Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥትና የግሉ ዘርፍ እየተነጋገሩም አልተግባቡም

ተዛማጅ ፅሁፎች

 መንግሥት የግሉ ዘርፍ ፍትሐዊ ውድድር ላይ ያተኩር ይላል

የግሉ ዘርፍ በበኩሉ መንግሥት አግላይ ነው ሲል ይወቅሳል

የአፍሪካ ልማት ባንክ በጠራውና ይበልጥ በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ላይ ብቻ ባተኮረው የውይይት መድረክ ወቅት፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች በመንግሥት ላይ የቆዩና ነባር ቅሬታዎችን ሲያስተጋቡ፣ መንግሥት በበኩሉ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያደርገው ተሳትፎ ዝቅተኛ ስለሆነ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል ሲል ወቀሳ አቀረበ፡፡

ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክክር መድረኩ የተገኙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) በንግግራቸው ወቅት እንዳስታወቁት፣ ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ለውጦች እየታዩ መጥተዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ከደርግ መንግሥት በኋላ ከወደቀበት ተነስቶ ብዙ ለውጥ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ የተጋረጡበትን ማነቆዎችም አልሸሸጉም፡፡ የፋይናንስ አቅርቦት፣ በተለይም እየተባባሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ዋቢ አድርዋል፡፡ የሊዝ ፋይናንስ፣ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚውል የብድር አቅርቦት በማመቻቸት፣ ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው የብድር አቅርቦት እያደገ ስለመምጣቱም አብራርተዋል፡፡

ይሁንና በ25 ዓመታት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ያሳየው የኢንተርፕነርሺፕ ጉዞ ዝቅተኛ እንደሆነ፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎቻቸውን ከመንግሥት ግቦችና ተልዕኮዎች ጋር ማጣጣም እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹እንመካከር፣ እንነገጋገር፡፡ የድርሻችሁን ውሰዱ፣ እኛም እንውሰድ፡፡ አገሮች እንዲህ ነው ውጤታማ የሆኑት፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በፍትሐዊ ውድድር እመኑ፡፡ ውድድር የዓለም አቀፍ ገበያዎች በር መክፈቻ ነው፡፡ ዘላቂነትን ማረጋገጥ የሚቻለውም በውድድር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና ሚኒስትሩ ስለውድድር የተናገሩት ነጥብ ትችት አስነስቶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ስብሰባውን ከፍተው ቢሄዱም፣ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ጎምቱው የፋይናንስ ባለሙያና የሕብረት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ የሰላ ትችት አሰምተዋል፡፡

መንግሥት የግሉን ዘርፍ በፍትሐዊነት ተወዳደር ሲል ቀድሞውኑ ራሱ መቼ በውድድር ያምናል የሚል ተቃውሞ ያሰሙት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር ነው በማለት የሚጠቀሰው አባባል ከንግግር ያልዘለለ የይስሙላ ንግግር ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ በአገሪቱ ሲታይ የቆየው የወጣቶች አመፅና ቁጣም ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ›› የሚያሰኝ ወቅት ስለመሆኑ ሲናገሩም፣ ጊዜው ይህንን እየጠየቀ ነው በማለት አሳሳቢነቱን አመላክተዋል፡፡

መወዳደሪያ ሜዳው የእኩል ተጫዋቾች አይደለም የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ በተለይም በፋይናንስ መስክ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች ላይ የሚተገብረውን የ27 በመቶ የቦንድ ሰነድ ግዥ ዋቢ አድርገዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በግል ባንኮች ላይ ባስቀመጠው ግዴታ መሠረት ከእያንዳንዱ ብድር ላይ እየተቀነሰ ለመንግሥት ፕሮጀክቶች እንዲውል የሚሰበሰበው ገንዘብ ለአምስት ዓመታት በብሔራዊ ባንክ የሚተዳደር ሲሆን፣ በየዓመቱ የሦስት በመቶ ወለድ ብቻ ይታሰብበታል ብለዋል፡፡

በአንፃሩ የግል ባንኮች ለአስቀማጮች እስከ 12 በመቶ ወለድ እንደሚከፍሉና ለተበዳሪዎች ደግሞ እስከ 21 በመቶ ወለድ እንደሚያስከፍሉ ጠቅሰው፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ የግል ባንክ ደንበኞች በምን አግባብ እንዴት ከብድር ወለድ ትርፋማ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ይጠይቃሉ፡፡ ይህንን ኢፍትሐዊ የፋይናንስ ሁኔታ የፈጠረው መንግሥት የሚከተለው አሠራር እንደሆነ በማብራራት፣ የመንግሥት የሕግ ማዕቀፍ በሚያሳየው ተለዋዋጭ አተገባበር ሳቢያ ለመተንበይ አስቸጋሪ ስለመሆኑ፣ ፍትሕ የሚሰጠው በውክልና ስለመሆኑ፣ ተገቢው የማጣራት ሥራ በመንግሥት እንደማይሠራና መሰል ቅሬታዎችን አሰምተዋል፡፡

በመድረኩ የተንፀባረቁ ሌሎችም ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በተለይም ብሔራዊ ባንክ የሰላ ትችት የቀረበበት በካፒታል ገበያ ላይ እያራመደ በሚገኘው አቋም ሳቢያ ሲሆን፣ የፌርፋክስ አፍሪካ አማካሪ ኩባንያ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ከአቶ ኢየሱስ ወርቅ ጋር በመተጋገዝ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥውንና ዋና ኢኮኖሚ ባለሙያውን ዮሐንስ አያሌውን (ዶ/ር) ሞግተዋቸዋል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት የካፒታል ገበያው ክፍት እንዲደረግ፣ ኢትዮጵያውያን በመንግሥትም ሆነ በግል ኩባንያዎች ውስጥ እንደ አቅማቸው ድርሻ በመግዛት፣ ባስፈለጋቸው ጊዜም ድርሻቸውን በመሸጥ የሚሳተፉበት የካፒታል ገበያ እንዲመሠረት ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን ሁለቱ የፋይናንስ ባለሙያዎች አስታውሰዋል፡፡

ምክትል ገዥው መንግሥት የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ እንዲጀመር ፍላጎት እንዳለው ቢገልጹም፣ በምን አግባብ መቆጣጠር ይቻላል የሚለው አሳሳቢ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ መቼ ሊተገበር ይችላል የሚለው ነጥብ የመንግሥት ሥጋት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ ይህን በሚያስረዱበት ወቅት አቶ ዘመዴነህ አቋርጠዋቸው እንደገለጹት ከሆነ፣ መንግሥት የመቆጣጠሪያ ሥልቶችን ቢያሻው ከኢንተርኔት ማውረድ እንደሚችል፣ ወይም በሚያሻው መንገድ የቁጥጥር ሥልቶችን መንደፍ እንደሚችል በማብራራት ከፍርኃቱም ከሥጋቱም እንዲላቀቅ አሳስበዋል፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት በቋሚነት የካፒታል ግብይት ይፈጸምባቸው ከነበሩት ተቋማት መካከል እንደ ወንጂ ሸዋ ስኳርና ሳባ ጠጅ የመሳሰሉትን ኩባንያዎች አስታውሰዋል፡፡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይካሄድ የነበረበው የካፒታል ወይም የስቶክ ገበያ ሒደት ‹‹ሼር ዲሊንግ ግሩፕ›› የሚል መጠሪያ እንደነበረው፣ የግብይቱ ሊቃነ መናብርትም የወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ ኮሜርሺያል ኖሚኒስ የተሰኘው ኩባንያ የዚህ ግብይት ሥርዓት ቅሪት ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ 

የካፒታል ገበያ ሊመሠረት የሚችልባቸው ገደቦችን በማስቀመጥ ማስጀመር ይገባል ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ መንግሥት የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ የውጭ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዳይሳተፉ በመከልከል ጭምር ማስጀመር የሚችልባቸውን መንገዶች አመላክተዋል፡፡ አገሪቱ ያሏት የሒሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ጉዳይ፣ የኩባንያዎች የሒሳብ መዝገብ አያያዝ (ለመንግሥት አካላት የሚያሳዩትና ለራሳቸው ለይተው የሚይዙት) ሥርዓት የሕዝብን አመኔታ እንዳያሳጣ ያሠጋል ያሉት ምክትል ገዥ ዮሐንስ፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለካፒታል ገበያ የመመዝገብ ብቃታቸውም አጠያያቂ መሆኑን በማውሳት ተከራክረዋል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተሰኘው ኩባንያ ስለካፒታል ገበያ በማጥናትና የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በማውሳት ለመንግሥት በሰነድ ቢያቀርብም፣ ይህ ገበያ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ በጊዜው ምላሽ መሰጠቱን አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውሰው፣ ከ20 ዓመታት በኋላም ጊዜው አይደለም መባሉ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ጨምሮ የአፍሪካ ልማት ባንክ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶችና የግሉ ዘርፍ ከባንኩ ተጠቃሚ መሆን ስለሚችልባቸው የብድርና ሌሎች የአገልግሎት መስኮች፣ ባንኩ ከተመረጡ የአገሪቱ የግል ዘርፍ ተዋናዮች ጋር የጀመረው ምክክር ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በመካሄድ ላይ ነው፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች