Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቀሉ

  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቀሉ

  ቀን:

  ‹‹አራት ዓመት ለእኔ ትንሽ መስዋዕትነት ነች›› አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

  የዶ/ር ብርሃኑ ነጋና የአቶ ጃዋር መሐመድ ክስ ተቋረጠ

  ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መንግሥት ባደረገላቸው ይቅርታ መሠረት ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ከእስር ተለቀው ከቤተሰቦቸው ጋር ተቀላቅለዋል፡፡

  ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ አቶ አንዳርጋቸው ከግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የእስር ጊዜያቸው በይቅርታ ቀሪ መደረጉንና በርዕሰ መስተዳድሩ ይሁንታ ከእስር እንደሚፈቱ መወሰኑን ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን ‹‹የማስፈቻ ማዘዣ አልመጣም›› ተብለው እስከ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በማረሚያ ቤት መቆየታቸውን፣ አቶ አንዳርጋቸው በቤተሰቦቻቸው ቤት አቀባበል ላደረጉላቸው ሰዎች ተናግረዋል፡፡

  ከእስር በመፈታታቸው ደስ እንዳላቸው የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው፣ ‹‹እፈታለሁ ብዬ አልጠብቅም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

  ‹‹የአራት ዓመታት መስዋዕትነት ለእኔ በጣም ትንሽ ነች፤›› ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ በአራት ዓመታት የእስር ቤት ቆይታቸው ብዙ ያዩት ነገር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ብዙ መነገር ያለበትና መነጋገርም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹በአሳሪዎቼ ፊት መነጋገር ባንችልም፣ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ የምንነጋገርበት ቦታና ጊዜ አለ፤›› ብለዋል፡፡

  አቶ አንዳርጋቸው ቦሌ ከጌቱ ኮሜርሻል በስተጀርባ የሚገኘው የአባታቸው አቶ ጽጌ ሀብተ ማርያም ቤት ሲደርሱ በርካታ ሰዎች ስለነበሩ፣ አባታቸውን ያገኙት ቆይተው በሰዎች ሸክም እንደነበር በሥፍራው ለማየት ተችሏል፡፡

  በተያያዘ ዜና በ2009 ዓ.ም. ከመረራ ጉዲና (ዶ/ር) ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) እና አቶ ጃዋር መሐመድ ክስ ተቋርጧል፡፡

  ክሱ የተመሠረተው በሌሉበት በመሆኑ የመረራ (ዶ/ር) ክስ ተቋርጦ ከእስር ሲፈቱ የእነሱ ክስ ባለበት ቆሞ ነበር፡፡ ሰሞኑን የብዙዎችን ክስ በማቋረጥ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3ሀ) መሠረት በተሰጠው ሥልጣን ክሱ እንዲቋረጥ አድርጎ፣ ክሱን ባለበት ትቶት ለነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦ አፀድቋል፡፡ በመሆኑም ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)፣ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ ኦኤምኤንና ኢሳት ቴሌቪዥን ክሳቸው ተቋርጧል፡፡

  በታምሩ ጽጌና በናሆም ተስፋዬ

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...