– ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች ተወገዱ
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ማዕከላዊ ላቦራቶሪው በሚያካሂደው የመድኃኒት ጥራት ምርመራ ሥራ ላይ፣ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተቋቋሙ የፋርማሲ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር የሚገኙ ላቦራቶሪዎችን ለማሳተፍ የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየሱን አስታወቀ፡፡
አቶ ጌታቸው ገነቴ በባለሥልጣኑ የመድኃኒት ጥራት ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ የትምህርት ቤቶቹ ላቦራቶሪዎች በምርመራው ሥራ እንዲሳተፉ የሚደረገው፣ የዓለም ጤና ድርጅት ወይም ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ድርጅቶች ዕውቅና ማግኘታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የተለያዩ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ አኳያ በሚቀጥለው ዓመትና ከዛ በኋላ በጥራት ምርመራው ሥራ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሌሎች አገሮች ላቦራቶሪዎችም በዚሁ ሥራ እንዲሳተፉ የሚጋበዙት አካሄድ የተቀየሰ ሲሆን፣ የጥቅም ግጭት እንዳይከሰትም የአሠራር ሥርዓት ይዘረጋል፡፡
ከዚህም ሌላ የመሥሪያ ቤቱን አራት የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላቦራቶሪዎችን አቅም በማሳደግና ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ሥራው ሙሉ ለሙሉ እንዲገቡ የማድረግ እንቅስቃሴም ከተያዙት የስትራቴጂ አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሥራው እንደተጀመረና ባለሥልጣኑም ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላቦራቶሪዎች መሣሪያዎችን በመገጣጠም፣ ባለሙያዎችን በኮንትራትና በቋሚነት በመቅጠር፣ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በተለያዩ ወቅቶች የጥራት ግድፈቶችን የሚያነሳ መሆኑን አስመልክቶም፣ ችግሩ እንዳለ ሆኖም መቶ በመቶ ሊቀንስ እንደማይችል፣ ጥራት የማስጠበቁ ሥራ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በመድኃኒት ጥራት ምርመራ ላይ ሌሎች ላቦራቶሪዎችን አሳታፊ የሚያደርግ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችን ሊቀይስ የቻለው፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ አምስት ሺሕ የሚጠጉ መድኃኒቶችን ለመመዝገብ በማቀዱ፣ ለዚህም ስኬታማነት በዓመት በቡድን እስከ 75 የመድኃኒት ዓይነቶችን ደረጃ ላይ የድረ ገበያ ጥራት ማከናወን ስለሚኖርበትና ይህን ዓይነቱን ግዙፍ ሥራ ለማከናወን የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማዕከላዊ ቤተ ሙከራ በሠለጠነ የሰው ኃይልና በሌላም ያለው አቅም ውስን ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከየካቲት 2007 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2008 ዓ.ም. ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ፣ ሦስት ሚሊዮን 62 ሺሕ 926 ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ መድኃኒቶች እንዲወገዱ ወይም እንዲመለሱ መደረጉን ወይዘሮ ሰብለ ሻምበል የባለሥልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ተናግረዋል፡፡
መድኃኒቶቹ እንዲወገዱ ወይም እንዲመለሱ የተደረጉበትም ምክንያቶች፣ በባለሥልጣኑን መሥሪያ ቤቱ ከተመዘገቡት መድኃኒቶች ውጭ ሆነው በመገኘታቸው፣ ከተገቢው የማቀዝቀዣ ሰንሰለት ውጪ በመቀመጣቸውና በዝናብ ምክንያት በመበላሸታቸው ነው፡፡
በምርቶቹ ላይ የጥራት ችግር መታየቱ፣ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜያቸው በምዝገባ ወቅት ከነበረው የተለየ ሆኖ መገኘቱ፣ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና የተቃረበ ሆነው መገኘታቸውና አስፈላጊው መግለጫ በምርቶቹ ላይ አለመኖር ለመወገዳቸው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡