታል፡፡ አዬ የከንፈር ወዳጅ፡፡ ይህንን ቁጭቱን ታዲያ ስሜቱ እዬተንተከተከ፣

‹‹አሸቅቤ ባየው ሰማይ ተሰንጥቆ፣

አዘቅዝቄ ባየው ያ’ዳም ልጅ ተጨንቆ፣

ከዚህ ሁሉ መሀል ልቤ አንችን ወዶ

ማሰሪያ የሌለው ሆኗል የጤፍ ነዶ፡፡

ቀይ ሎሚ ነሽ እኮ የምትመጠጭ፣

ትርንጎ ነሽ እኮ የምትገመጭ፣

ከሆዴ ገብተሻል አርፈሽ ተቀመጭ፡፡››

ሲል ያንቆላጵሳታል፡፡ ፍቅር ነዋ! ፍቅር የሰብአዊ ንጉሥ!!!

ቃሉ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙት አገሮች ካለው የተፈጥሮ ነዳጅ ይልቅ ተዝቆ የማያልቅ የባህል ሀብት ያለበት፣ ነዋሪዎቹ «ቤት ለእንቦሳ» ሲሉ ጥርሳቸው ለፈገግታ የሚሽቀዳደምበት፣ ውበት እንደ ‹‹ሱናሜ›› ያጥለቀለቀው፣ እስላም ክርስቲያኑ ኅብረት ፈጥረው የሚኖሩበት እና የፍቅር ሰንደቅ ከዳር እስከ ዳር የሚውለበለብበት ውብ የውቦች ሀገር ነው ቃሉ፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስና የቋንቋ ወይም በአጠቃላይ የሥነ ሰብእ ሊቃውንት ተረከዛቸውን አንስተው ወደ ቃሉ ቢተሙ በሙያ ዘርፋቸው ጥርኝ ዘርተው ዳውላ ያፍሳሉ ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ብቻ ስለቃሉ ሁሉንም ማለት ቢሳነኝ ዝም ማለትን መረጥኩኝ፡፡ ቸር እንሰንብት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles