Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ​‹‹ራሴን በራሴ!››

​‹‹ራሴን በራሴ!››

ቀን:

መሰንበቻውን በተከበረው የጥምቀት በዓል፣ በጃንሜዳ ጥምቀተ ባሕር ለመፀበል ከተገኙ ወጣቶች መካከል አንዱ በእጅ ስልክ ፎቶ ማንሻው ክስተቱን ሲቀርጽ (ፎቶ በናሆም ተስፋዬ)

*****

ትንጎራደዳለች ውበት ተጎናጽፋ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትንጎራደዳለች ውበት ተጎናጽፋ

እንደ ሌላ አገሮች ሌቱ ደመና አልባ

ጨለማውም ይሁን ብርሃኑም የላቀ ከዋክብት የሞላ፤

የተወሃሃዱት ዓይኗን ገጽታዋ

እንደዚህ ስትፈካ በለስላሳው ብርሃን

እግዜር የነፈገው ለጠራራው ቀን።

ቅንጣት ጥላም ትሁን፤ ብታንስ አንዲት ጮራ፤

ግማሽ ያጎድለዋል ያን ስም የለሽ ፀጋ

የተጎነጎነው በጥቁር ጎፈሬ ሹርባዋ ዞማ፤

ወይ ለስላሳው ብርሃን ፊቷ ላይ ያበራ –

የመሠከሩበት ሐሳቦች የጣሙ በጥሞና እርጋታ

ውብም ነው ተወዳጅ ያረፉበት ቦታ።

በዚያች ጉንጭና ቅንድብ ሽፋሽፍት፤

ለስላሳም፤ የረጋ፤ ሆኖም የተሟላ ርቱዕ አንደበት፤

ፈገግታዋ ኃያል፤ ቀለሟ የጋለ፤

ደግሞም የሚያሳብቅ በምሥራች ቀናት በደስታ የዋለ፤

ሰላማዊው መንፈስ፤ ከዚያም በታች ያልፋል፤

የልቧ ፍቅርም በቅንነት ሞልቷል።

 • ከጆርጅ ጎርደን ባይረን/ ነፃ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

 

****

የ48 ዓመቱ ሜኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ

ዘንድሮ የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት እያከበረ ያለው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማኅበር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ48 ዓመት በፊት በዓሉን ካከበረባቸው ቦታዎች አንዱ ገነት ሆቴል ነበር፡፡ ለ32ኛ ዓመቱ ክብር ለሚዘጋጀው ግብዣ ዋጋ ጠይቆ ያገኘውን ምላሽ የያዘው ጽሑፍ ቀጥሎ የተመለከተው ነው፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቲም የተቋቋመበትን 32ኛ ዓመት በሚያከብርበት ሐምሌ 6 ቀን 1960 ዓ.ም. በገነት ሆቴል ለሚያደርገው የቡፌ ምግብ ግብዣ አስፈላጊ የሆነውን ምግብ ለ900 ሰው በሆቴላችን አዘጋጅተን እንድናቀርብ ስለተጠየቅን፣ ከዚህ በታች በዝርዝር ተጽፈው የሚገኙትን ልዩ ልዩ ዓይነት ምግቦች በሚገባ አዘጋጅተን ለማቅረብ በሰው 3 (ሦስት ብር) ሒሳብ የምንጠይቅ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን፡፡

የምግብ ዓይነቶች

 

 1. የበግ ቀይ ወጥ፣ የበግ አልጫ

16. ፌቲኒ ቢስቲካ

 1. ቦዘና ሽሮ

17.  የዶሮ አሮስቶ

 1. ምንቸት አብሽ

18. ዱባ ዶልማ

 1. ጥብስ ወጥ

19. የጎመን ጥቅል

 1. ዶሮ ወጥ

20. የበግ ኮስቴሌት

 1. ሆድ ዕቃ ወጥ

21. የበሬ ኮተሌት

 1. ለምለም ዝግኒ

22. ምላስ ቅቅል

 1. ዝልቦ ጎመን

23. ሩዝ በሥጋ

 1. ደረቅ ሽሮ

24. ሙሉ በግ በፍርኖ ጥብስ

 1.  ቅንጨ

25. የበግ አሮስቶ

 1.  ክትፎ

26. ፓልፔቲ ፍሪቲ

 1.  ዓይብ ከጎመን ጋር

27. እስካሎፒኒ በነጭ ቪኖ

 1.  የህል ቅቤ

28. ፍርምባ

 1.  ርጥብ ሥጋ

29. ፍራፍሬ

 1.  ቀዝቃዛ ምግብ

 

 

 •  

 ከእሥራኤል ወደ ሊባኖስ የበረረ አሞራ በሰላይነት ተጠርጥሮ ተያዘ

የእሥራኤልን ድንበር አቋርጦ ወደ ሊባኖስ የበረረው አሞራ ሰላይ ሊሆን ይችላል በሚል በሊባኖስ ውስጥ መያዙን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው ከሆነ፣ በእሥራኤል እየተመናመነ የመጣውን የአሞራ ቁጥር ለመጨመር ምርምር እየተደረገ ነው፡፡ በመሆኑም አሞራው ከጥብቅ ቦታው እንዲወጣና እንዲበርም ተደርጓል፡፡ አሞራው ሲለቀቅ የቴልአቪብ ዩኒቭርሲቲ መሆኑን ለማሳወቅ የሚያስችል ቀለበት ከእግሩ ላይ የታሰረለት ሲሆን፣ የሚደርስበትን ቦታ ለመከታተልም አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ጀርባው ላይ ተደርጎለታል፡፡ ክንፉ ላይም የእስራኤል ስለመሆኑ መለያ ተንጠልጥሎለታል፡፡

ሆኖም የእሥራኤልን ድንበር አቋርጦ በሊባኖስ ቤንት ጀቤይል ከተማ እንደገባ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ተይዟል፡፡ በጎላን ተራራዎች የአዕዋፋት ተመራማሪ የሆኑት ኦሃድ ሃትዞፍ እንደሚሉት፣ አሞራው በአካባቢው ነዋሪዎች ከተያዘ በኋላ፣ በሚመለከታቸው አካላት ምርመራ ተደርጎበታል፡፡ ሆኖም ለስለላ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አልተገኙበትም፡፡ በመሆኑም ከተያዘበት አካባቢ ተለቋል፡፡

*****

ቀበሮና ጅብ

በአንድ ወቅት አንድ ጅብና ቀበሮ አብረውም እየተጓዙ ሳለ በመንገዳቸው ላይ ጅቡ በሬ ሲያገኝ ቀበሮዋ ላም ታገኛለች፣ ቀጥሎም ጅቡ ቢላዋ ሲያገኝ ቀበሮዋ ደግሞ የታሰሩ ሸንበቆዎች ታገኛለች፡፡ ቀበሮዋም እንዲህ አለች “አንዱ ሸንበቆ ቢጠፋብኝ ሌላውን እጠቀማለሁ፡፡ አንተስ፣ ቢላዋው ቢጠፋብህ ምን አማራጭ አለህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡

ጅቡም “ሸንበቆዎቹን ስጭኝና ቢላዋውን ሰጥሻለሁ፡፡” አላት፡፡ ቀበሮዋም “እሺ” አለች፡፡ ከዚያ ደግሞ “ላሜን ሳርዳት አትጮህም፡፡ ያንተ በሬ ግን ያጓራል::” አለችው፡፡

ጅቡም “እንግዲያው ላምሽን ስጭኝና በሬዬን ልስጥሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ በዚህም ሁኔታ ተለዋውጠው መሄድ እንደጀመሩ ቤት አገኙ፡፡ ጅቡ ያገኘው ቤት አንድ በር ብቻ ያለው ሲሆን፣ ቀበሮዋ ያገኘችው ቤት ግን በከፊል የፈረሰና ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ነበር፡፡

ቀበሮዋም ጅቡን እንዲህ አለችው “ጠላት በዚህኛው ቀዳዳ ቢመጣብኝ በዚያኛው አመልጣለው፣ ሌላ ጠላት በዚያኛው ቀዳዳ በኩል ቢመጣብን በዚህኛው በኩል አመልጣለው፣ አንተ ግን ጠላት በበሩ በኩል ቢመጣብህ በየት በኩል ታመልጣለህ?”

ጅቡም “እሺ እንለዋወጥ፡፡ ቤቴንም ውሰጅና ያንቺን ቤት ልውሰድ::” አላት፡፡ በዚህም ሁኔታ ከተለዋወጡ በኋላ ቀበሮዋ ጅቡን እንዲህ አለችው “አሁን ውሃ ላመጣ ስለምሄድ ላሜ ልትወልድ ትችላለችና ጠብቅልኝ፡፡”

ጅቡም “እሺ” አለ፡፡

ቀበሮዋም ከቤት ወጥታ እንዳለች ላሚቷ በወለደች ጊዜ ጅቡ እትብቱን ወስዶ በበሬው ፊንጢጣ ውስጥ አኖረው፡፡ ቀበሮዋም ከሄደችበት ስትመለስ እንዲህ ብላ ጠየቀችው “ላሜ ወለደች?” ጅቡም “አይ ይህ የኔ ጥጃ ነው፡፡ የኔ በሬ ነው የወለደው::” አላት፡፡ እሷም “በሬ ይወልዳል እንዴ?” ብላ ብትጠይቀው እሱም “አዎ” አላት፡፡ እሷም “አይወልድም::” ብላ ተቃወመች፡፡

ከዚያም ወደ ዳኛ እንሂድ ብለው ተስማሙ፡፡ በመንገዳቸውም አንድ ዝንጀሮ አገኙ፡፡ ጅቡም ዝንጀሮውን “እዚህ ምን እየሰራህ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ዝንጀሮውም “ውሃ እየቀዳሁ ነው::” ብሎ መለሰለት፡፡

በመቀጠልም ጅቡ “ውኃ ከድንጋይ ላይ ይቀዳል እንዴ?” ቢለው ዝንጀሮውም መለስ አድርጎ “ጥጃስ ከበሬ ይገኛል እንዴ?” ብሎ መለሰለትና በዚህ ሁኔታ ጅቡ ተሸነፈ፡፡

 • ተራኪው የማይታወቅ የአፋር ተረት
 •  

ውርጃ በማይፈቀድባት ኤል ሳልቫዶር ሴቶች እስከ 2018 እንዳይወልዱ ተጠየቁ

ባለፉት አራት ወራት 4,000 ያህል የዚካ ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውና ይህም የቫይረሱ ተጠቂዎች በሚወልዷቸው ሕፃናት ላይ የአዕምሮ መታወክ እንደሚያስከትል መታወቁን ተከትሎ፣ የኤል ሳልቫዶር መንግሥት የአገሪቱን ሴቶች እስከ 2018 ልጅ እንዳይወልዱ ጠየቀ፡፡

በኤል ሳልቫዶር ውርጃ የተከለከለ ነው፡፡ በአገሪቱ የሚኖሩ ሴቶች ተደፍረው እንኳን ቢያረግዙ፣ ማስወረድ አይፈቀድላቸውም፡፡ አንዳንድ ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር አስወርጿቸው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በኤል ሳልቫዶር ሦስት የዚካ ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ተከትሎ መንግሥት የአትውለዱ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ የሴት መብት ተሟጋቾች ውርጃ ይፈቀድ ሲሉ የመደራደሪያ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ቢቢስ እንደዘገበው፣ በሽታው የሚተላለፈው በወባ ወይም በዳንጉ ትንኝ ነው፡፡ በሰዎች ንክኪ የማይተላለፍ ቢሆንም፣ በእርግዝና ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋል፡፡ ቫይረሱ በእርግዝና ወቅት የጽንሱ አዕምሮ በአግባቡ እንዳያድግና እንዲዛባ ያደርጋል፡፡ የአዕምሮን ዕድገት በማቀጨጭም ለሞት ይዳርጋል፡፡ በሌላ በኩል ጭንቅላት ከመጠን በላይ እንዲያድግ፣ አዕምሮ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሠራም ያደርጋል፡፡

የዚካ ቫይረስ እየተስፋፋ መሄድን ተከትሎ የአሜሪካው የበሽታዎች መቆጣጠሪያን መከላከያ ማዕከል፣ 20 በሚሆኑ የደቡብ አሜሪካ፣ የማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም የካሪቢያን አካባቢዎች የጉዞ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...