ግድያና ኢሰብዓዊ የወንጀል ተግባር ከፈጸሙ ተከሳሾችና ፍርደኞች በስተቀር፣ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተከሰውና ፍርድ አርፎባቸው ለነበሩ 9,817 ተከሳሾች የትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች መንግሥታት ይቅርታ አደረጉ፡፡
በትግራይ ክልል መንግሥት ይቅርታ የተደረገላቸው 2,206 ታራሚዎች ሲሆኑ፣ 45 ሴቶች መሆናቸውን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋና የክልሉ የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ ተናግረዋል፡፡
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት የተፀፀቱና ሥነ ምግባራቸው የተስተካከለ መሆኑ መረጋገጡን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ለ7,611 ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል፡፡ ይቅርታ ከተደረገላቸው ውስጥ 7,183ቱ ወንዶች ሲሆኑ፣ 428 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሥርቶባቸውና ተፈርዶባቸው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መታረማቸውና በሠሩት የወንጀል ተግባር መፀፀታቸው እየታየና እየተረጋገጠ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡