ባለንብረቶች በመንገድ ብልሽት ለኪሳራ ተዳርገናል አሉ
መንግሥት ከውጭ በገፍ የገዛቸው ምርቶች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸው፣ በተለይ ከወደብ እስከ ጋላፊ ያለው መንገድ ክፉኛ በመበላሸቱ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደተፈጠረ ተመለከተ፡፡
መንግሥት ለ2010/2011 ዓ.ም. ምርት ዘመን የሚያስፈልግ 1.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በ600 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግዥ እየፈጸመ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ገበያ ለማረጋጋት 200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ1.6 ቢሊዮን ብር በሚሆን ወጪ፣ እንዲሁም 400 ሜትሪክ ቶን ስኳር በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡
ከተፈጸመው ግዥ ውስጥ በአብዛኛው ጂቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን፣ መንግሥት በተለይ ለማዳበሪያ ቅድሚያ በመስጠት ወደ አገር በማስገባት ላይ ነው፡፡
ነገር ግን በጂቡቲ በኩል እስከ ጋላፊ ድረስ ያለው 200 ኪሎ ሜትር መንገድ በመበላሸቱ የተሽከርካሪዎችን ምልልስ ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን እየሰባበረ ጉዞን አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል፡፡ በዚህ ምክንያት በወደብ በሚፈለገው ፍጥነት ምርት እየተነሳ ካለመሆኑ በተጨማሪ በመንገዱ ብልሽትም ምልልስ ተስተጓጉሏል ተብሏል፡፡ 250 ተሽከርካሪዎች ያሉት የሰሜን ድንበር ተሻጋሪ ደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አደም መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመንገዱ ብልሽት ምክንያት የተሽከርካሪዎች ምልልስ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡
‹‹ከምልልስ መስተጓጎሉ ባሻገር ዕቃዎች እየተሰባበሩ ነው፡፡ የመለዋወጫ ዋጋ ንረትም እጅግ በመጨመሩ ተሽከርካሪዎች ከመንገድ እየወጡ ነው፤›› በማለት አቶ አደም ገልጸው፣ ‹‹በተለይ ለማዳበርያ ጉዞ የሚከፈለው ክፍያ በነፃ ገበያ መርህ ሳይሆን በተቆረጠ ዋጋ በመሆኑ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል፣ በትርፍ ሳይሆን በኪሳራ ነው እየሠራን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከአምስት ሺሕ በላይ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ወደብ የደረሰውን ምርት ለማስገባት በቂ እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡
ለረዥም ጊዜ የትራንስፖርት ባለሥልጣንን የመሩት አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ከሁለት ሳምንት በፊት ተነስተው የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አብዲሳ ያደታ ተተክተዋል፡፡ አቶ አብዲሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደብ የደረሱ ምርቶችን በማንሳት ወደ አገር የማስገባቱ ሥራ ቀጥሏል፡፡
‹‹በእርግጥ በጂቡቲ በኩል ያለው መንገድ ተበላሽቷል፡፡ ይህንን መንገድ ለማሠራት መንግሥት ከጂቡቲ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው፤›› በማለት የገለጹት አቶ አብዲሳ፣ ‹‹ባለፈው ሳምንት ረቡዕ 300፣ ሐሙስ 280፣ ዓርብ 334፣ ቅዳሜ 441፣ እሑድ 281 ተሽከርካሪዎች ምርት አንስተዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አቶ አብዲሳ እንዳሉት ቅድሚያ የተሰጠው ለምርት ዘመኑ አስፈላጊ ለሆነው ማዳበሪያ ነው፡፡ ጎን ለጎንም ስንዴ፣ ስኳርና ሌሎችንም ዕቃዎች የማንሳቱ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ቁርጥ ዋጋን በተመለከተ አቶ አብዲሳ፣ ‹‹መጀመርያ ጨረታ ይወጣል፡፡ በጨረታው የተገኘው ዋጋ ለሁሉም እንዲሠራ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አደም ግን በጨረታው ተወዳድሮ አሸናፊ ነው የተባለው የትራንስፖርት ድርጅት አቅም የሌለውና እሱ ባቀረበው ዋጋ እንድንሠራ በመወሰኑ፣ ሥራውን ለመሥራት አዳጋች ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህንንም ጉዳይ ለመንግሥት በተደጋጋሚ ቢያስረዱም እስካሁን ምላሽ አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡