በውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና አመዳደብ ችግር ምክንያት አዲስ አበባ ከተማ ከአንድ ዓመት በኋላ ከበድ ያለ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር ሊገጥማት ይችላል ተባለ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 46 ሚሊዮን ዶላርና ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲቀርብለት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳልተሰጠው አስታውቋል፡፡
ሊከሰት ለሚችለው የውኃ እጥረት መነሻው የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የጀመራቸውን የውኃ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የጠየቀው የውጭ ምንዛሪ ምላሽ ሳያገኝ አንድ ዓመት በማስቆጠሩ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የከተማውን የውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ በተለይ ሁለት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክትና የአያት ፈንታ የጥልቅ ጉድጓድ ፕሮጀክት ናቸው፡፡ በተለይ የለገዳዲ ፕሮጀክት በሰሜን አዲስ አበባ ያለውን ፅኑ የውኃ ችግር ይፈታል ተብሎ የተጀመረ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በቀን 86 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ የማመንጨት አቅም አለው፡፡
ይኼ ፕሮጀክት አራት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ የሲቪል ሥራዎች ተጠናቀው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን ለመገግዛት የውጭ ምንዛሪ ተጠይቆ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአያት ፈንታ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት በቀን 68 ሺሕ ሜትር ኩብ ውኃ የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ የሲቪል ሥራዎች ተጠናቀው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ ተጠይቆ ነበር፡፡
እነዚህን ሁለት ፕሮጀክቶች ጨምሮ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለውኃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች የጠየቀው፣ 46 ሚሊዮን ዶላርና ስድስት ሚሊዮን ዩሮ መሆኑ ታውቋል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አመዳደብ ለሰው ልጆች ሕይወት መሠረት ለሆነው ውኃ ከማድላት ይልቅ፣ እምብዛም ረብ ለሌላቸው ከረሜላና አልኮል መጠጦችን ለመሳሰሉ ሸቀጦች መሆኑ እንዳሳዘናቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች በዚህ ወቅት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመት በፊት የተጠየቀ የውጭ ምንዛሪ እስካሁን ምላሽ ባለማግኘቱ የለገዳዲ ፕሮጀክት ኮንትራክተር የዋጋ ንረት ልዩነት መጠየቁ ታውቋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ውኃው ወደ ሥርጭት ቢገባ የከተማው ውኃ አቅርቦት የመሻሻሉን ያህል ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ በተለይ ከአንድ ዓመት በኋላ ከበድ ያለ የውኃ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የማያውቁ የከተማው ባለሥልጠናት ከወዲሁ ሥጋት እንደገባቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡