የህንዱ ሞተር ብስክሌት ገጣጣሚ የ20 በመቶ የብድር ድጎማ ጠይቋል
ያማሃ ሞተር የተሰኘው የጃፓን ሞተር ብስክሌት አምራች፣ ለአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊሶች መገልገያነት የሚውሉ 275 የሞተር ብስክሌቶችን ሊያቀርብ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
ኩባንያው የአገር ውስጥ ወኪሉ በሆነው ሐግቤስ ኩባንያ በኩል እያስገጣጠመ የሚያቀርባቸው የፖሊስ ሞተር ብስክሌቶች 900 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሲሆኑ፣ ከ2.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደወጣባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኩባንያው ዓለም አቀፍ የገበያ ልማትና የቢዝነስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ሞቶኪ ዋንታናቤ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ያማሃ ሞተር ከሽያጭ አቅርቦቱ ጎን ለጎን ለሥልጠናና ለድኅረ ሽያጭ አገልግሎት ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ለ50 የትራፊክ ፖሊስ አባላት የቴክኒክ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
የሐግቤስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ወንድአፍራሽ በበኩላቸው፣ ከጃፓን የሚመጡትን ሞተር ብስክሌቶች በአገር ውስጥ በመገጣጣም ብቻም ሳይሆን፣ በሌሎችም የምርት አቅርቦቶች ላይ ከኩባንያው ጋር ላለፉት 40 ዓመታት ያህል በአጋርነት መሥራቱን አስታውሰው፣ ከዚህ በፊትም ለአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ አገልግሎት እንዲውሉ ግዥ የተፈጸመባቸው ሞተር ብስክሌቶች ሥራ ላይ ከማዋላቸው በፊት መሠረታዊ የአነዳድና ከአደጋ የመከላከል ሥልጠናዎች ለአሽከርካሪዎቹ ትራፊክ ፖሊሶች መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ለትራፊክ ፍሰት ማስተናበሪያነትና ቁጥጥር ሥራ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 67 ሞተር ብስክሌቶች ሲሆኑ፣ በአዲሱ ግዥ መሠረት 275 አዳዲስ ሞተር ብስክሌቶች ሥራ ላይ ስለሚውሉ የትራፊክ ቁጥጥሩን እንደሚያጠናክሩት ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ለእጀባ የሚውሉት በአብዛኛው ባለ 1,300 ሲሲ ሞተር ብስክሌቶች ሲሆኑ፣ እነዚህን ጨምሮ ባለ 900 ሲሲዎቹን ሞተሮች ለክልሎችም በማቅረቡ፣ በጠቅላላው ከ330 በላይ የትራፊክ ፖሊስ ሞተሮች ከያማሃ ተገዝተው ሥራ ላይ ስለመዋላቸው ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ የተሰኘው የህንድ ሞተር ብስክሌት ገጣጣሚ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪም ሆነ የብድር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ እንዲቻል መንግሥት ወደ ውጭ ለሚልኩ ኩባንያዎች የ20 በመቶ የገንዘብ ድጎማ በብድር መልክ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ የኩባንያው ተወካዮች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ወቅት በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደጠየቁት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአገር ውስጥ አልፈው ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንዲቃለልላቸው የሚያስችላቸው የ20 በመቶ የገንዘብ ድጎማ ማድረግ ይገባል፡፡
ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ከዚህ ቀደምም በቆዳ ኢንዱስትሪዎች በኩል ተጠይቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ያቀረቡት ጥያቄ እንደ ወጪ ንግድ ማበረታቻ የሚቆጠርላቸውና እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ማበረታቻ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም ወደ ውጭ ልከው ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 30 በመቶ የሚደርሰው በብር ተቀይሮ እንደ ማበረታቻ እንዲሰጣቸው የሚያመላክት ሲሆን፣ ይህም ሲደረግ ያለባቸውን የሥራ ማስኬጃ የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ሊቀርፍላቸው የሚያስችል ማበረታቻ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ እንዲህ ያለው ማበረታቻ ወይም በአገር ውስጥ ገንዘብ ታሳቢ የሚደረግ ወይም ‹‹ካሽ ባኪንግ ኢንሴንቲቭ›› የሚባለውና እንደ ቱርክ ያሉት አገሮች የወጪ ንግዳቸውን ለማስፋፋት የተጠቀሙበት የማበረታቻ ሥልት ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡
ሐግቤስ ኩባንያ የአርመን ዝርያ ባላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ከ67 ዓመታት በፊት የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ1,500 በላይ ሠራተኞችን የሚያንቀሳቅሱ በርካታ ኩባንያዎችን ያቀፈ ግሩፕ ኩባንያ ሲሆን፣ እንደ አቶ ዓለማየሁ ማብራሪያ ከሆነም በ25 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደበት የሚገኘውና በቢሾፍቱ ከተማ ፓስታና ማካሮኒ የሚያመርተው ፋብሪካ፣ በኩባንባው ሥር ከሚጠቀሱ ትልልቅ ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች ውስጥ ይመደባል፡፡