Thursday, May 30, 2024

የኦዴግና የኢሕአዴግ ድርድር በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር)፣ የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ ከመረጠና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ከተሾሙ ሁለት ወራት ሊሞላቸው ከአንድ ሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ብቻ ይቀራል፡፡ በእነዚህ ሁለት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች እየተዘዋወሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲያነጋግሩና ሲያወያዩ ነበር፡፡

በእነዚህም ውይይቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመርያ ጊዜ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉትን ንግግሮች በመመንዘር ምን? መቼና? እንዴት? ይደረግ የሚሉ ጉዳዮችን ሲያነሱ ነበር፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ያስችል ዘንድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶች እንደሚደረጉ፣ እነሱ ‹‹በተፎካካሪነት›› የሚታዩ እንጂ እንደ ጠላት ተፈርጀው የሚገለሉ እንዳልሆኑና የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ስብስብ መሆናቸውን አምኖ የተቀበለ ሥርዓት ለመገንባት ያለመ እንቅስቃሴ እንደሚደረግም፣ በንግግራቸው አስታውቀው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፣ ‹‹ዴሞክራሲ ለእኛ ባዕድ ሐሳብ አይደለም። በዓለም ውስጥ በብዙ ማኅበረሰቦችና አገሮች ዴሞክራሲ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዓታችን ተዳድረን ለዓለም ተምሳሌት ሆነን ኖረናል። አሁንም ዴሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም አገር በላይ ለእኛ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዴሞክራሲ ያለ ነፃነት አይታሰብም። ነፃነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ፀጋ እንጂ። ነፃነትን በዚህ መልኩ ተረድቶ ዕውቅና የሰጠውን ሕገ መንግሥታችንን በአግባቡ መተግበር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ መንግሥታችን መሠረት ሊከበር ይገባል። የዜጎች በአገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዴሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ ዕውን መሆን አለበት፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

 ለዚህም፣ ‹‹በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የመጀመርያውም የመጨረሻውም መርህ፣ በመደማመጥ የሐሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ የጋራችንና የእኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን እሳቸው በተኳቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች ውሳኔ ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም፣ ይኼንን ንግግር ወደ ተግባር ለማሸጋገር አግዟል የተባለለትና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የነበሩና በፖለቲካ አመለካከታችን ታሰርን እንጂ ጥፋት አላጠፋንም ብለው የሚከራከሩ በርካታ ግለሰቦችን ክሶች በማቋረጥ ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡

ይሁንና እነዚህ ዕርምጃዎች ጅምር እንደሆኑና በቀጣይም መንግሥት ዕውን በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ክፍተትና ችግር መፍታት ካለበት አሳታፊና እውነተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲያወያይ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ የምርጫ ምኅዳሩን እንዲያሰፋ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር፡፡

ይሁንና መንግሥት፣ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ከተውጣጡ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ድርድሮችን ሲያደርግ ቢቆይም፣ በውክልና ከገቡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር የሚደረገው ድርድር እምብዛም ያላስደሰታቸው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ያጣጣሉት ሲሆን፣ ትክክለኛ የሕዝብ ድጋፍ ካላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አጀንዳ ይዞ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ሲናገሩ ነበር፡፡

ይሁንና እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ከመንግሥት የእንወያይ ፍላጎት ያልታየ ስለሆነ፣ አመራሮቹም ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሒደቱን ለማስቀጠል የቀረባቸው የኢሕአዴግ አመራር እንዳልነበረ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም የትውውቅ ዝግጅት ከማድረግ የዘለለ፣ ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዳደረጉት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ኢሕአዴግ አመራሮች ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አላደረጉም፡፡ ይሁንና እሳቸው ከሚመሩት ፓርቲ የተወከሉ የልዑካን ቡድን አባላት ራሱን ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ገንጥሎ፣ በተናጠል የፖለቲካ ፓርቲ በመመሥረት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) በሚል ስያሜ ከሚንቀሳቀሰው ድርጅት ጋር ድርድር በማድረግ፣ አመራሮቹ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

የኢሕአዴግና የኦዴግ ተወካዮች የተገናኙበት ጊዜና ቦታ ባይገለጽም፣ ኦዴግ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተመራ ልዑክ ጋር ግንቦት 3 እና 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ተገናኝተው መነጋገራቸውን፣ በቀጣይም የሚደረገው ውይይት አዲስ አበባ እንደሚሆን አስታውቆ ነበር፡፡

‹‹ሁለቱ አካላት አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ በማስመልከት ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡ ኦዴግ ለረዥም ጊዜ አብሮት በዘለቀው የሕዝብ ወገንተኝነት ምክንያት፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩንና የተጀመሩትን ለውጡች ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነት አስታውቋል፤›› ሲል ኦዴግ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

ይኼንን ውይይት ተከትሎ አምስት አባላት ያሉት የኦዴግ ልዑክ ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባዱላ ገመዳና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል፡፡

የኦዴግ ልዑክም የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ሌንጮ ለታና ምክትል ሊቀመንበሩ ዲማ ነገዎን (ዶ/ር) ጨምሮ አምስት የድርጅቱን አባላት ያቀፈ ነው፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አዲስ አበባ ሲገቡ በሰጡት መግለጫ፣ ካሁን ቀደም በተደረገው ውይይት ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ወደ አገራቸው መጥተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ማሰባቸውንና ከእነሱ ጋር የፖለቲካ ትብብር ያላቸውና በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ ግፋ ሲልም ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተጣምረው ለመሥራት እንደሚያስቡም ተናግረዋል፡፡

‹‹በቅርቡ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ያደረግነው ውይይት በፖለቲካና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ መጥተን እንድንነጋገር በተስማማነው መሠረት ነው አሁን የመጣነው፡፡ በቅርቡ ያደረግነው ንግግር በጣም የተሳካና ወንድማማችነት የተሞላበት ስለነበር ደስ ብሎናል፡፡ ዋናው የምንነጋገርበት ጉዳይ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰፋ ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው አሠራር በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት፣ በፓርላማ ከገዥው ፓርቲ ውጪ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ የሌለበት መሆኑ የፖለቲካ ምኅዳሩን አጥብቦታል፤›› ሲሉ ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼም መደረግ የነበረበትን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጎድቶታል ብለን ነው የምናምነው፤›› ብለዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ብቻውን የበላይነት ይዞ መቆየቱ እንደሚጎዳው ስለተገነዘበና ይህም ለአገሪቱም ጎጂ ስለሆነ፣ አሁን በፓርቲው ውስጥም ሆነ በአገሪቱ ያለውን ለውጥ በመጠቀም ለውይይት እንደመጡም ምክትል ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡

አቶ ሌንጮ በበኩላቸው፣ ከስድስት ዓመታት በፊት መንግሥትን ለማግኘትና ለመወያየት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበርና ይህም ሳይሳካ መቆየቱን ገልጸው፣ ለዓመታት ‹‹በዝቅተኛ ደረጃ›› ከመንግሥት ጋር ግንኙነቶች የነበሯቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ከመንግሥት በኩል ፍላጎት እንዳልነበረ አክለዋል፡፡

‹‹አገሪቱ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ በፍጥነት እየተለወጠች በመሆኑና እኛ ደግሞ ከአገሪቱ ከወጣን ረዥም ጊዜ ስለሆንን፣ ያንን ካጠናን በኋላ ነው ተሳትፏችን በምን ዓይነት ሁኔታ ይሁን የሚለውን የምንወስነው፤›› ሲሉ አቶ ሌንጮ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፍላጎታችን ግን ግልጽ ነው፣ ያለው ፌዴሬሽን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሌንጮ አክለውም በውጭ አገር የተደረገው ውይይት እነሱን እዚህ አገር ማስመጣት ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር፣ የፖለቲካ ጉዳዮችን ገና እዚህ አገር ውስጥ እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል፡፡

‹‹እዚህ ለመድረስ መፈታት የነበረባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ካሁን በኋላ ግን ሰፋ ያሉ የፖለቲካ ውይይቶችን እናካሂዳለን፡፡ ያለው ለውጥ ምንድነው? ጠንካራና ደካማ ጎኖቹ ምንድናቸው? ሊያመጣ የሚችለው አደጋና የሚያመቻቻቸው ነገሮች ምንድናቸው? የሚለውን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተን እኛ የትና እንዴት አስተዋፅኦ ማድረግ እንደምንችል እንለያለን፡፡ ውጭ ስለኖርንና ብዙ ደጋፊዎቻችንም ውጭ ስላሉ፣ እንደ ድልድይ ለመሆንና በዚያ ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን፤›› ሲሉ አቶ ሌንጮ አስረድተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከመንግሥት ጋር እያደረገ ያለውን ውይይት አስመልክቶ ምንም ዓይነት መግለጫ ከመንግሥት አልተሰጠም፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የልዑካን ቡድኑን አባላት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው እንዳነጋገሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኦዴግ አመራሮች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ የኦዴግ አመራሮች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ ተስማምተዋል፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች የኢትዮጵያን አንድነት ማጠንከርና የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱን ጥልቅ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገው ለመሥራት ተስማምተዋል፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የካቲት ውስጥ ባወጣው መግለጫ ውጭ አገር ካሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኝነቱን በገለጸበት ወቅት፣ የኦዴግ አመራሮች በደስታ እንደሚቀበሉትና በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀው ነበር፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከልም ጥሩ ግንኙነት እንደነበር የኦዴግ ሊቀመንበር በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ኦዴግ የኦሕዴድን ውሳኔ እያደደነቀ ይኼንን አጋጣሚ በመጠቀም ከፓርቲው ጋር ለመሥራት ፈቃደኝነታችንንና ዝግጁነታችንን ልናሳውቅ፣ የኦሮሞ ሕዝቦችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ፌዴሬሽን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ ልክ ከፓርቲያችን ምሥረታ ጀምሮ ስናራምደው እንደነበረው አቋም ጠንክረን እንሠራለን፤›› ይል ነበር መግለጫው፡፡

ኦዴግ ከኦነግ ግር በነበረው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት በተገነጠለ ቡድን የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆን፣ የኦሮሞ ፌዴሬሽንን ለማቋቋም ከሚያስበው ኦነግ የተለየ አቋም የሚያንፀባርቅና በፌዴሬሽን የሚያምን የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በፓርቲ ደረጃ ምንም ዓይነት አስተያየት ላለመስጠት እንደተስማሙ ጠቅሰው፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ ከኦፌኮ ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሪ እንዳቀረበላቸውና ትክክለኛ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ለመነጋገር እንደተዘጋጁ አስታውቀዋል፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -