Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በረዥም ጊዜ ብድር የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት መፈረሙ ተተቸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፣ በዳኒሽ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር አማካይነት ዳኒዳ ቢዝነስ ፋይናንስ በተባለው ተቋም በኩል ለአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል የ201 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት መፈረሙ ትችት አስነስቷል፡፡

መንግሥት የ100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከነፋስ ለማመንጨት ይረዳው ዘንድ ከዴንማርክ መንግሥት ጋር የገባው የረዥም ጊዜ ብድር ስምምነት፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሽርክና ኢንቨስትመንት አሠራር ሊተገበር ጫፍ በደረሰበት ወቅት መሆኑ ነው ትችቱን ያስከተለው፡፡ ሒደቱን የተከታተሉ የሪፖርተር ምንጮች እንዳብራሩት፣ መንግሥት ወደዚህ ስምምነት መግባቱ እየተካሄደ ከሚገኘው የሽርክና ስምምነት አኳያ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይኼውም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ውስጥ ራሱን የቻለ ክፍል ተቋቁሞለት ሥራ የሚጀምርበት ቀን እየተጠበቀ የሚገኘው የዚህ የሽርክና አሠራር፣ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በመሆኑም ሰሞኑን በረዥም ጊዜ ብድር እንዲገነባ ስምምነት የተደረገበት የአሰላ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዚህ ማዕቀፍ ሊስተናገድ ይገባው እንደነበርና መንግሥትም ብቻውን የ201 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ተሸካሚ ከሚሆን ይልቅ በሽርክና ስምምነት መሠረት፣ በራሳቸው የሚያልሙ ኩባንያዎችን ቢያሳትፍ ይሻለው እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት የልማት ሥራ ውስጥ ሳይገባና ጊዜ ሳያባክን አልምተው ሊሸጡለት ከሚችሉ ኩባንዎች ጋር በመደራደር የነፋስ ኃይል ግዥ መፈጸምም ሌላኛው አማራጭ እንደነበር እነዚሁ ተቺዎች ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሽርክና አሠራር ገና ተግባራዊ ካለመደረጉም ባሻገር፣ በኢትዮጵያና በዴንማርክ መንግሥታት መካከል ሲደረግ የቆየ የድርድር ውጤት በመሆኑም በአዲሱ የሽርክና ሥርዓት መሠረት ሊስተናገድ አለመቻሉ እንደማያስገርም ከመንግሥት ወገን ለሪፖርተር ተብራርቷል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሽርክና አሠራር እንዲህ ያለውን የብድር ስምምነትና የፕሮጀክት ግንባታም እንደማይከለከል ተብራርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተፈረመው የብድር ስምምነት ውስጥ 50 በመቶው በዕርዳታ የሚሰጥ ሲሆን፣ የተቀረው የገንዘብ መጠን ግን በረዥም ጊዜ የብድር ስምምነት መሠረት ከዴንማርክ የግል ባንኮች በሚገኝ ፋይናንስ ሊሸፈን እንደሚችል የስምምነት ሰነዱ አመላክቷል፡፡

በዴንማርክ አምባሳደር ሜቲ ታይጂሰንና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ መካከል ባለፈው ሳምንት ስምምነት የተደረገበት የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲህ ያሉ ትችቶችና ምላሾች ቢስተናገዱበትም፣ ከአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሰላ ውስጥ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ግንባታው መካሄድ እንደሚጀመር የስምምነቱ ሰነድ ላይ ሰፍሯል፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. በ2025 እንደሚጠናቀቅ ሲገመት፣ የፕሮጀክቱ የግንባታ ወጪም ከጠቅላላው 201 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 186.4 ሚሊዮን ዶላር ሊጠይቅ እንደሚችል በፕሮጀክት ስምምነት ሰነዱ ውስጥ የተካተተው ሐተታ አመላክቷል፡፡

በሒደቱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሁሉን አቀፍ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ የተሳተፈ ሲሆን፣ የኃይል ማመንጫውን ከማሠራጫዎች ጋር የሚያገናኙና የሰብ ስቴሽን ግንባታዎችን ለማካሄድ የሚውለውን 9.6 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ እንደሚያቀርብም ተጠቅሷል፡፡ መንግሥት ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን መሬት በማቅረብና በፕሮጀክቱ ግንባታ አካባቢ የሚኖሩት ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ በማስፈር ብሎም የካሳ ክፍያ በመፈጸም እንደሚሳተፍ ሲገለጽ፣ ፕሮጀክቱ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው አካባቢያዊ ተፅዕኖ ውስጥ ፕሮጀክቱ በሚገነባበት አካባቢ በሚገኝና ከ30 እስከ 50 ሔክታር በሚደርስ መሬት ላይ የሚገኝ የዕፀዋት ሽፋን ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ተገምቷል፡፡ ይህም ሆኖ በዓመት ከ330 ሺሕ ኪሎ ዋት አወር የነፋስ ኃይል በማመንጨት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገምቷል፡፡ በኪሎ ዋት አወር የ0.10 ዶላር ወይም 2.8 ብር የአገልግሎት ክፍያ ሊጠይቅ እንደሚችልም በፕሮጀክቱ የስምምነት ሰነድ ላይ የሰፈረው ማብራሪያ ይጠቁማል፡፡ ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባ ከ50 እስከ 75 ለሚደደርሱ ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ ሲጠበቅ፣ ፕሮጀክቱ ሌሎችም ከበካይ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ጋር የተያያዙ ተጓዳኝ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ ተነግሮለታል፡፡

ኢትዮጵያ ከነፋስ ኃይል የ1,244 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት ዕቅዷን እንድታሳካ የዴንማርክ መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በ2017 ዓ.ም. መጨረሻ በሁሉም የታዳሽ ኃይሎች መስክ በኢትዮጵያ ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን 17,250 ሜጋ ዋት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በኃይድሮ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች አማካይነት ተመርቶ እየቀረበ የሚገኘው 4,200 ሜዋ ጋት ኃይል ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ከፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ ብድር በ290 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የተገነባውና ከመቀሌ አቅራቢያ አሼጎዳ በተባለው አካባቢ የነፋስ ኃይል የሚያመርተው ፕሮጀክት 120 ሜዋ ጋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዳማ አንድ የተሰኘውና 51 ሜጋ ዋት የነፋስ ኃይል የሚያመነጨው፣ እንዲሁም አዳማ ሁለት የተሰኘውና 153 ሜጋ ዋት የነፋስ ኃይል የሚያመነጨውን ፕሮጀክት አካቶ እስካሁን ከ320 ሜጋ ዋት ያላነሰ የነፋስ ኃይል በአገሪቱ እየመነጨ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥትና የግል ዘርፉ የሽርክና አሠራር ማዕቀፍ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመፅደቁም ባሻገር፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል ራሱን የቻለ አስፈጻሚ አካል እንደተደራጀለት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. መካሄድ በጀመረው የግል ዘርፉ ልማት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ በጠራው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ በእንግድነት የተገኙት ሚኒስትር አብርሃም፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሽርክና ሥርዓት ለአሠራር በሚመች አደረጃጀት ተሰናድቶ ለትግበራ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ይህ አሠራር ከብዙ በጥቂቱ የግል ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር በስምምነትና በአጋርነት በሚያደርጓቸው ስምምነቶች መሠረት በጋራ የማልማት፣ የግል ኩባንያዎች ያለሙትን መንግሥት በመግዛት፣ እንዲሁም በጋራ ባለቤትነትና ባለድርሻነት የሚሳተፉባቸው የልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች