Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሰባት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው

በሰባት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው

ቀን:

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያደጉ አገሮች በሽታዎች ናቸው ተብለው ሲወሰዱ የቆዩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እነዚህ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ ኅብረተሰቡን እያጠቁ ነው፡፡ የሥርጭት መጠናቸውም በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ መካከል አንዱ ካንሰር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው የጡት ካንሰር ነው፡፡ ይህም ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቃ ያለ በሽታ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ሲምፖዚየምን አስመልክተው፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ሕክምና ኃላፊ ዶ/ር ማኅተመ በቀለ እንደገለጹት፣ የጡት ካንሰር ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ የሚስችል በብሔራዊ ደረጃ ምዝገባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ምዝገባው የሚገልጸው መረጃ ትክክለኛ እንደሚሆን፣ ነገር ግን አሁን ባለው መረጃ መሠረት 34 በመቶ ያህሉ የሴቶች የጡት ካንሰር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

የጡት ካንሰር የያዛቸው ሴቶች ዘግይተው ነው? ወይስ ቶሎ ነው ወደ ጤና ተቋም የሚመጡት የሚለውን ለማወቅ በየተቋማቱ የተሠሩት የዳሰሳ ጥናቶች ተከልሶ ሲታይ እስካሁን ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሦስተኛና አራተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር ሲሆን ቆይተው የሚመጡት ናቸው፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር የሚመጣው በጣም ጥቂት ነው፡፡ እርግጥ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ነገር ሰዎች በጡት ካንሰር መያዛቸውንና አለመያዛቸውን ለማወቅ የሚያስችላቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ማካሄድ ግድ ይላል፡፡ በተረፈ አጋላጭ ሁኔታዎቹ ሴት መሆኑንና ጡት መኖሩ በራሱ አጋላጭ ሁኔታ ነው የጡት ካንሰር ወንዶችም ላይ እንደሚከሰት፣ በፊት አንድ በመቶ ብቻ የነበረው አሁን ወደ አራት በመቶ ከፍ ብሏል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡

ራስን ለመከላከል ረገድም በመጀመርያ ጡትን በመደባበስ ካንሰር መከሰት አለመከሰቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ በዚህም ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሰፊው እንደተያዙት ከዶ/ር ማኅተመ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹ከሆርሞንና ከዕድሜ አንፃር የሚመጡ አጋላጭ ሁኔታዎች እሉ፡፡ በየትኛው ዕድሜ ማን ተጋላጭ እንደሚሆን ለሰዎች ማስተማር፣ እንዲያውቁትም ማድረግ ይገባል፡፡ ለበሽታው የተዳረጉ ሰዎችንም መጀመርያ መለየት፣ ከፍተኛ ሪስክ ያለባቸውን ሰዎች ከዚያ በኋላ በአንደኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ያሉትን ደግሞ በቶሎ ማከም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የካንሰር ሐኪሞች በብዛት እንደሌሉ፣ ይህም ሆኖ ግን የጡት ካንሰር በአብዛኛው የሚታከመው በቀዶ ሕክምና ሐኪሞች እንደሆነ፣ በተለይ በሽታው ቶሎ ከተደረሰበትና ቀዶ ሕክምና ከተሠራ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ፣ ለዚህም የቀዶ ሕክምና ቁጥሩ በጥሩ ሁኔታ እየጨመረና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በያዘው ስትራቴጂ መሠረት የቀዶ ሐኪሞች ቁጥር በፊት ካለው ምናልባትም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በጣም እጅግ ብዙ እንደሚሆን ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

በጋዜጣው መግለጫው ላይ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የካንሰርን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአምስት ዓመት ብሔራዊ የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር መርሐ ግብር በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን አውስተው፣ በዚሁም ካንሰር መከላከልን ማዕከል በማድረግ፣ በወቅቱ በምርመራ የመለየት፣ የማከምና የማገገም አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የማኅፀን በር ጫፍ ቅድመ ካንሰር ልየታና ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለማስፋፋት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ወደ 200 ጤና ተቋማት አገልግሎትን እየሰጡ ናቸው፡፡ ይህን አገልግሎት በሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስና አስፈላጊውን የሕክምና መሣሪያ ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንም ወ/ሮ ሮማን ተናግረዋል፡፡

በአንድ ማዕከል ብቻ ተወስኖ የነበረውን የጡት ካንሰር ምርመራና ሕክምና አገልግሎት ባልተማከለ ሁኔታ ለመስጠት እንዲቻል የጡት ካንሰር ምርመራና የመድኃኒት ሕክምና አገልግሎት ወደ 12 ሆስፒታሎች እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ የተካሄደውም ሲምፖዚየም ይህን አገልገሎት ለማሻሻል የሚረዱ የልምድ ልውውጥና ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አቀማመጥ መሠረት ያደረገ በአዲስ አበባ የጥቁር አንበሳና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በሰባት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ማዕከላትን በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ አገልግሎቱንም በሰው ኃይል አጠናክሮ ለመጀመር በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡  

አዲሷ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰህርላ አብዱላሂ የጡት ካንሰር የያዛቸው ሴቶች ቶሎ ብለው ወደ ሕክምና ተቋም እንዲመጡ ሰፊ ማስገንዘቢያ ሊሠራ እንደሚገባ  አሳስበው፣ በአዲስ አበባና በየክልሉ የጡትና የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ በነፃ እንዲካሄድ ሁኔታ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡   

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ የተካሄደው ይኼው ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ሲምፖዚየም ዋና ዓላማ በአፍሪካ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን የጡት ካንሰር ሕክምናን በማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሲምፖዚያሙ ላይ የአሥር አገሮች ተሞክሮና ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...