በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ይፋ የሚደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት ዘንድሮ ትኩረቱን በስደተኞች ላይ ሲያደረግ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ ከአፍሪካ 17 ሚሊዮን ሰዎች ወደተለያዩ አገሮች መሰደዳቸውን እንዳመለካተ ተጠቁሟል፡፡
በመጪው ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ይፋ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCATD) ሪፖርት ቅድመ መግለጫ እንዳሳየው ከሆነ፣ ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ከተመዘገቡ 19 ሚሊዮን ስደተኞች ውስጥ 17 ሚሊዮኑ ከአኅጉሪቱ ወደ ሌሎች አገሮች ተሰደው የሄዱ ናቸው፡፡ ይሁንና አፍሪካ ስደተኞችን የምታመነጭ ብቻም ሳትሆን የስደተኞች መዳረሻ ስለመሆኗ ይፋ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ሪፖርት፣ ከ5.5 ሚሊዮን ያላነሱ ስደተኞች በአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደተጠለሉ ስለማመላከቱም ተጠቅሷል፡፡
‹‹ማይግሬሽን ፎር ስትራክቸራል ትራንስፎርሜሽን፤›› በሚል ርዕስ ይፋ የሚደረገው ሪፖርት፣ በተለይ ከአፍሪካ የሚሰደዱ የተማሩ አለያም የሙያ ሥልጠናና ልምድ ያካበቱና በከፊል እንዲህ ያለውን ዕድል ያገኙ አፍሪካውያን በተሰደዱባቸው አገሮች ውስጥ ስለሚገጥሟቸው ጥሩና መጥፎ አጋጣሚዎች ያብራራል፡፡
ስደተኞቹ በውጭ ያካበቷቸው ዕውቀትና ችሎታዎች፣ የቀሰሟቸው ክህሎቶችና ያዳበሯቸው ልምዶች ለአፍሪካ ለውጥ ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚተነትነው ሪፖርቱ፣ በተለይም በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረጉ የስደት እንቅስቃሴዎች በንግድና በልማት ላይ ሊያሳርፉ ስለሚችሉት በጎ ተፅዕኖም ይተነትናል ተብሏል፡፡ ከዚህ በመነሳትም በአፍሪካ የስደትና የስደተኞች ፖሊሲ ሊቀረጽና ሊተገበር እንደሚገባ የፖሊሲ ሐሳብ በማቅረብ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በኩል የሚተገበረውን እ.ኤ.አ. የ2063 የአፍሪካ አጀንዳ የልማትና የኢኮኖሚ ለውጥ ትግበራን እንዲያግዝ የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍ እንዲሆንም ሪፖርቱ ይጠይቃል፡፡
ምንም እንኳ ስደት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ቢባልም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካይነት በሚካሄድባቸው የማታለልና ማጨበርበር ወንጀል ሳቢያ ለሞትና ለከፋ አካላዊ ጉዳት ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ በተለይም ወደ አውሮፓ ለመሻገር በጀልባ የሚሳፈሩ በርካታ ስደተኞች በባህር ሲሰጥሙ የሚያሳዩ ዘገባዎች በሰፊው ሲሰራጩ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ከዚህ ሲከፋም አካላቸው እየወጣ በሕገወጥ የሰውነት አካል አዘዋዋሪዎች የሚደረግባቸው ኢሰብዓዊ ጥቃትም ስደተኞች የሚጋፈጡት የስደት ዓለም ሰቆቃ ነው፡፡
ይሁንና ከስደተኞች ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አኳያ አገሮች የውጭ የሐዋላ ገቢ የሚያገኙበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ምንም እንኳ በውጭ አገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ የሚላከው የሐዋላ ገቢ መጠን አከራካሪ ቢሆንም፣ በመንግሥት የሚገለጸው መጠን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የሚያሳይ ነው፡፡ ከሐዋላ ገቢ ባሻገር ከፍተኛ ዕውቀትና ችሎታ ያካበቱ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መስኮች ሊያደርጉ የሚችሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦም በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
በሕክምና መስክ፣ በምህድስና፣ በኢይሲቲ፣ በሕዋ ሳይንስ፣ በግብርናና በሌሎች በርካታ መስኮች ከፍተኛ ልምድ፣ ዕውቀትና ችሎታው ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነትና አንቱታ ያህል በኢትዮጵያም የልምዳቸውንና የዕውቀታቸውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር ባለመዘርጋቱ አገሪቱ ልታገኝ የሚገባትን ያህል ጠቀሜታ ማግኘት እንዳልቻለች ይታወቃል፡፡
እንዲህ ያሉ እውነታዎች እንደሚያስቃኝ የሚጠበቀው ሪፖርት በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ ሙኪሳ ኪቱዪ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከፍተኛ ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር) ብሎም በኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች አማካይነት ይፋ እንደሚደረግና ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡
ባለፈው ዓመት ይፋ የተደረገው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት ከቃኛቸው ዓብይ ጉዳዮች መካከል የሮቦቶች ወይም የአውቶሜሽን መስፋፋትን የቃኘው ክፍል ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በየጊዜው እየተስፋፋ የመጣው የሮቦቶች ጉዳይ በርካቶችን ከሥራ ገበታቸው እንደሚያሰናብት ቢታመንም፣ ተመድ ግን ሥጋቱ ተጨባጭ አይደለም ሲል መሟገቱ አይዘነጋም፡፡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት እየተስፋፋ የመጣው የአውቶሜሽን አዝማሚያ ወደፊት በኢትዮጵያም ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ሲገመት፣ እስከ 40 በመቶ የሚደርሰው የሥራ ዘርፍ በአውቶሜሽን አማካይነት ሊከናወን እንደሚችል የዓለም ባንክ ያወጣቸው ትንበያዎች ያመላክታሉ፡፡