እንቁራሪቶች በምድርና በውኃ ውስጥ መኖር የሚችሉ ሲሆን፣ እንቁላል የሚጥሉት ግን ውኃ ውስጥ ነው፡፡ ረዘም ባለ ጅራታቸው የሚለዩት እንቁራሪቶች፣ አብዛኛው ኑሮዋቸው በረግረጋማ ስፍራ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቆዳቸው ከደረቀ ስለሚሞቱ ነው፡፡
ሳይንስ ኪድስ በድረገጹ እንዳሰፈረው፣ እንቁራሪቶች ውኃን በአፋቸው አይጠጡም፡፡ ይልቁንም በቆዳቸው ይመጣሉ፡፡ በአፍንጫቸው የሚተነፍሱ ቢሆንም፣ ከሚያስፈልጋቸው አየር ግማሽ ያህሉን የሚስቡት በቆዳቸው ነው፡፡ ምግባቸውን ለመያዝና ለማላመጥ አጣብቆ የሚይዘውንና እንደ ጡንቻ የጠነከረውን ምላሳቸውን ይጠቀማሉ፡፡ ምላሳቸው እንደ ሌሎች ፍጥረታት ከአፋቸው ግርጌ ሳይሆን ከአፋቸው መጀመሪያ ላይ የሚጀምርም ነው፡፡
ዓይናቸውን በእንቅልፍ ሰዓትም ቢሆን አይጨፍኑም፡፡ በአንድ ጊዜ ወደፊት፣ ወደጎንና ወደላይ ማየት ይችላሉ፡፡ ምግባቸውን ለመሰልቀጥም በዓይናቸው ይታገዛሉ፡፡ ዓይናቸውን በማርገብገ አፋቸው ውስጥ ያለውን ምግብ ወደ ውስጥ ያስገባሉ፡፡
በመዝለል ችሎታቸውና በድምፃቸው የሚታወቁት እንቁራሪቶች፣ በመላው ዓለም ይገኛሉ፡፡ በዝርያ ብዛታቸውም በዓለም ከቀዳሚዎቹ ስፍራ ይመደባሉ፡፡ ከ6400 በላይ የእንቁራሪት ዝርያዎች ሲኖሩ፣ የመኖር ዕድሜ ጣሪያቸውም ከአሥር እስከ 12 ዓመት ነው፡፡ ርዝመታቸው እንደዝርያቸው ቢለያይም፣ ከ15 ሴንቲ ሜትር አይበልጡም፡፡
አንዳንድ የእንቁራሪት ዝርያዎች መርዛማ ናቸው፡፡ ከቆዳቸው የሚያመነጩት ፈሳሽም ሰውን የመግደል አቅም አለው፡፡ እንቁራሪቶች ማንኛውም ሕይወት ያለውን ነገር ይመገባሉ፡፡ የአፋቸው መጠን እስከያዘ ድረስ፣ ትናንሽ አሳዎችን፣ ሸረሪቶችን፣ እጭ ትላትልና ሌሎችንም ይመገባሉ፡፡
ሁሉም የእንቁራሪት ዝርያዎች በዝላያቸው የሚታወቁ ቢሆንም፣ የአፍሪካ እንቁራሪት የሚባለውን የሚያህል የለም፡፡ የሳንዲያጐ የእንስሳት መጠበቂያ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የአፍሪካ እንቁራሪት እስከ 4.2 ሜትር ድረስ መዝለል ይችላል፡፡