የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የእነ አቶ መላኩ ፈንታና የእነ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ መዝገብ ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤት አቀረበ፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ከነባለቤታቸው፣ ከነጋዴዎች የአቶ ከተማ ከበደ፣ የእነ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ የአቶ ጌቱ ገለቴና ሌሎችም ክስ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ቀርቧል፡፡
በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ የታሰሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆና ሌሎችም ተከሳሾች ክስም እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ የታሰሩት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልና ሌሎችም ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡