ሁሌም ጥሎብኝ የሴቶችን መማር፣ ማደግና ስኬት በእጅጉ እከታተላለሁ፡፡ በዚህ ዘመን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ አባባልም እየተፈጠረ ነው፡፡ ‹‹ሴትን ልጅ በማስተማር ታላቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ይቻላል፤›› ነው የሚባለው፡፡ በእርግጥም እኔም ይኼንን ውብ አባባል እጋራዋለሁ፡፡ በተለይ ድህነት የሰፈነባት አገር ውስጥ ሴት ልጅ ለውጤት የሚያበቃት ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል፡፡ ሴትን ለመጥቀም ብቻ ሲባል የሚደረገውን ከንቱና ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ድጋፍ ግን በፍፁም እቃወማለሁ፡፡ ለግለሰብም ለአገርም ጠቃሚ ስላልሆነ፡፡ በተለይ በሴቶች መብት ስም ራሳቸውን የሚኮፍሱና የባዕድ አጀንዳ የሚያቀነቅኑ ‹ፌሚኒስቶች› እንደ ቅንቅን ይኮሰኩሱኛል፡፡ ጭቁን ሴቶችን የሚፀየፉ አስመሳዮች በእነሱ ስም እየበለፀጉ፣ በሌላ ወገን የፈረንጅ አጀንዳ እያራገቡ ይመፃደቃሉ፡፡
ይኼንን የማምንበትን አስተያየት ዘወትር ከጓደኞቼ ጋር እነጋገርበታለሁ፡፡ አንዳንዶች ይኼንን ርዕስ ለምን እንደማተኩርበት እንዳስረዳቸው ይጨቀጭቁኛል፡፡ ሌሎች ደግሞ በዚህ አቋሜ ምክንያት የሴት መብት አቀንቃኝ አድርገው ያዩኛል፡፡ ፅንፈኛ አቋም ያላቸውና ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር መራመድ ያቃታቸው ደግሞ የሴቶች ጉዳይ እንዳይነሳ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ የሚያንቋሽሹ አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የሴቶች ጉዳይ በጠባብ ሥነ ምኅዳር ውስጥ ሳይሆን በሰፊው ዓለም የመወያያ አጀንዳ ስለሆነ፣ የእነዚህኞቹ ተራ ሙግት አያሳስበኝም፡፡ የሚያናድዱኝ በሴቶች መብት ማስጠበቅ ስም ራሳቸውን ፋኖ ያደረጉ ነገር ግን በተግባር የሌሉበት ናቸው፡፡
በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንነጋገርና ሴቶች ለምን የባንክ አስተዳዳሪዎች አይሆኑም? ሴቶች ለምን የጦር ኃይል አዛዥ አይሆኑም? ሴቶች ለምን በብዛት በዲፕሎማትነት አይሠማሩም? ኧረ ለመሆኑ ሴቶች ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን አይሆኑም? ይኼ ሁሌ የሚከነክነኝ ጉዳይ ነው፡፡ ወደፊት በብዛትና በጥራት የምናስተምራቸው ሴቶች ይኼንን ያሳኩታል ብዬ አምናለሁ፡፡ የወንዶች የበላይነት በሰፈነበት አገር ውስጥ ጥቂት ሚኒስትሮች ብቻ ማየት ያስከፋል፡፡ ሴቶች ለአገር መሪነት ከወዲሁ ቢታጩ ይበጀናል፡፡ በወንዶች አልሳካም ያለው አዝጋሚው ፖለቲካ ራሱ በሴቶች ቢመራ ምን ይመስላችኋል?
እንዲህ ዓይነቱን በጎ ምኞች በውስጤ እያብሰለሰልኩ ሳለሁ አንድ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ልትጠይቀኝ ቢሮዬ መጣች፡፡ እንግዳዬን ምሳ ለመጋበዝ መሥርያ ቤቴ አካባቢ ያለ ምግብ ቤት ይዣት ሄድኩ፡፡ ምሳችንን እየበላን ሳለ የተለመደው የሴቶች ጉዳይ ተነሳ፡፡ ጓደኛዬ የእኔን ስሜት በጣም ስለምትረዳ የሴቶችን ጉዳይ ቀድማ ያነሳችው እሷው ናት፡፡ በዚሁ የሴቶች የሥልጣን ጥያቄ ዙሪያ አንድ ሁለት ስንባባል ከቆየን በኋላ ሰሞኑን አንድ ጭምጭምታ መስማቷን ነገረችኝ፡፡ ሁለመናዬ አዲሱን ወሬ ለመስማት ሲል ብቻ ጆሮ ሆነ፡፡ ይኼንን የተረዳችው ጓደኛዬ አዲሱን ጭምጭምታ እንዲህ ነገረችኝ፡፡
‹‹የሚቀጥለው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን ታውቃለህ?›› በማለት በጥያቄ ጀመረች፡፡ ‹‹ኧረ እኔ እንጃ?›› አልኳት፡፡ ‹‹የወደፊቷ ፕሬዚዳንት ሴት ናት፤›› ስትለኝ በደስታ ከመቀመጫዬ ብድግ አልኩ፡፡ ‹‹ተረጋጋ እባክህ! ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመርያዋን የሴት ፕሬዚዳንት ሳታገኝ አትቀርም፡፡ ይህም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዕውን ይሆናል፤›› ስትለኝ ልቤ ደስ አለው፡፡ ይህቺ ጓደኛዬ በግምት ማውራት አትወድም፡፡ ስለዚህ እኔ በደስታ ጮቤ ብረግጥ አይፈረድብኝም፡፡ ያም ሆነ ይህ የወደፊቷ ፕሬዚዳንታችን ማን ናት ብሎ መጠየቁ አይከፋም፡፡ ጓደኛዬ ለጊዜው ስም አይጠራም ብላኝ ወጓን ቀጠለች፡፡
‹‹ስም መጥራት ክልክል ነው፡፡ ይህች ወይዘሮ ግን ለቦታው ብቁ መሆኗን አልደብቅህም፡፡ ምንም እንኳን ብዙዎች ግራ ሊገባቸውና ለማመን ቢቸገሩም ለዚህኛው ሥራ ግን ትመጥናለች ተብሎ በሚገባ ይታመንባታል፤›› ስትለኝ፣ እኔም ጆሮዬን ሰጥቼ ከማዳመጥ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ‹‹ስለዚህ ይህች ወይዘሮ ፕሬዚዳንት የመሆን ተስፋ አላት?›› ስላት፣ ቀልድ የማታውቀው ጓደኛዬ፣ ‹‹ምናልባት ካስፈለገም ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ዕድል አላት፤›› በማለት ኮስተር ስትልብኝ፣ ‹‹ሹመት ያዳብር፤›› ብዬ ምሳዬን መብላቴን ቀጠልኩ፡፡ ውድ እህቶቼ በባዕዳን በጀትና አጀንዳ የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር ሳያመጡ በከንቱ የሚያደርቋቸሁን ‹ፌሚኒስት› ተብዬዎችን ጆሮ ዳባ ብላችሁ፣ ትኩረታችሁን ሁሉ ትምህርትና ክህሎት ማዳበር ላይ አድርጉ፡፡ ነፃ የሚያወጣችሁና ለታላቅ ክብር የሚያበቃችሁ ኢትዮጵያዊ ማንነታችሁና ጥረታችሁ ብቻ እንደሆነ አውቃችሁ፣ ከፈረንጅ ጥገኛ አስተሳሰብ አሸካሚ ፌሚኒስቶች ራቁ፡፡ እኩልነት በሥራ እንጂ በመፈክር ጋጋታ ወይም በደመነፍሳዊ መወራጨት አይገኝም፡፡
(መርዕድ መንግሥቴ፣ ከአራት ኪሎ)