Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሓሸንጌና ሕጉምብርዳ

ሓሸንጌና ሕጉምብርዳ

ቀን:

በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በይበልጥም ከጥንታዊው ሥልጣኔ ጋር ተያይዘው ከሚጠቀሱ ቅርሶች መካከል የአክሱም ሐውልቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ወድቆ የሚገኘው ከሐውልቶቹ ረዥሙና ግዙፉ፣ 33 ሜትር ርዝማኔና 520 ቶን ክብደት አለው፡፡ በዓለም ላይ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተሠርተው ከቆሙ ሐውልቶችም ግዙፉ ነው፡፡

ይህን ሐውልት በመጠን አንሶ የሚከተለው፣ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ (1928-1933 ዓ.ም.) ተወስዶ ጣሊያን ሮም አደባባይ ቆሞ የነበረና ከዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው እንዲሁም የተቀሩት ሐውልቶች በሦስተኛውና አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሠሩ ይገመታል፡፡ አክሱምም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ኃያላን ከነበሩት ግብፅ፣ ሮምና ፋርስ (ፐርሽያ) ግዛቶች አንዱ እንደነበረ ታሪክ ያትታል፡፡

በትግራይ ክልል ከፍተኛ ጎብኚዎች ካሏቸው ሥፍራዎች በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ ስለ ትግራይ በጽሑፍ ያገኘናቸው መረጃዎች፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ የሚያሳዩ ቅርሶች በብዛት የሚገኙበት ክልል እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡ የይሓ ቤተ ምኩራብ፣ የሳባውያን ጽሑፍ የተቀረፀባቸው ልሙጥ የሃንዛት፣ የመላዞ ሐውልት፣ የስቀራና የአዲ አከውሒ (መቓብር ጋውኣ) ቁፋሮ ቦታዎችና የንግሥተ ሳባ ቤተ መንግሥት ከሚጠቀሱት ጥቂቱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአህመዲን ነጃሺ መስጊድን፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ከተፈጥሯዊ ሀብቶች መካከል ደግሞ የገርአልታ፣ ዓድዋ፣ አምባላጌና ግራካሕሱ ተራሮች ይጠቀሳሉ፡፡

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 665 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ወይና ደጋማዋ ማይጨው ከተማ የተፈጥሮ ሀብት ከተቸሩ የትግራይ አካባቢዎች ውስጥ ትጠቀሳለች፡፡ ከተማዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩ አገዛዞች ሥር የተከሰቱ በርካታ ታሪኮች ባለቤት ናት፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ከፋሺስት ጣሊያን ጋር ያደረጉት ጦርነት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በ1928 ዓ.ም. የፋሽስት ጣሊያን ሠራዊት ኢትዮጵያውያንን ድል የነሳበት ስፍራም ይኸው ነው፡፡ በአካባቢው የተሰውትን ለመዘከርም ቅሪተ አካላቸው የሚጐበኝበት ሙዚየም ተዘጋጅቷል፡፡

ወደ ከተማዋ የሚወስዱ መንገዶች፣ ከመቐለ ወደ ማይጨው ያለውን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፣ ተራራማ ናቸው፡፡ የመልክዓ ምድሩ አስቸጋሪነት ከጣሊያን ጦርነት በተጨማሪ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትግል ጋርም ተያይዞ ይነሳል፡፡

ከከተማው በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ያሉት የሓሸንጌ ሐይቅና ሕጉምብርዳ ደን ተፈጥሯዊ መስህቦች ናቸው፡፡ ስለአካባቢው ያገኘነው መግለጫ፣ ተራማማው አካባቢ ከፊል ደጋማና ነፋሻ ሜዳማው ደግሞ ቆላ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

ከከተማው 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የበርካታ እንስሳትና ዕፀዋት መገኛ የሆነው የሕጉምብርዳ ደን ይገኛል፡፡ ደኑ ውስጥ በርካታ አገር በቀል ዕፀዋት ያሉ ሲሆን፣ የአፍሪካና አውሮፓ ስደተኛ አዕዋፋትም ይገኛሉ፡፡

ስለ ሕጉምብርዳና በዛው አካባቢ የሚገኘው ግራካሕሱ ደን አስመልክቶ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከ102 በላይ የሚሆኑ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዕፀዋት ተገኝተዋል፡፡

ጥናቱ የተፈጥሮ ሀብት ይዞታቸው እየቀነሱ ከመጡ አካባቢዎች አንዱ ትግራይ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ዕፀዋት በተሻለ ይዞታ የሚገኙት፣ መቁረጥ በተከለከለባቸው ጥብቅ ሥፍራዎችና በሃይማኖት ቦታዎች እንደሆነም በጥናቱ ተገልጿል፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት የእንጨት መሰንጠቂያ ገብቶ፣ ደኑ እንደተጨፈጨፈና ቀድሞ ከነበረው ይዘቱ እንደተመናመነም ጥናቱ ያሳያል፡፡

ወደ 21,654 ሔክታር እንደሚሸፍን የሚነገርለትን ይህን ደን አልፈው ጥቂት እንደተጓዙ፣ የአገሪቱ የደጋ ሐይቅ የሆነውን ሓሸንጌን ያገኛሉ፡፡ ሐይቁን የሚያዋስነው ሰፊ ሜዳ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን የሚመግቡበትና የሚያቆዩበት ቦታ ነው፡፡ በአቅራቢያው የእርሻ ስፍራም ይገኛል፡፡ ሐይቁ እስከ 2,069 ሜትር ከፍታ ባላቸው ተራሮች መካከል ክብ ሠርቶ መገኘቱ ማራኪ እንዳደረገው ይነገርለታል፡፡ በእሳተ ገሞራ አማካይነት የተፈጠረው ሓሸንጌ፣ ወደ 1,668 ሔክታር ስፋትና 19 ሜትር ጥልቀት አለው፡፡

ሐይቁን በስተደቡብ ከሚያዋስነው ተራራ አጠገብ በደን የተሸፈነው የማርያም አዲ ጎሎ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በሐይቁ ጠርዝ ላይ ምፍሳስ ባህሪ የተባለ የአርኪዎሎጂ ቦታ አለ፡፡ በስድስተኛው ወይም በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሠሩ ቤተ ክርስቲያኖች እንዳሉም ይነገራል፡፡

የአርኪዎሎጂ ቦታው ስለአካባቢው ጥንታዊ ሥልጣኔ የሚያስረዳ እንደሆነ ስለ ሓሸንጌ የሚያወሱ ጽሑፎች ያስነብባሉ፡፡ ሐይቁ እንደ ሕጉምብርዳ ደን ሁሉ የአገር በቀልና ስደተኛ ወፎች ማረፊያ ሲሆን፣ በአካባቢው በትግርኛ ‹‹ፀኣዳ ባህሪ›› እንደሚባልም ይነገራል፡፡ በአህመድ ኢብን ኢብራሒም አልገአዚ (ግራኝ አህመድ)፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በጣሊያን ወረራ ወቅትና በሌሎችም አጋጣሚዎች በሐይቁ ዳርቻ ሕይወታቸውን ያጡ ብዙዎች ናቸው፡፡

ሐይቁ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ ባለሙያዎች በርካታ ሲሆኑ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኧርዝ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተመራማሪዎች ሥራዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የፓሊዮ ኢንቫይሮመንታል ኤንድ ሔሪቴጅ ኮንሰርቬሽን ትምህርት ክፍል በድረገጹ እንዳሰፈረው፣ አካባቢው የአርኪዮሎጂ ቦታ መሆኑ በይፋ የታወቀው በ1989 ዓ.ም. ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና አርኪዮሎጂስቱ አቶ ተክሌ ሐጐስ በተባሉ  በ2005 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ጥናት፣ በአካባቢው ስላለው ሀብት እንዳስገነዘበና ዩኒቨርሲቲው ከ2006 ዓ.ም. በኋላ በአካባቢው ጥልቅ ጥናት ማድረግ እንደጀመረም ተመልክቷል፡፡ በምፍሳስ ባህሪ የአርኪዎሎጂ ቦታ የሸክላ ሥራ ውጤቶች፣ የብርና የድንጋይ የዕደ ጥበብ ውጤቶች እንዲሁም የሰዎችና እንስሳት ቅሪቶች ተገኝተዋል፡፡

በአካባቢው ካሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶች በተጨማሪ እንደ ጠመዞ ማርያምና አባ ጉባ ያሉ ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያኖች ይገኛሉ፡፡ የደቡብ ዞን ባህልና ቱሪዝም አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ታረቀ እነዚህን ጠቅሰው እንደሚናገሩት፣ ሐሸንጌ ሐይቅና ህጉምብርዳ ደን ከሌሎች የአካባቢው መስህቦች በበለጠ ጎብኚ አላቸው፡፡ የአርኪዎሎጂ ቦታዎቹና ገዳማቱ ካላቸው አቀማመጥ አንፃር ለጎብኚ ምቹ እንዳልሆኑም ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው የመሠረተ ልማት ሲሟላ ለውጥ እንደሚታይ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

የአገሪቱን የሥልጣኔ ታሪክ ከማመላከት በተጨማሪ በርካታ ጎብኚዎችን መሳብ የሚችሉት እኒህ የተፈጥሮ ቦታዎች ካላቸው እምቅ ሀብት አንፃር ተደራሽነታቸው ሰፍቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በቦታው በተገኘንበት ወቅት ብዙ ጎብኚዎች አልነበሩም፡፡ ወደ ሁለቱም የተፈጥሮ መስህቦች የሚወስደው መንገድ የተመቸ ቢሆንም፣ ሐሸንጌ ሐይቅ አካባቢ፣ ከሐይቁ ውጪ ጎብኚን የሚስብ ነገር የለም፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከውጪ አገር ተቋም ጋር በመተባበር ጥናት በሚያካሂድበት የአርኪዎሎጂ ቦታ ብዙ ግኝቶች እንደተገኙ ይናገራሉ፡፡ በተለይም የአክሱም ሥልጣኔን የሚያመለክቱ በአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ለተመልካች እይታ የሚቀርቡበት ሙዚየም የማሠራት ዕቅድ እንዳለም ገልጸዋል፡፡

በሐሸንጌ ሐይቅ ዙሪያ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ ባለሀብቶች እንዳሉም ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ቦታው ምቹ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን፣ ለጎብኚዎች ማረፊያ ሎጆችና ሆቴሎች የመገንባት ዕቅድ እንዳለም ያክላሉ፡፡ ‹‹አካባቢውን በቱሪዝም መስህብነት ልንጠቀም የምንችልበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፤›› ይላሉ፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶቹን ጠብቆ ማቆየትን በተመለከተም፣ አቶ ዳዊት ለሐይቁና ለደኑ ብቻ ተነጥሎ የተቀመጠ ጥበቃ ባይኖርም፣ ሁሉም የተፈጥሮ ሀብቶች በሚደረግላቸው ጥበቃ ስር ይካተታሉ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...