Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀል አምራቾች ብሔራዊ ባንክ እነሱን ያገለለ ለውጭ ኩባንያዎች ብቻ የሚስማማ መመርያ ተግባራዊ ማድረጉን ተቃወሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ፍንራኮ ቫሉታና ሌሎችም ማበረታቻዎች እንዲሰጣቸው ጠየቁ

የቤት ክዳን ቆርቆሮ በኮንትሮባንድ እንደሚገባም አስታውቀዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከመስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ መመርያ፣ አገር በቀል አምራቾችንን ያገለለና የውጭ ባለሀብቶች እንደ ልባቸው ጥሬ ዕቃና ሌሎችም ግብዓቶችን ማስገባት እንዲችሉ የሚያስችላቸው ነው ሲሉ የአገር ውስጥ አምራቾች ተቃውሞ አሰሙ፡፡ በመመርያው መደናገጣቸውን በመግለጽ ጭምር አቤቱታቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር ተጠሪ በሆኑ ተቋማትና በዘርፉ ተዋንያን የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች አማካይነት ከሐሙስ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ መካሄድ የጀመረውን ዓውደ ርዕይ ከከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በተደረገ ውይይት ወቅት፣ የአገር ውስጥ አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች በማኅበሮቻቸው በኩል አሰምተዋል፡፡ ከማኅበራቱ ጥያቄዎች ቀደም ብሎም የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ስለሚታዩ ችግሮች ያስጠናው ጥናትም ቀርቧል፡፡

ከመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንስዱትሪዎች ማኅበር፣ ከኬሚካልና ኮንትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ከፈርኒቸር፣ ከፕላስቲክና ጎማ፣ ከአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ከኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ማኅበራት የተውጣጡ ተወካዮች በአብዛኛው በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በጥሬ ዕቃ ዕጦት፣ በመንግሥት ፖሊሲና በአስተዳደራዊ በደል ላይ ያጠነጠኑ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን አሰምተዋል፡፡

የመሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂንሪንግ ኢንዱስትሪዎችን በመወከል የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ፣ ከ70 በላይ ኢንዱስትሪዎች የተወከሉበትን የማኅበሩን ጥያቄዎችና ቅሬታዎች በንባብ አሰምተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከወራት በፊት ያወጣውና በአሁኑ ወቅትም መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገበት የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ግዥ (ሰፕላየርስ ክሬዲት) የውጭ ብድር አቅርቦት መመርያ፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያገለለ በመሆኑና የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን ላኪነትና የውጭ አልሚ መሆንን በጥቅሉ በመሥፈርትነት ማስቀመጡ አጠያያቂ አሰኝቶታል፡፡

ማኅበሩ ባቀረበው መሠረት በውጭ አገር አልሚነት ወይም የውጭ ኩባንያዎች ተብለው የተጠቀሱት፣ ነገር ግን ለአገር ውስጥ ገበያም ጭምር የሚያመርቱም ሆነው ሳለ መመርያው ግን የአገር ውስጥ አልሚዎችን በዚህ አግባብ አለማካተቱ፣ ‹‹የአገር ውስጥ አምራቾችን በማግለል ለኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር የሚዳርግ አደገኛ ዕርምጃ ነው፤›› በማለት፣ የማኅበሩን አቋም ለመንግሥት አስታውቀዋል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መንግሥት ለአገር ውስጥ አምራቾች ልዩ ድጋፍና ትኩረት እንደሚያደርግ ካስቀመጠው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ጋር የሚረር በመሆኑ፣ የባንኩ መመርያ አገር በቀል አምራቾችንም እንዲያካትት በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ ለግንባታ ሥራዎች የሚውሉ ምርቶች ዓመታዊ የማምረት አቅም አምስት ሚሊዮን ቶን እንደ ደረሰ ያስታወቀው ማኅበሩ፣ በግንባታው ዘርፍ ያለው ዓመታዊ ፍላጎትም ሦስት ሚሊዮን ቶን እንደሚገመት ጠቁሟል፡፡ ሆኖም በተለይ የብረታ ብረት አምራቾች ከገነቡት የማምረት አቅም ውስጥ የ20 በመቶውን ብቻ ለማምረት እንደቻሉና ይህም ግብዓት ከውጭ ለማምጣት በመቸገር ሳቢያ የተከሰተ ስለመሆኑ ተገልጾ፣ ከውጭ የሚገባው ያለቀለት ምርት ግን 60 በመቶ እንደሚደርስና ከአገር ውስጥ ማቅረብ የተቻለው ግን 40 በመቶ ብቻ መሆኑ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡትን ፋብሪካዎች ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተ አኳኋን እየታየ ነው በማለት ማኅበሩ አስጠንቅቋል፡፡ 

አገር በቀል የጋልቫናይዝድ ኢንዱስትሪዎች የሚፈጥሩትን የምርት እሴት ከግምት ያለስገባና ከውጭ ከሚገባ ያለቀለት ምርት እኩል የሚያደርግ ‹‹ኢፍትሐዊ የገቢ ዕቃዎች ታሪፍ›› እየተተገበረ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ መንግሥት ይህንንም ያሻሽል ዘንድ ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡ በማኅበሩ አደገኛ ተብሎ የተጠቀሰው የዘርፉ ሌላኛው ችግር የቆርቆሮ የቤት ክዳን በኮንትሮባንድ በገፍ እየገባ መሆኑን በማስታወቅ ነበር፡፡ በማኅበሩ በኩል አደገኛ እንደሆነና የጣራ ክዳን አምራቾችን ህልውና የሚፈታተን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲገታ፣ ቁጥጥሩም እንዲጠናከር ተጠይቋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ጭምሮ 11 ያህል ጥያቄዎችና ማስተካከያዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዲስትሪ ማኅበር በኩል ቀርበዋል፡፡

ሌሎቹም ማኅበራት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ መንግሥት በሚፈጽማቸው ግዥዎች ውስጥ ለአገር ውስጥ አምራቾች የ15 በመቶ ብልጫ ይሰጣል የሚለው ሕግ በአግባቡ እንደማይተገበር፣ በአገር ውስጥ የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች እያሉ ከውጭ ማስመጣት፣ በአገር ውስጥ የተመረቱ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችና ማስዋቢያዎች እያሉ ለውጭ ቅድሚያ መስጠት፣ በጨረታ ሰነድ ውስጥ ሳይቀር እነዚህ ቁሳቁሶች የተሠሩባቸው አገሮች በስም እየተጠቀሱ እንዲቀርቡላቸው ማስታወቂያ የሚያስነግሩ የመንግሥት ተቋማት በርካታ ስለመሆናቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) እንዲያውቁት አድርገዋል፡፡

በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አማካይነት በየነ ታደሰ (ዶ/ር) በተባሉ ባለሙያ የተደረገው ጥናትም፣ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ የአገሪቱን የንግድ ባንኮች የወረፈ ነበር፡፡ እንደ አጥኚው ምልከታ ከሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ የሚያከፋፍልበት፣ አቅርቦቱን የሚያስተዳደርበትና የሚከታተልበት አሠራር ግልጽነት የጎደለውና አብዛኛው ሕዝብ ሊረዳው የሚችል እንዳልሆነ ተችተዋል፡፡

ምንም እንኳ ጽሑፍ አቅራቢው በአገሪቱ የሚታየው የግብዓት ወጪ፣ ለካፒታል ዕቃዎችና በከፊል ላለቀላቸው ዕቃዎች ግዥ ከሚጠየቀው የውጭ ምንዛሪ አኳያ ዝቅተኛ ድርሻ ቢኖረውም፣ ረዥም ጊዜና መዘግየት የሚታበት በመሆኑ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ይላሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2016 በነበሩት ዓመታት ውስጥ ለጥሬ ዕቃ ግዥ የተጠየቀው የውጭ ምንዛሪ 1.2 በመቶ ብቻ ሲሸፍን፣ ለካፒታል ዕቃዎች የ30 በመቶ፣ እንዲሁም በከፊል ላለቀላቸው ዕቃዎች መግዣ ከ16 በመቶ በላይ መሸፈኑን አጣቅሰዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ በመስጠት ይስተናገዳል ቢባልም ይህ በአግባቡ አይተገበርም ያሉት አጥኚው፣ የንግድ ባንኮችም ቢሆኑ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የማበደር ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ ካበደሩም እስከ 16 በመቶ የብድር ወለድ ስለሚስከፍሉ፣ እንዲህ ያለው የብድር ወለድ የትኛውንም አምራችና ነጋዴ እንደማያዋጣ በመኮነን እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት ሊያሻሽላቸው ይገባል ካሏቸውና የመፍትሔ ሐሳብ በማለት ካቀረቡባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በልዩ ሁኔታ የፍራንኮ ቫሉታ አሠራር እንዲያመቻችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚጠይቀው ይገኝበታል፡፡ በዚህ አግባብ አስመጪዎች በራሳቸው መንገድ በውጭ ምንዛሪ ዕቃዎችን ማስገባት እንዲችሉ የሚፈቅድ አሠራር ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ በሚከተለው የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ አሠራር ግን አስመጪዎች ለሚያመጡት ዕቃ የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ መጠን ማስመዝገብ (በራሳቸው መንገድ ከውጭ አበዳሪዎችም ቢያገኙት) ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ካሉት መጠይቆች ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች በራሳቸው መንገድ ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚያስፈልጋቸውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ከቻሉ፣ በብሔራዊ ባንክ በኩል የግድ ማስመዝገብና ማስፈቀድ የሚለው መጠይቅ ቀለል እንዲልላቸው መደረጉ ተሰምቷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአምራቾቹን ጥያቄዎች ካዳመጡ በኋላ አመጣጣቸው ዓውደ ርዕዩን ከፍተውና የመንግሥትን መልዕክት አስተላልፈው ለመሄድ እንደነበር ሳይሸሽጉ ገልጸው፣ ሆኖም የቀረቡላቸው ጥያቄዎች እንዲህ በድንገት በተገኙበት የውይይት መድረክ የሚፈታ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ ወደፊት የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በስፋት የሚዳስስ የውይይት መድረክ በመጥራት፣ የተነሱት ችግሮች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት የሚደረግበትን ዕድል ለማመቻቸት ቃል ገብተዋል፡፡ ምንም እንኳን በመድረኩ እንደሚገኙ ሲጠበቁ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቢሆኑም፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ መደሰታቸውን አምራቾቹ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች