ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የመጀመርያው የአገር መሪ በመሆን ለሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙትን የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን፣ ዓርብ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በታላቁ ቤተ መንግሥት ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ሐሙስ ዕለት ምሽት አዲስ አበባ ሲገቡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ዓርብ ዕለት በታላቁ ቤተ መንግሥት በተደረገ ይፋዊ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ደግሞ፣ ለፕሬዚዳንቱ ክብር ሰባት ጊዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡
የይፋዊ አቀባበል ሥነ ሥርዓቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ የሁለትዮሽ፣ እንዲሁም ባለ ብዙ ፈርጅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የደረሷቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት ላይ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሁለቱ አገሮች ከዚህ ቀደም የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ የተፈራረሟቸውን 20 የሚሆኑ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት፣ በአኅጉሪቱ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ መንገድ ለመሥራት፣ የአፍሪካ ኅብረት የተሃድሶ አጀንዳዎችን ማስፈጸምና የፓን አፍሪካ እሴቶችን በአኅጉሪቱ ለማስፋፋትና ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያ ከላከቻቸው የሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ ከዓመታት በኋላ ከሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ጋር በተለየ ደረጃ ተገናኝተዋል፡፡
ሩዋንዳ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከተፈችው በ1970 ዓ.ም. ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ኤምባሲዋን በሩዋንዳ የከፈተችው አምና ነበር፡፡ በሩዋንዳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው የከፈቱት ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ነበሩ፡፡