Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአቶ አንዳርጋቸው ጽጌና እነ አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ 771 ሰዎች ከእስር ተፈቱ

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና እነ አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ 771 ሰዎች ከእስር ተፈቱ

ቀን:

ይቅርታ ለማድረግና ክስ ለማቋረጥ መሥፈርቱ ምን እንደሆነ አልተገለጸም

በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት ሰባት ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት እነ አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ፣ 771 ተከሳሾችና ፍርደኞች በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ከእስር እንዲፈቱ ተደረገ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ቅዳሜ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ በሽብር ወንጀል ተከሰው የነበሩ 137 ግለሰቦች፣ አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ ዓለማየሁ ጉጆና አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤልን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 31 ግለሰቦች፣ በልዩ ሁኔታ የ27 ሰዎችና የአራት ድርጅቶች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሥርቶባቸው የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው የነበሩ 576 ሰዎች ይቅርታ እንደተደረገላቸውም አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት አድርጎ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን በሚመለከት ኅብረተሰቡ ሲያነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ቅሬታዎችን በመመልከት፣ ከላይ የተጠቀሱት ተከሳሾችና ፍርደኞች ክሳቸው እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ መደጉን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተከሳሾች ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንደሆነ፣ ፍርድ ያረፈባቸውም ለይቅርታ ቦርድ ቀርቦና በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ውሳኔ ተሰጥቶበት መሆኑንና በአዋጁም በልዩ ሁኔታ እስረኞችን መልቀቅ እንደሚቻል በመደንገጉ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የግንቦት ሰባት ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አንዳርጋቸው፣ በሽብር ወንጀል ሁለት ጊዜ ክስ ተመሥርቶባቸው በዕድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከዱባይ ወደ አስመራ ለመሄድ የመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በፀጥታ ሰዎች ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በቀጥታ ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ተወስደው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስረው ላለፉት አራት ዓመታት ያህል ቆይተዋል፡፡ ከእስር እንዲፈቱ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ግፊቶች የነበሩ ሲሆን፣ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት ትዕዛዝና የሥራ አቅጣጫ መሠረት፣ ዓርብ ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ይቅርታ ተደርጎላቸው ከእስር መፈታታቸው ታውቋል፡፡

በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው ላለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኙት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና በሕግ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ የሁሉም ተከሳሾች ክስም ተቋርጧል፡፡

በሦስት የተለያዩ የክስ መዝገቦች ክስ ተመሥርቶባቸው በሁለቱ መዝገቦች ጥቂት ተከሳሾች በነፃ ሲሰናበቱ፣ አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በአንድ፣ በሁለትና በሦስት ክሶች ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት፣ ፍርድ ቤቱ ለማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ በሌላ አንድ መዝገብም ጥፋተኛ ለማለት ወይም በነፃ ለማሰናበትም በተመሳሳይ ቀን ቀጠሮ ተይዞ ነበር፡፡   

በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ክስ የመመሥረትና ክስ የማቋረጥ ሥልጣን የተሰጠው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ጉዳዩን በጥልቅ በመመርመር የክስ መዝገቡን ማቋረጥ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ክሳቸው እንዲቋረጥ፤›› በማለት፣ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦ ክሱ እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡

በመሆኑም በእነ አቶ መላኩ የክስ መዝገብ የተካተቱት፣ አቶ ገብረ እግዚአብሔር ነጋ፣ አቶ ከተማ ከበደ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ክሳቸው ሲታይ የነበሩት አቶ ጌቱ ገለቴ (በሌሉበት)፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ (የአቶ ገብረ ዋህድ ባለቤት)፣ የኢሊሊ ሆቴልና የገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት አቶ ገምሹ በየነ (በሌሉበት)፣ አቶ ፍፁም ገብረ መድኅን፣ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጌትአስ ኩባንያ፣ ኮሜት ትሬዲንግ ሐውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበርና ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በሌላ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸውና በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸው በመገናኛ ብዙኃን በወቅቱ በነበሩት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ተነግሮ በቁጥጥር ሥር የዋሉትና ክስ የተመሠረተባቸው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ዋስይሁን አባተ፣ አቶ አክሎግ ደምሴ፣ አቶ ዘርፉ ተሰማ፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ ወ/ሮ ስህን ጎበና፣ አቶ ጌታቸው ነገሪ፣ አቶ ነጋ መንግሥቱ፣ አቶ ሙሳ ሙሐመድ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ (ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት)፣ ኮሎኔል መላኩ ደግፌ፣ ትርሲት  ከበደ፣ አቶ ገዛኸን ኢጀራ፣ ቤዛዓለም አክሊሉ፣ አቶ ወንድሙ መንግሥቱ፣ አቶ ቢልልኝ ጣሰውና ማኅደር ገብረሃና ክስም እንዲቋረጥ ተጠይቆ ተቋርጧል፡፡

ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ስለተቋማቸው የሥራ ተግባርና ክስን ለማቋረጥ በአዋጅ ሥልጣን እንደተሰጠው ጠቁመው፣ ከላይ የተጠቀሱት 771 ግለሰቦችና አራት ድርጅቶች ክስ እንደተቋረጠና በይቅርታ እንደተፈቱ ከገለጹ በኋላ፣ ማስተናገድ የሚችሉት አንድ ሦስት ጥያቄዎችን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ሰዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም፣ 31 ግለሰቦችን ብቻ ለይቶ መፍታትና በቅርቡ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ላይ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ምዝበራ ተጠርጥረው ክሳቸው እየተካሄደ ቢሆንም፣ የተወሰኑ ከሁለት ተቋማት ብቻ የተመረጡ ሰዎች በክስ ማቋረጥ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገው እንዴት እንደሆነና የመለያ መሥፈርቱ ምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

አቶ ብርሃኑ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፣ መፍትሔው ማሰርና መቅጣት ሳይሆን መፍትሔ የሚመጣበትን መሥራት ነው፡፡ ‹‹በሙስና ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው የተከሰሱት? ከ90 በላይ ክስ ተመሥርቶ በአንድና በሁለት ጉዳዮች ብቻ ክርክር ይካሄዱባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ወደፊት ሙስና እንዳይፈጸም መከላከል፣ ድርጊቱ ከተፈጸመም ከመታሰራቸው በፊት በሚስጥርም ይሁን በሌላ መንገድ ማስረጃ ሰብስቦ ከተረጋገጠ በኋላ መጠየቅ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ እየያዙ ማሰር ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ፣ በትልልቁ ላይ ትኩረት ተደርጎ ካልተሠራ በሽርፍራፊው ላይ ብቻ ትኩረት መስጠት ጥቅም እንደሌለው አክለዋል፡፡

የሽብር ተግባር ወንጀል ተከሳሾችን በሚመለከት በአንድም በሌላ ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ መሆኑን ጠቁመው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት ሕግና ሕግን ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ይቅርታው ቀጣይነት እንዳለውና እንደሌለው ተጠይቀው ‹‹ይቀጥላል፣ ግን መብት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ክስ ተቋረጠ ማለት ወንጀል ወይም ጥፋት የለም ማለት አለመሆኑን አቶ ብርሃኑ ጠቁመው፣ የተቋረጠ ክስ ሊንቀሳቀስ እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ተጠርጣሪዎቹን ጭምር በማሳየት የመንግሥትንና የሕዝብን ሀብትና ገንዘብ መውሰዳቸውን የገንዘቦቹ ዓይነትና መጠን ተገልጾ፣ በርካታ ይዞታዎችም መኖራቸውን የሚያረጋግጡ ሰነዶች ታይተው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የፕሮጀክቶቹ ስም እየተጠቀሰ ለግለሰቦች ጥቅም መዋሉና ሌሎችም ማስረጃዎች ቀርበው እያለ፣ ክስን ማቋረጥ በቀጣይ ለኅብረተሰቡ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብርሃኑ፣ ምላሽ ሳይሰጡበት መግለጫቸውን አጠናቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...