Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው ከሥልጣናቸው መቼ እንደሚወርዱ አይታወቅም››

አቶ ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር)፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

አቶ ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር) በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሲቪል ኢንጂነሪንግ ከዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ወስደዋል፡፡ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ቢዝነስ ከግሪኒውች ዩኒቨርሲቲ የወሰዱ ሲሆን፣ በሥራው ዓለም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማማከር አገልግሎት ላይ ናቸው፡፡ በይበልጥ ግን በተለያዩ ማኅበራት ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ የመጀመርያው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበር መሥራችና የቦርድ አባል ናቸው፡፡ የኮንትራክተሮች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አማካሪ ቦርድ ምክር ቤት አባል፣ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል ሆነው ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡ በሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ላይም አገልግለዋል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የተመሠረተውና ለመንግሥት በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ የሚታወቀው፣ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሕዝባዊ ምክክር (ቲንክ ታንክ) የምሁራን ፎረም መሥራችና ሊቀመንበር በመሆን እያገለገሉ ነው፡፡ በቅርቡ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭትን ለመሸምገል የተቋቋመው የሽማግሌዎች ኅብረት አስተባባሪ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሊቀመንበር በመሆንም በማገልገል ላይ ሲሆኑ፣ ሰሞኑኑ ደግሞ አምስት የአሠሪዎች ፌዴሬሽኖች በጥምረት የፈጠሩት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በ30 ምሁራን ስብስብ በተቋቋመው ፎረም እንቅስቃሴና አዲስ በተቋቋመው የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፎረማችሁ ለመንግሥት የፖሊሲ ሐሳቦችን በማቅረብና ተፈጻሚ እንዲሆን  በመሳተፍ ይታወቃል፡፡ ይህንን ዓብይ ጉዳይ ይዛችሁ ምን ያህል ተንቀሳቅሳችኋል? በእርግጥ ያሰባችሁትን ማድረግ ችላችኋል? ፎረማችሁ ሠርቷል ብለው ሊጠቅሱልኝ የሚችሉዋቸው ተጨባጭ ሥራዎች አሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ትልልቅ ሊባሉ የሚችሉ ሥራዎችን ነው የሠራው፡፡ በዋናነት ለመንግሥት የፖሊሲ ሐሳቦችንና አማራጮችን በማቅረብ ለአገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ በቀላሉ የሚተነተን አይደለም፡፡ በትንሹ ብንጀምር እንኳን መጤ ባህል እየፈጠረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ የሠራነው ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በመጤ ባህል ኅብረተሰባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በመረዳትና ይህንንም በማጥናት የመፍትሔ ሐሳቦች አቅርበናል፡፡ መጤ ባህል የእኛ የምንለውን ባህላችንን በርዟል፡፡ ወጣቶችን ወደ ሱስ በማስገባት ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የራቁት ዳንስ በየቦታው መታየቱ ገጽታችንን የሚያበላሽ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ ትልቅ ሲምፖዚየም አዘጋጅተን መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ አሳስበን ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ግን ዕርምጃው ያዝ ለቀቅ በመሆኑ ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው እንቅስቃሴያችን ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት የሚመለከት ነው፡፡ ዋጋ ተወደደ ተብሎ መንግሥት ነጋዴዎችን ያስር ነበር፡፡ ሸሽጋችሁ አከማችታችኋል በማለት የሚያስራቸው ነበሩ፡፡ ይህ አካሄድ አያዋጣም ብለን ሊሆን የሚገባውን ሐሳብ አቅርበናል፡፡ መንግሥት ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ያቅርብ፡፡ ይህ ሲሆን ሸሽጎ ያከማቸ ሁሉ ያወጣል የሚሉና ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመንግሥት በማማከራችን፣ እነዚህ ነገሮች ተግባራዊ ሆነው የኑሮ ውድነት የሚቀረፍበት አሠራር ተፈጥሮ ለተወሰነ ጊዜ ጥሩ እየሄደ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለይ ትልቅ ሥራ የሠራነው ከዛሬ አንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር አካባቢ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ችግር ላይ ነው፡፡ በየቦታው የንብረት መቃጠልና ሌሎች አስከፊ ድርጊቶች በመከሰታቸው 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የሃይማኖት አባቶች ሰብስበን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖንሰርነት ይህንን ችግር ለመፍታትና ለማስወገድ ምን መደረግ አለበት ብለን የሠራነው ነው፡፡ ችግሮቹ ምንድናቸው? ብለን ካየን በኋላ መፍትሔዎችን በመንቀስ ለመንግሥት የመፍትሔና የፖሊሲ ሐሳቦችን አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት የመፍትሔ ሐሳቦች አቀረባችሁ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- እነዚህ ያቀረብናቸው 16 የሚሆኑ የፖሊሲ ግብዓት ሐሳቦች ናቸው፡፡ አንዱና ትልቁ ወጣቱ ልዩ ፓኬጅ ተዘጋጅቶለት የሥራ ዕድል የሚያገኝበት ዕድል በአስቸኳይ እንዲፈጠር የሚል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ዩኒቨርሲቲ ተቋቁሞ፣ ከዚህ ሁሉ ዩኒቨርሲቲ የሚወጡት ተማሪዎች የእናት የአባታቸውን እንጀራ በልተው ጠዋት ወጥተው ማታ ይገባሉ፡፡ ይህ አኗኗራቸው አበሳጭቷቸው ወደ አመፅ ቢገቡ ምን ይገርማል? ስለዚህ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ሲያዘጋጅ መጀመርያ እነሱን የሚቀበልበትን ማዘጋጀት አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን በአስቸኳይ ልዩ ፓኬጅ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ነው፡፡ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ለሰላም ሲባል ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የሚል ሐሳብ መጀመርያ ያቀረብነው እኛ ነን፡፡ በአገር ውስጥ ካሉትም ሆነ በውጭ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መንግሥት ይነጋገር፣ ይደራደር፡፡ በሰላማዊ መንገድ አብረን እንሥራ እስካለ ድረስ ሁሉንም አቅርቦ መንግሥት እንዲያነጋግር መጀመርያ ሐሳቡን አቅርበናል፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ምህዳሩንም ማስፋት እንዳለበት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ሁሉም በነፃ ምርጫ የሚሳተፍበት አማራጭ በአስቸኳይ እንዲፈለግ ጭምር ምክረ ሐሳባችንን አቅርበናል፡፡ በተለይ የአንዳንድ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ግንኙነት ኃላፊነትና የጋራ ተጠያቂነት እስከምን ድረስ ነው? የሚለውም ጉዳይ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ይህ የላላ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ታች ወርዶ ኅብረተሰቡ ውስጥ እየዋለ አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ በሰላማችን ላይ ክፍተት ፈጥሯል የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን ያጠቃለለ ጭምር ነበር፡፡ ሌሎች ዘርዘር ያሉ መፍትሔ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው የተለዩ ሐሳቦችን አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ምክረ ሐሳባችሁ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ሆኗል ብላችሁ ታምናላችሁ? አንዳንድ ምክረ ሐሳባችሁ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚመስሉ ምልክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች እነ አቶ ሌንጮ ለታ ወደ አገር ቤት መመለሳቸው የእኛ ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት እያገኘ ነው፣ የእኛ ውጤት ነው ይላሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- አዎ! እኛ ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር ተነጋግረናል፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቢሮ ሄደን ተመካክረናል፡፡ እናንተ ያቀረባችሁትን ምክረ ሐሳብ ቀስ በቀስ እየተገበርን ነው ብለው ነግረውናል፡፡ ግን በአብዛኛው የሰጠናቸውን ሐሳቦች ተቀብለው ሥራ ላይ ማዋልና በተጨባጭ መሬት ላይ የማውረድ ችግር ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሰውን ሐሳብ ወስዶ የራስ አድርጎ የማቅረብ ሁኔታዎች በአንዳንድ አካባቢዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የራስ ያልሆነ የሰው ሐሳብ ወስደህ ወደ ሥራ ላይ ስታውለው ይቸግርሃል፡፡ ግን የሐሳቡን አቅራቢዎች ማሳተፍና አብሮ መሥራት ረዥም መንገድ ሊያራምድህ ይችላል፡፡ ሌላው ሐሳባችን ተቀባይነት አግኝቷል ብለን የምናምንበት በ2009 የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ንግግር በሙሉ እኛ ያቀረብናቸው ሐሳቦች መሆናቸውን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን እንዴት ልታውቁ ቻላችሁ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የመንግሥት አካላት ይኸው የእናንተን ሐሳብ መንግሥት ተቀብሎ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ተካቷል ብለው አመሥግነውናል፡፡ ግን በጣም ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ምክረ ሐሳቦች የሰጣችሁባቸው አገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ለመንግሥት ያቀረባችሁት ነገር አለ፡፡ ስለእሱ ይንገሩኝ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ብዙ ያሳሰብናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ የህዳሴው ግድብ ዘላቂ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ ብለን 97 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት ነው የሰጠናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የህዳሴውን ግድብ የተመለከተው ፕሮጀክታችሁ ምን ዓይነት ነው? ምን ለማድረግ የሚያስችል ነው? ጥናቱስ እንዴት ተጠና? ተቀባይነትስ አግኝቶ ተተግብሯል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ግድቡን ከደለል ነፃ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ከደለል ነፃ ለማድረግ ብቻ 97 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ሁሉ ጥናት እኛ ዘንድ ባሉ ሳይንቲስቶችና የተፈጥሮ ሀብት ምሁራን የተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጥናት መቼ ነው የቀረበው? ለማን ሰጣችሁ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ይህን ነገር ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ያቀረብንላቸው፡፡ እሳቸውም ይኼ ነገር በጣም በዛ ወይ ግድቡን አቁሙ በሉን አሉ፡፡ እኛም አቁሙ አንልም፡፡ ሥጋቱን ነው የምናሳየው፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ግድቡ በደለል ይሞላል፡፡ በደለል ከተሞላ በኋላ መልሶ ለማውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡ በደለል ከተሞላ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ስለማይችል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ቀውስ ያስከትልባችኋል ብለን ነገርናቸው፡፡ እሳቸውም እስቲ በሌላ መንገድ አጥኑልን ብለው ጠየቁን፡፡ እሺ አልንና ሕዝብን በማንቀሳቀስ የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ የምትሠሩ ከሆነ፣ ሊሠራ የሚችል ነገር አለ ብለን እንደገና ወደ 12 ቢሊዮን ብር አወረድነው፡፡ ሌላ ፕሮጀክት ቀረፅን፡፡ አሁንም ቢሆን የህዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል በመሆኔ አብሬ እየሠራሁ ነው፡፡ በተለይ ጂአይዜድ ወደ አራት ሚሊዮን ብር ሰጥቶን በቤንሻጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየዘዋወርን የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የሠርቶ ማሳያ አድርገን እንዴት አድርገው መሬቱን እንደሚጠቀሙ፣ ግድቡ ከደለል የሚጠበቅበትን፣ የተፋሰሱ አካባቢ የሚለማበትን፣ እንዲሁም ወጣቱ በተፋሰሱ አካባቢዎች መሬት ቆንጣጭ ልማቶችን እንዲያካሂድ፣ ጥብቅ አካባቢ በማድረግ አፈር የሚይዙ ችግኞችና ዛፎች እንዲተከሉ በማድረግ ከደለል እንዲፀዳ ለማድረግ መሠራት እንደሚኖርበት የሚለውን ሐሳብ ሁሉ እኛ ነን የሰጠነው፡፡ በዚህ ሥራ እኛም የበኩላችንን እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ችግር ላይ የተከናወነ ሥራ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በዚህ ላይ የሠራችሁት ምን ነበር? የተገኘ ውጤት አለ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- አዎ ፎረማችን አንዳንድ ጊዜ የእሳት ማጥፋት ሥራ ይሠራል፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኞች ላይ የተነሳው ግጭት አሳስቦን በዚህ ላይ ምን ማድረግ አለብን? ይህንን ችግር ለመፍታት የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለን ስብሰባ አደረግንና የአገር ሽማግሌዎች መድረክ አቋቋምን፡፡ ክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን የበላይ ጠባቂ አድርገን በእኔ ሰብሳቢነት ከሃይማኖት ተቋማት አባቶችን፣ ምሁራንን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በማካተት የአስታራቂ ሽምግልና ብሔራዊ ኮሚቴ አዋቅረን ጅግጅጋ ድረስ ሄድን፡፡ እርግጥ ይህንን ሥራ ከፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ነበር የሠራነው፡፡ ምክንያቱም ግንኙነቶችን እነርሱ ናቸው ያመቻቹት፡፡ ጅግጅጋ ከሄድን በኋላ ክቡር አቶ አብዱ ዓሊን አነጋገርናቸው፡፡ የአገር ሽማግሌዎችን ይዘው ጠበቁን፡፡ በፍቅር በክብር ተቀብለው በተለይ እንደ እናንተ ዓይነት ነፃና የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆናችሁ ኢትዮጵያውያን የአገር ሽማግሌዎችን እንቀበላለን፣ ስለዚህ በእናንተ የሚመጣው እርቀ ሰላም መሠረታዊ ይሆናል ብለው አመሥግነውን እኛም አመሥግነን መጣን፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ሠራችሁ? ዕቅዳችሁስ ምን ነበር?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ዕቅዳችን ጅግጅጋ የተፈናቃዮችና ችግሩ የተከሰተባቸው ዞኖች አካባቢ ተወካዮች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ እርጉዞችና ሼኮች ያሉበት ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ነው፡፡ ይህ ኮንፈረንስ ደግሞ ችግሩን ነቅሶ አውጥቶ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ ነው፡፡ ከዚያ ከኦሮሚያ ጋር ለሚደረገው እርቀ ሰላም ከፌዴራል 100 ሰዎች እንዲወክሉ ጨርሰን መጣን፡፡ ከኦሮሚያ ደግሞ ክቡር አቶ ለማ መገርሳን አገኘናቸው፡፡ ካቢኔያቸውን ይዘው በክብር ነው የተቀበሉን፡፡ እሳቸውም እንደ እናንተ ዓይነት የአገር ሽማግሌዎችን እንቀበላለን፣ በእናንተ ያልተፈታ በማንም አይፈታም፣ የፖለቲካ አመራሮች ብዙ ጊዜ ተቃቅፈን ተሳስመናል፣ እስካሁን አልፈታነውም፣ ግን በእናንተ በአገር ሽማግሌዎች ይፈታል የሚል እምነት ስላለን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንሰጣለን አሉን፡፡ ከዚህ በኋላ አባገዳዎችን ማነጋገር ስለነበረብን አነጋገርናቸው፡፡ በሐሳባችን ደስተኞች ሁኑ፡፡ አብረውን ለመሥራትም ፈቃደኛ ሆኑ፡፡ ከዚያ በኋላ መሀል ላይ ፌዴራል ጉዳዮች ጅግጅጋ ላይ ስብሰጣ ጠራ፡፡ እንግዲህ ጉዳዩን መንግሥት ያዘው ብለን ተውነው፡፡ እስካሁን ድረስ ወገኖቻችን ድንኳን ውስጥ አሉ፡፡ ብርድ ይፈራረቅባቸዋል፡፡ አዲስ ቦታ ነው፡፡ ከትውልድ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የተማሪዎች የትምህርት ጊዜ እያለፈ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ያሉት ተፈናቃይ ወገኖቻችን የእርሻ ጊዜያቸው እያለፈባቸው ነው፡፡ ሁኔታው ለመንግሥትም ለክልልም ሸክም ነውና አሁን በዚህ ላይ ለመሥራት እየገፋንበት ነው፡፡ በየቦታው ያለው እንዲህ ያለው የሰላም ዕጦትና ችግር አሳስቦን ደግሞ፣ አገር አቀፍ የሰላምና መግባባት ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት አንድ ሺሕ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከየክልሉ መጥተው ስለሰላም እንዲመክሩ፣ ሰላምን ለማስከበር መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት ደግሞ ምክረ ሐሳብ የሚሰጥ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ የጀመራችሁት ሽምግልና በምን ተቋጨ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- አሁን የመንግሥት አካላት ገብተውበታል፡፡ አሁን እኛ በዚህ ሽምግልና ላይ የነበረንን ሥራ አቁመናል፡፡ ግን በቀጣይ የምንሠራቸው አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ተቋቁሟል፡፡ እርስዎም ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ የዚህ ኮንፌዴሬሽን መመሥረት ዓላማው ምንድነው?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ስንመሠርት የአሠሪዎች ጥቅምና መብት፣ እንዲሁም የሠራተኞችና የመንግሥት የሦስትዮሽን መድረክ ለማስፋትና በመመካከር ለአገሪቱ የተሻለ ዕድገትና ልማት ታስቦ ነበር፡፡ ግን መሀል ላይ አላስፈላጊ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ብዙዎቻችን ወጣን፡፡ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሊያሠራ የማይችል፣ ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ የማይሄድና አሳታፊ ባለመሆኑ፣ በጥቂት ሰዎች ለብዙ ዓመታት የተያዘና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማይካሄድበት ስለሆነ ብዙዎች ጥለው ወጡ፡፡ እኛ ቀደም ብለን የወጣን በመሆናችን የአዲስ አበባ አሠሪዎች ፌዴሬሽን መሥርተን፣ የአዲስ አበባ አሠሪዎችን ድምፅ እያሰማን ቆይተናል፡፡

አሁን ሌሎች ፌዴሬሽኖች በመምጣታቸው ወደ ኮንፌዴሬሽን መግባት ግድ እየሆነ መጣ፡፡ ኮንፌዴሬሽንን ከሁለት ፌዴሬሽኖች በላይ ሊመሠርቱት ይገባል የሚለው የአሠሪው ፍላጎት እየሰፋ በመምጣቱና የተለያዩ ዘርፎች በማበባቸው ምክንያት፣ የግድ ጊዜውና ወቅቱ በሚጠይቀው መሠረት ወደዚህ ገብተናል፡፡ ኮንፌዴሬሽን ሲሆን በአገር ውስጥም በውጭም ሐሳቡም፣ ድርሻውም፣ ተደራሽነቱም ሆነ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው፡፡ በኮንፌዴሬሽን መሰባሰባችን የብዙ ፌዴሬሽኖችን መብት የሚያስጠብቅና የአገራችንን አሠሪዎች ወደላቀ ደረጃና አስተሳሰብ የሚያራምድ ይሆናል፡፡ ወደ ቴክኖሎጂ መስክ ለመሸጋገር፣ የአሠሪው ድምፅ የትም ቦታ እንዲሰማ ለማድረግና የሠለጠነ አሠሪ እንዲኖር፣ ሕግና ሥርዓት አክባሪ አሠሪ እንዲኖር ነው ፍላጎታችን፡፡ አሠሪው ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ድምፁ የሚሰማበት መንገዶች የሉትም፡፡ አሠሪው ለአገሩ ልማት ዕድገት የሚሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አሠሪ መደገፍ አለበት፡፡ የልማት ምንጭ ነው፡፡ ግብር የሚከፍለው እሱ ነው፡፡ እሱ ቀጨጨ ማለት የመንግሥት አስተዳደር ቆመ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የተመቻቸ የሥራ ሁኔታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው ጋር አሠሪው መነጋገር ያስፈልገዋል፡፡ መደራደር ያስፈልጋል፡፡ የአሠሪው መጠናከርና ማደግ፣ የአሠሪው የተመቻቸ የሥራ አካባቢ መኖር ለሠራተኛው ዕድገት ነው፡፡ አሠሪው እየጠነከረና እያደገ በሄደ ቁጥር ሠራተኛውም በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል፡፡ አሠሪው ሲያተርፍ ለሠራተኛው ትልቅ ዕርካታና ድጋፍ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የሠለጠኑ አሠሪዎች በአገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ በኢንዱስትሪ፣ በእርሻና በአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ ዕውቀትና ግንኙነቶች እንዲኖሩ ጭምር ለማድረግ የዚህ ኮንፌዴሬሽን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግና ለበርካት ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንዲኖር ለማድረግ የግድ አሠሪው መሰባሰብና መጠናከር አለበት፡፡ አጥፊ አሠሪዎች እንኳን ቢኖሩ ለማረምና ለማስተካከል፣ ሕግና ሥርዓት እንዲይዙ ለማድረግ የግድ በቅርበት የራሳቸው ማኅበር፣ ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንን ለማቋቋም ለወራት ስትደክሙ እንደነበር ገልጻችኋል፡፡ አሁን ካሉት ስድስቱ ፌዴሬሽኖች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን እዚህ ስብስብ ውስጥ አልገባም በማለቱ፣ አምስቱ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽኑን መሥርታችኋል፡፡ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን አልገባም ያለው ለምንድነው? በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴሬሽኑ ኮንፌዴሬሽን አቋቁሜያለሁ ብሏል፡፡ ይህ ደግሞ ያለመግባባት መኖሩን ያሳያል ችግሩ ምንድነው?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን የነበረው ጊዜውና ወቅቱ ፈቅዶ፣ በየዘርፋቸውና በየክልላቸው የፌዴራል መዋቅሩን ይዘው እየተንቀሳቀሱ ካሉ ፌዴሬሽኖች ጋር እንዲመጣ በተደጋጋሚ ጥሪዎች አድርገንለታል፡፡ ደብዳቤም ጽፈናል፣ ሽምግልናም ልከናል፡፡ እሺ አሳውቃለሁ እየተባለ ጊዜያችን ተቃጥሏል፡፡ ወደ ስድስት ወራት አቃጥለውብናል፡፡ እኛም ፌዴሬሽኖቻችን ኮንፌዴሬሽኑን ለመመሥረት ለምንድነው የምትቆዩት እያሉን ስላስቸገሩን ወደዚህ መጥተናል፡፡ እኛ ከእነርሱ ጋር (ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን) ግጭት የለንም፡፡ እነሱ በሚሄዱበት መንገድ መሄድ ይችላሉ፡፡ እኛም እንደዚያው፡፡ አሠሪው ጠንካራውን ዓይቶ ወደሚመቸው ሊመጣ ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ አሠሪውን የሚመለከቱ አዋጆች ሲታወጁ አሠሪው በእነዚህ አዋጆች ላይ ቁጭ ብሎ አንድ ቀን የተወያየበት ጊዜ የለም፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ታወጀ ሲባል ነው የምንሰማው፡፡ ነገር ግን ታች ድረስ ወርዶ አሠሪው መብቱን የሚያስጠብቅለት አዋጅ መሆኑን አንኳን መነጋገር መቻል ነበረበት፡፡ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው ከሥልጣናቸው መቼ እንደሚወርዱ አይታወቅም፡፡ ብዙ ሰዎች ከዚያ የመጡ ናቸው፡፡ ይህንን መንግሥትና የመንግሥት አካላት ቢያውቁም በዓለም የሥራ ድርጅት ሕግ መሠረት መንግሥት ጣልቃ አይገባም በማለት እያዩ ዝም ነው የሚሉት፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ወሳኙ አሠሪው ነው፡፡ ሁልጊዜ የማይፈለግ ነገርን ማስወገድ የተፈጥሮ ግዴታ ስለሆነ፣ ያው መላ አገሪቱን የሚወክሉ አሠሪዎች በዚህ ኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ተሰባስበዋል፡፡ እነዚህ አሠሪዎች ናቸው እንግዲህ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንን የመሠረቱት፡፡ ነገ ጠዋት ደግሞ ከሠራተኛውና ከመንግሥት ጎን ቆመው በእኩልነት ለመነጋገር፣ ለአሠሪውም ለመንግሥትም፣ ለሠራተኛውም ጥቅም በጋራ ለመሥራት ታስቦ ነው በአገራችን የመጀመርያ የሆነው የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የተመሠረተው፡፡  

ሪፖርተር፡- እናንተ ይህንን ኮንፌዴሬሽን ለማቋቋም ቀድማችሁ አስተዋውቃችኋል፡፡ ነገር ግን ኮንፌዴሬሽንን በመሠረታችሁበት ዕለት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በተመሳሳይ ስም ኮንፌዴሬሽን መሠርታለሁ ብሏል፡፡ ይህ የሆነው ለምንድነው?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽን እሆናለሁ ብሎ የእኛን መርሐ ግብር፣ ሰምቶ ቀድሞ ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ መጀመርያውኑ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ሆኖ እየተጓዘ ያለው ተሳታፊ አሠሪዎች በሌሉበት የተወሰኑ ጥቂት አሠሪዎችን በመያዝ ብቻ ነው፡፡ እነሱን በማንከባለል ሲሠራ በመቆየቱ ብቻ ነው፡፡ እኛ ኑ አብረን እንሥራ አካሄዳችሁ ትክክል አይደለም፣ ይህ አሠሪው ቤት ነው፣ እንደ ጊዜው መቀየርና መለወጥ አለበት ብለን በአንድ ወቅት ብንነግራቸው፣ በፍፁም እዚያ አካባቢ የሚያስደርሱ አይደሉም፡፡ እኛ ኮንፌዴሬሽኑን ሐሙስ ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደምንመሠርት ጥሪ ማስተላለፋችንን ሲሰሙ፣ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ኮንፌዴሬሽን መሥርተናል አሉ፡፡ መጀመሪያ ሕጋዊ የሆኑና መሠረት ያላቸው ብዛት ያላቸው አሠሪዎች ስብስብ ነው ፌዴሬሽን ራሱ፡፡ ምክንያቱም ለኮንፌዴሬሽን መሠረት ስለሆን ማለት ነው፡፡ ፌዴሬሽን እዚያው ራሱን በራሱ መቀየር አይችልም፡፡ ያ የሽሚያ ፌዴሬሽን ቶሎ ሳይቀድመኝ ልቅደማቸው ወይም ላደናቅፋቸው ዓይነት አካሄድ ነው ሲያካሂዱ የነበሩት፡፡ ይህም ቢሆን ሁለት ሦስት ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን ቢኖርም ችግር የለውም፡፡ ዋናው የአሠሪውን ጥቅም ማነው የሚያስጠብቀው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ በይፋ ምሥረታ ያደረጋችሁበትን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የሚለውን ስም በሚመለከተው አካል አስመዝግባችኋል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- አዎ አሳውቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ አልገባም ባለው ፌዴሬሽንና በእናንተ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ምን ዓይነት ይሆናል? ኅብረተሰቡስ ጉዳዩን እንዴት ይረዳው?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ከእንግዲህ ወዲህ እኮ ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን አይገናኝም፡፡ እነሱ ወደዚህ ኮንፌዴሬሽን ነው መግባት ያለባቸው፡፡ እንግዲህ ሲገቡ ደግሞ መሥፈርት አለው፡፡ ይኼንን መመዘኛ የሚያሟሉ ከሆነ ሊገቡና ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ የመመሥረቻ ዕድላቸውን፣ ጊዜያቸውንና የአክብሮት ግብዣችንን ገደል ከተውታል፡፡ ስለዚህ አሁን በመደራጀት ላይ ያሉ ሌሎች ሦስት ፌዴሬሽኖች አሉ፡፡ ለእነሱ መድረክና ቦታ እንሰጣቸዋለን፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ ተደርጐ እስኪገቡ ድረስ በምክር ቤት ውስጥ እናሳትፋቸዋለን፡፡ ይህንን ደግሞ በጥልቀትና በስፋት በየክልሎች ባሉት መስተዳደር አካላት ውስጥ ሁሉም በየዘርፉ እየተደራጀ፣ በየክልሉ እየተሰባሰበና ፌዴሬሽን እያቋቋመ ወደ ኮንፌዴሬሽናችን እንዲመጣ እናደርጋለን፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴያችን ደግሞ የዓለም የሥራ ድርጅት ከእኛ ጋር እንደሚሠራ ቃል ገብቶልናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሠሪዎች በቀጥታ የሚወከሉባቸው የተለያዩ ማኅበራት አሉ፡፡ ለምሳሌ የንግድ ምክር ቤቶች አሉ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ነጋዴዎች ማኅበር የሚባል አለ፡፡ በየዘርፉም ሠራተኞች ማኅበርተኛ የሆኑበት የዘርፍ ማኅበራት አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አሠሪዎች አባላት የሆኑባቸው ማኅበራት ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ናቸው? እንዲህ መብዛቱ ጥቅሙ ምንድነው? መሰባሰቡስ ይታሰባል? አንድነትና ልዩነታቸውስ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- እኔም እኮ የግብርና ኢንቨስተሮች ማኅበር ሰብሳቢ ነኝ፡፡ ስለዚህ ግብርናን በግብርና ነው፡፡ በሌላውም የኢንቨስትመንት መስክ ያለ በአንድ ላይ ሆኖ ማኅበር ሊኖረው ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ ነጋዴዎች ማኅበርም የምናውቃቸው ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ ማኅበር ሲመሠረት አንድ አካባቢ ያለ መብት ለማስከበር ነው፡፡ በአንድ ዓላማ ሥር ያሉ ለመማማሪያ ለመተጋገዣ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፌዴሬሽን በሚሆንበት ጊዜ የራሳቸውን ማኅበርና መብታቸውን ጠብቀው በአንድ ላይ የሚሆኑበት ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽን በሚሆንበት ጊዜ ለመግባትም ለመውጣትም መብት ያላቸው፣ በራሳቸው ግን መሄድ የሚችሉ ኃይሎች ያሉበት ኅብረትና ጥምረት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቀድሞ የጠቀስካቸው በየራሳቸው መስክ የየራሳቸውን ሥራ የሚያስጠብቁ ናቸው፡፡ ይህ ኮንፌዴሬሽን የሚለየው አሠሪው ላይ የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የተቋቋሙበት ማኅበራት አሠሪ ቢሆኑም አሠሪ ብለው አይደለም የተቋቋሙት፣ የነጋዴ ማኅበር ነው ያሉት፡፡ ቻምበርም ቢሆን ራሱ የተቋቋመለት ዓላማ አለው፡፡ የአሠሪውን መብት የሚያስጠብቅ በመታጣቱ ምክንያት ቻምበር ይህንን ኃላፊነት ወስዶ መሥራት ጀመረ እንጂ፣ የአሠሪን መብት ለማስጠበቅ አይደለም፡፡ ቻምበር የአሠሪውን ድምፅ ያሰማ የነበረው ማኅበራት እንደ አንድ አባል ሆነው ቻምበር ስለገቡ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የአሠሪውን መብት የሚያስጠብቅ አካል ስላልነበረ ነው፡፡

ግን እዚህ ያለው ኮንፌዴሬሽን የአሠሪውን መብት እያስጠበቀ በድርድርና በተለያዩ መድረኮች ላይ እየሠራ ሲሄድ፣ ያን ጊዜ ቻምበር ይህንን አደርጋለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ቻምበር ኃላፊነቱና ሥልጣኑ ሌላ ነው፡፡ በብዙ አገሮች ቻምበሮች የሚሠሩት ሥራ አላቸው፡፡ ቻምበር ለነጋዴዎች ድጋፍ የመስጠት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ስለዚህ የምንመሳሰልበት ነገር ሲኖር በምንሠራው ሥራ ብንለያይም፣ በአንድ ላይ ሆኖ ለመሥራትም የሚያስችሉን መንገዶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን መሥራች ነበሩ እርስዎና ሌሎች ሰዎች ወጥታችኋል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን መሥርተን እኔም በሥራ አስፈጻሚነት ስሠራ ቆይቼ፣ በሁለተኛው ምርጫ ባላወቅነው መንገድ ያልሆኑ ሰዎች ገብተው ሕገወጥ ሥራዎች ሲሠሩ በማየታችን እንዲታረሙ ብንጠይቅም ሊታረሙ ባለመቻላቸው ወጣን፡፡ በወቅቱ ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሰነው ነበር፡፡ እንዲያውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 3,500 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠን አዘው ቦታውን ለማስፈቀድ የሕንፃውን ዲዛይን ሁሉ የሠራሁት እኔ ነኝ፡፡ ይህንን መሬት ከወሰድን በኋላ አሁን የት እንዳለ አናውቅም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...