Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበወሊድ የሚሞቱ እናቶችን ለመታደግ

በወሊድ የሚሞቱ እናቶችን ለመታደግ

ቀን:

እናታቸው ነርስ የመሆን ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም አልተሳካላቸውም፡፡ በትዳር ዘመናቸውም አራት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያ የመሆን ህልማቸውንም በልጆቻቸው ለማሳካት ያልሙ ነበር፡፡ ስለ ሕክምና ሙያ ጥሩነት ለልጆቻቸው በየአጋጣሚው ሁሉ ከመናገር የቦዘኑበት ጊዜም አልነበረም፡፡ በስተመጨረሻም ህልማቸው ዕውን ሆኖ ሦስቱ ልጆቻቸው ሐኪሞች ሆኑ፡፡

አንደኛዋ ልጃቸው ዶ/ር ትዕግሥት ግርማ የአምሬፍ ሔልዝ አፍሪካ የቀድሞ ዳይሬክተር፣ የዓለም ጤና ድርጅት የኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በእነዚህም የአገልግሎት ጊዜያቸው የአገራቸው እናቶች በወሊድ ወቅት የሚደርስባቸው የሞት አደጋ እንደ እግር እሳት ሲያንገበግባቸው ከርሟል፡፡

አገልግሎታቸውን ጨርሰው በጡረታ ከተሰናበቱም በኋላ እናቶችን በተሻለ ለመደገፍ የነበራቸውን የሕይወት ዘመን ህልም ዕውን ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ፈጠረላቸው፡፡ ስለሆነም ከቤተሰቦቻቸው ያገኙትን የከተማ ቦታና የጡረታ አበል ተጠቅመው ለትርፍ ያልቆመ የአዋላጅ (ሚድዋይፍ) ነርሶች ማሠልጠኛ የግል ኮሌጅ አቋቋሙ፡፡

ከየካቲት 12 ሆስፒታል በስተጀርባ የሚገኘውና ባለሦስት ፎቅ ሕንፃ ያለው ይህ የአዋላጅ ነርሶች ማሠልጠኛ የግል ኮሌጅ ግንቦት 17 ቀን 2010 ተመርቋል፡፡ ኮሌጁ የሲሙሌሽን፣ የሌክቸርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍሎችንና ቤተ መጻሕፍት አሉት፡፡ ከዚህም ሌላ የዓለምና የአገር አቀፍን ደረጃዎች ያሟላ ሥርዓተ ትምህርት መቅረፁ ታውቋል፡፡

የኮሌጁ መሥራች፣ ባለቤትና ዳይሬክተር ዶ/ር ትዕግሥት እንደገለጹት፣ የኮሌጁ የሥልጠና ደረጃ ባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ 100 ተማሪዎችን ተቀብሎ በአዋላጅ ነርስነት ሙያ የአራት ዓመት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ከዚህም ሌላ በመጀመርያው የትምህርት አጋማሽ በዲፕሎማ ደረጃ ላሉ የአዋላጅ ነርሶችና ለሌሎም ነርሶች ተቀብሎ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ሙያ እንደሚያሠለጥን ተናግረዋል፡፡

ከዶ/ር ትዕግሥት ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ኮሌጁ የሚያገኘውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ በተለያዩ የገጠር ሥፍራዎች የሚገኙ፣ የደሃ ቤተሰብ የሆኑ፣ ኮሌጁ የሚያወጣውን የመግቢያ መሥፈርት የሚያሟሉና በአዋላጅ ነርስነት ለመሠልጠን ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች እየመለመለ በነፃ ለማሠልጠን ያውላል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት የአዋላጆች ቁጥር 55 ሺሕ እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በአገልግሎት ላይ የሚገኙት 13 ሺሕ ብቻ እንደሆኑና በቂ የአዋላጅ ነርሶች አለመኖራቸው ለሚታየው ከፍተኛ የእናቶች ሞት ዋና ምክንያት እንደሆነ ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡

ዶ/ር አቦነሽ ኃይለ ማርያም የሕፃን ሐኪምና የኮሌጁ የቦርድ አባል ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ከ100 ሺሕ ወላድ እናቶች መካከል 860 ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጉ እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ ቁጥር ወደ 300 ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

ሲስተር የዘብነሽ ክቤ የተባሉት ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹ቀደም ሲል የአዋላጅ ነርሶች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የወሊድ አገልግሎቱ የሚሰጠው በተወሰኑ ነርሶች ብቻ ነው፡፡ ከቁጥራቸውም ማነስ የተነሳ የእናቶች ሞት ቁጥር ከፍ ያለ ነበር፡፡ እንደውም የሞቱ መጠን በአግባቡ ተመዝግቦ አያውቅም፤›› ብለዋል፡፡

የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞት በአሁኑ ጊዜ ቢቀንስም በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም ከፍተኛ ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠት ብቁ፣ በሥነ ምግባር የታነፁና ሩኅሩኅ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የለደግ አዋላጅ ነርሶች ማሠልጠኛ ኮሌጅም ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ለመስጠት በሚያስችል ዘመናዊ የማሠልጠኛ መሣሪያዎች በሚገባ እንደተደራጀ ጠቁመዋል፡፡

የኮሌጁ መጠሪያ ‹‹ለደግ›› ምሕፃረ ቃል ሲሆን፣ ይህም የአያታቸውን የደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ፣ የእናታቸውን የወ/ሮ ደብርነሽ ለጥይበሉና፣ የአባታቸውን የብርጋዲየር ጄኔራል ግርማ ገብረ አምላክ ስሞች የመጀመርያ ፊደላትን የያዘ ነው፡፡

የአዋላጅ ነርሶች ሥልጠና በ1987 ዓ.ም. እንደተጀመረ፣ በአሁኑ ወቅት የአዋላጅ ነርሶች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቶ ከ12 ሺሕ በላይ እንደደረሰ ከሲስተር የዘብነሽ ክቤ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 100 ሚሊዮንን ያለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በመውለጃ ጊዜያቸው ላይ የሚገኙ እናቶች ናቸው፡፡ አሁን ያሉት አዋላጅ ነርሶች ለተጠቀሱት እናቶች በቂ የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት አይቻላቸውም፡፡

ካሉት የአዋላጅ ነርሶች ቁጥር አንፃር ሲታይ ድርሻው አንድ አዋላጅ ነርስ ለ10 ሺሕ ወይም 15 ሺሕ እናቶች ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 43 ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች አዋላጅ ነርሶችን እያሠለጠኑ ያስመርቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...