Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የፖለቲካና የሚጥሚጣ ትንታ!

ሰላም! ሰላም! ናፍቆትና ጥርጣሬ አቀራርበው ባራራቁን ጎረቤቶቻችን ሠፈር ሁለት ሁለት ሚስት ለባሎች እንደ ኩፖን በአዋጅ መታደል ተጀምሯል ሲሉ ሰማሁ። “እኔ ምለው? ምንድነው እንደዚህ አዳሜ ባልተያዘ ባልተጨበጠ ወሬ የራሱን አሳንሶ የሰው የሚያገዝፈው?” ብዬ ባሻዬን ብጠይቃቸው፣ “የባሰ ካልሰማህ መቼ ያለህን ታመሰግንና?” ብለው አለፉት። እኔ ስለዴሞክራሲ እንደማወራ እሳቸውም ስለአምባገነንነት እንዳወሩ ሳንግባባ ተለያየን። ኧረ እንኳን ተለያየን! የሚገርመኝ አንዳንዴ በሰው ሕመም የታመምን መስለን እኛ ለራሳችን የምንጨምቀው ሐሴት አለን ልበል? እንደ ባሻዬ ልጅ ምሁራዊ አተናተን “ሳይኮሎጂካል ሱፒሪየሪቲ’ ይባላል” ብሎኛል። ‘አልገባኝም’ ልለው እጄን ሳወጣ በርግጎ ሞያሌን ነክቶ ሊመለስ ነበር። መመለሱንም እኔ እንጂ እሱ ያቀደው አልመሰለኝም ለነገሩ። ኋላ “ምን ያስበረግግሃል? በየት አገር ነው ተማሪ እጁን ሳያወጣ ጥያቄ የሚያቀርበው?” እለዋለሁ፣ “ለጊዜው እሱን ዝለለውና እንደለመድነው እንሾካሾክ” አለኛ። ዋዛ አድርጋችሁታል?!

“ታዲያ በሚገባኝ ቋንቋ እንደማስረዳት ‘ሳይኮ’ ምናምን እያልክ ምን እንደ ውዝፍ ግብር ራስ ምታት ታሸክመኛለህ?” ስለው ደግሞ፣ “በቃ እሺ በአጭሩ ‘በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት’ በሚለው ያዘው፤” ብሎ ጥሎኝ ሄደ። አይዟችሁ ሞያሌ አይደለም! እንኳን ምሁርነቱን የማልጠረጥረውን ወዳጄን ትርጉም፣ በልጅነቴ በየቪዲዮ ቤቱ የስንቱን ህንድ ፊልም ትራጀዲ ትርጉም አምኜ ቦሊውድን አሳድጊያለሁ ብዬ አመንኩታ። አንዳንዴ እኮ ከማመን የበለጠ አማራጭ መፍትሔ የለንም። ያውም አማራጭ ፖሊሲና ‘አይዲዮሎጂ’ ይዞ የሚያሳምን ተቃዋሚ በናፈቅንባት አገር? እንዴ? የያዝነውን ይዘን ማልቀስ ነው እንጂ ጎበዝ! ዓይናችን እንደሆነ እንኳን በዚህ በቦሊውዱም ኦቴሎ አልጠፋ። ምናልባት ደግሞ ወደፊት ዴሞክራሲያችን ሲጎለብት እንባችንም የሚገደብበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። ይሆናል አልኩ ይቅርታ አድርጉልኝ። ስለእምነት እየሰበኩ ጥርጣሬን መዝራት መቼም በእኔ አልተጀመረም። እንዲያው ብቻ እስከዚያው ድረስ የባሰውን እየመረጥን የባሰንን መርሳት ባንለማመድ ሸጋ ነበር። ወጉ ባይቀርብኝ ግን እናንተ ምን ጨነቃችሁ?!

ነበር ካበዛሁባችሁ በድጋሚ ይቅርታ አልጠይቅም። ምንም ቢሆን ስለነበር ከእኛ በላይ ብዙ የከተበ የለም ብዬ ነው። የሦስት ሺውን ትቼ የእኔን የሰላሳ ዓመት ትውስታ ላጫውታችሁ። ቅድም የባሻዬ ልጅ ‘ሳይኮሎጂ’ ያላት ቃል የገባውም ያልገባውም ያጠናትም የኮረጃትም እንዲሁ በጅምላ ሲደጋግማት ስሰማት ለምን እንደሆነ እንጃ፣ ጎረምሳ ሳለሁ በሳይክል ጋላቢነት የሠፈሬን ወጣት ልብ ያሸፈትኩበት ዘመን ነው ትዝ የሚለኝ። ለነገሩ ያኔ መሸፈትም ማሸፈትም ቀላል ነበር። እንዳሁኑ ጠበቅ አላለም። ማለቴ የዘንድሮ ልጅ ‘ጓደኛዬ ሳይክል ጋለበ’ ብሎ ጀሌው የሚሆንበት ዘመን አይደለም ለማት ፈልጌ ነው። ከፖለቲካ ውጪ መጫወት አይቻልም እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ! የዘንድሮ ልጅ ሲጀመር . . . ብስክሌት መጋለብ አይደለም ወጥቶም በእግሩ መሮጥ የታከተው ይመስላል። የሚያስቀምጥ ነገር በዝቷላ። ደግሞ ማን ከማን አንሶ እየተባለ ወላጅ ከወላጅ ሳንቲም የመዝራት አቅም በሚለካካበት በዚህ ዘመን፣ የትኛው ልጅ ነው ጓደኛው ሳይክል ጋልቦ እሱን ቅናት ሲጋልበው የሚያድረው? እውነቴን ነው እኮ። መጪው ትውልድ እኮ ዕድለኛ ነው። የጠየቀው ሁሉ ሳይሟላለት አይድርም። የወላጅ ጥያቄ ግን ተከድኖ አድሮ ተከድኖ ይውላል። ‘ዚስ ኢዝ ሳክሪፋይስ!’ ብለን እንለፈውና አብረን ሳይክል እንጋልብ።

ያው የምታውቁ እንደምታውቁት በእኛ ዘመን ደግሞ ሳይክል መጋለብ በ‘ዱርዬነት’ ያስፈርጅ ነበር። ‘ባይዘዌ’ ፍረጃን ከሕዝብ ያልተማረ መንግሥት የትም ዓለም የለም። ከእኛም በፊት ካላችሁ ደግሞ ሳይክል አገራችን መሬት ላይ በቀጭን ጎማዋ ሽር ማለት ስትጀምር ‘ስፒሪቹዋሊ’ በዲያቢሎስ ሥራ ታውጃ ‘ሶሺዎሎጂካሊ’ የጋለባትን አስገልላ ነበር ይባላል። “መቼ እኛ የምንጋልበው እንወዳለን የሚጋልበን እንጂ?” ያለው የባሻዬ ልጅ ነው። ይኼን አባባሉን ባሻዬ ዳዊት እየደገሙ በማስተጋባቱ ፀበል ካዘዙለት ይኼው አራት ቀኑ ነው። አፍና ልቦና ሥራቸው ተቀራራቢ መሆኑን ከመጽሐፉ እንጂ ከሲግመን ፍሮይድ ስላልቀሰምን ፀበል ‘ሳይኮ ቴራፒያችን’ ነው ብንል እንስት ይሆን? ትርጉም ከፈለጋችሁ የባሻዬን ልጅ ፀበል ሲጨርስ ጠይቁት። አደራ ትርጉም ይገላል ብላችሁ የማታምኑትን ብቻ ይመለከታል ማስታወቂያው!

እና ምን ነበር የምናወራው? በየት በየት አድርጌ ብጋልብ ነው ፀበል የረጨኋችሁ? ግድ የለም እሺ አሁን ወደ ገደለው ገባሁ። እንደለመድኩት አንድ ቀን ሳይክል ተከራይቼ ሳሽቀበንን ለካ ሳይታወቀኝ ከሠፈሬ ርቄያለሁ። ኋላ ሳስበው ግን አብዮት ጠባቂዎች ስላስቆሙኝ አገሬን ለቅቄ የማላውቀው አገር ድንበር የገባሁ መስሎኝ እንጂ የትም አልሄድኩም። ትዝ ይለኛል ሁለት ረጃጅም ወጠምሻ መለዮ ለባሾች ነበሩ ያስቆሙኝ። ክው ብዬ ዓይን ዓይናቸውን አያለሁ። እነሱ እኔን አስቁመው የለየለት የተራማጅና የአድሃሪ ክርክር ገጥመዋል። አንዱ “ብስክሌት መንዳት የተራማጅነት ምልክት ነው። ከተራማጅነትም አልፎ አብዮቱ በተቀላጠፈ ፍጥነት እንዲጓዝ የሚያስብን ብሩህ ንቃት የታደለ ወጣትን ይገልጻል፤” ይላል። ያኛው “የሠራተኛው መደብ ትግል በላቡ፣ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ በተመሠረተ ተፈጥሮአዊና ጠንካራ ዜጋ ትግል እንጂ፣ ስሜትን እያነሆለለ የሩቅ ግብና ዓላማን በሚያድበሰብስ ‘ሜካኒካዊ ቁስ አካል’ አይሰምርም፤” ይላል።

በመሀል እኔ ያለሁበትን አላውቅ የምጋልበውን አላውቅ የሚጋልበኝን አለይ፣ በድን በሉኝ ምን አለፋችሁ። መጨረሻዬ ናፈቃችሁ መሰለኝ? እህ . . . እንዲያ ካለ እሰጥ አገባ በተዓምር ካልሆነ በምን ልተርፍ ኖሯል? ተፋጠው እንኳን እነሱ አንጃዎቹ መሪዎቻቸው በቅጡ ባላጠኑት ፍልስፍና እየተነታረኩ ሲረሱኝ እግሬ አውጪኝ ብዬ ተፈተለኩ። አታምኑኝም ከዚያ ወዲህ ሳይክል ጋልቤ አላውቅም፡፡ አገላለቡም እንደተደናገረኝ አለሁ። አሁን በቀደም ረጅም የታክሲ ሠልፍ መሀል ትንኝ አክዬ ‘ኤክስኪዩቲቭ’ የማሻሽጣቸው ደንበኞቼ ዘገየህ እያሉ ሲጮሁብኝ ብቻ ተማረርኩ። “ሳይክል ልግዛ ይሆን?” ብዬ አሰብኩ። ኋላ ደግሞ አዙሬ ሳስበው እንኳን በሳይክልና በመኪና በእግር መተላለፍ ባቃተን ጎዳና ላይ ትናንት ኑር ብሎኝ ያመለጥኳት ቀኔ ዞራ ብትመጣስ ብዬ ተውኩት። ብታድሩ፣ ብትራመዱ እለፍ ካልተባላችሁ መቼ ታልፉና ዘንድሮ? አይደል እንዴ?

ደግሞ ምን ሆነ መሰላችሁ? ያን ያልኳችሁን ‘ኤክስኪውቲቭ’ አሻሽጬ (አሁን እንኳ ሁለት ፐርሰንቴን ብቻ ሳይሆን የትራንስፖርቱን እንግልት ታሳቢ ያደረገ ኮሚሽን መቀበል ጀምሬያለሁ) “ያበደ ባለሁለት መኝታ ኮንዶሚኒየም አለ፤” ተብዬ ተደወለልኝ። ‘ኮንዶሚኒየም ካበደ ማንን ተስፋ ልናደርግ ነው?’ በውስጤ እያልኩ ሄድኩ። እውነቴን እኮ ነው። በቀደም ከባሻዬ ጋር ስለዚህ ግነታዊ የግብይት ሥርዓት ስንጫወት፣ “እኔ እኮ ምለው” ብለው ጀመሩ። ሲቀጥሉ፣ “በቀደም ከዚህ ጎረቤታችን ካለው ሱቅ ስኳር ልገዛ ሄድኩ። እኔ ስኳር ሱቅ አትፈልጉኝ ማለቷን መቼ አወቅኩና? ኋላ ‘እንዲያውም ምንም የለህም?’ ስለው ኮብልስቶን በመሳሰለ ቅርፅ ታሽጎ የሚሸጥ ስኳር አመጣና ‘ይኼ ያበደ ስኳር ነው። ይመቼዎታል’ አይለኝ መሰለህ? መቼ ዕለት ደግሞ ያው እንደ ልማዷ ውኃ፣ ውኃ ጠምቷት ነው መሰል እልም ብላ ስትጠፋ ጉሮሮዬ አድርጎት የማያውቀውን ክው ብሎ ደረቀ። አይ ባሻዬ ወንዱ! አረጀሁልህ እኮ አንበርብሬ! አሁን እኔ በዱር በገደሉ እየገባሁ ፋሽስትን ያባረርኩ እመስላለሁ? ይኼውልህ ዘመን ወንዙን አድርቆ፣ ቧንቧዬን አዘግቶ፣ ታሽጎ የሚሸጥ ውኃ ላይ ጣለኝ። ኋላ (ይኼ ባለሱቅ መቼም አፉ ጤፍ ይቆላል) ‘እስኪ ብዙ ሰው የሚጠቀመውን የታሸገ ውኃ ስጠኝ’ ብለው ፊቱ ያገኘውን ብድግ አድርጎ ‘ባሻዬ ገና እንደቀመሱት ወደ እኔ ይምጡ። ያበደ ነው ስልዎት’ አይለኝ መሰለህ?” ብለው ትንፋሽ ሰብስበው ሲያበቁ፣ “እኔ ምልህ ግን አንበርብር . . . ውኃው አብዶ፣ ስኳሩ አብዶ፣ የሚሸጥ የሚከራየው ቤት አብዶ፣ የምንበላው አብዶ፣ የምንጠጣው አብዶ  . . . የኋላ ኋላ እኛ ደህና የምንቀር ይመስልሃል?” አሉኝ። ምኑን አውቄ ባሻዬ! ምኑን አውቄ!

እንሰነባበት? “እውነትም እንደተባለው ያን ያበደ ባለሁለት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር አሻሻጥኩት። ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ቤቱ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ወጥቶበት ታድሷል። ኩሽናው ክፍትና ተለጣፊ ዕቃ መሰነቂያ ያለው ሆኖ ተደራጅቷል። መታጠቢያ ቤቱ ተቆፍሮ እንደ አዲስ በገንዳ ዘንጦ ተሠርቷል። እያንዳንዱ በር ከሰላሳ ሺሕ ብር በታች የማይገመት ዋንዛ እንጨት ሥሪት ነው። ተሸጠ በዘጠኝ መቶ ሺሕ። ካለ ምን ጣጣ አለ፤” እያልኩ ለማንጠግቦሽ ስነግራት፣ “ምናለበት እሱ ቢቆይህና ልብስህን ለባብሰህ ብንወጣ፤” ብላ ተማረረችብኝ። ለካ ሠርግ ተጠርተናል። ሰው ለስንት ክፉ ነገር በሚጠራበት ዘመን ማን የሞላው ነው ደግሶ የጠራኝ አላልኩም። ይብላኝ አጠገቡ ያለን አክባሪውን እየረሳ የግለሰብ መብቴ አልተከበረም እያለ ለሚዘፍን። ሽክ ብዬ ሚስቴን በጉያዬ ሸጉጬ ፌሽታው ላይ ደረስኩ። መብሉ ሳይነሳ በየጠረጴዛው ላይ የቀረበው ውስኪ ሳይከፈት ምን እንደምሰማ ታውቃላችሁ? እኔማ ማንጠግቦሽ አብራኝ ኖራ ባትታዘብ እኒያን አብዮት ጠባቂዎች በሕይወት ካሉ አፈላልጌ አምጥቼም ቢሆን በታዛቢነት እሾም ነበር። የዘንድሮ ታዛቢ ደግሞ በጀቱ ካልፈቀደ አይገኝም። እንዴ! አሁን እስኪ ማን ስለአውሮፓ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን አወራ? በግድ ነው እንዴ!  

 የዳሸን ተራራን የሚያስንቅ ሳህኑ ላይ የቆለለ የሠርጉ ታዳሚ፣ “ስማ ልጅቷን አላውቃትም ነው የምትለኝ? የለየላት አጭቤ እኮ ናት። አላወቀም እሷ እንዳቀፈችው፤” ሲል ሙሽሪትን ያማል። ያኛው፣ “እሱስ ቢሆን በዚህ ዕድሜው ይኼን ያህል ገንዘብ ከየት አምጥቶ ነው? አድናቂዋ ነኝ። ዜሮ ባይደረድር እኮ ሚሊዮን አንድ ሁለት ሦስት ነበር። ይኼም ድህነት ቅነሳ ነው። ይመቻት፤” ሲል ጆሮዬ ጥልቅ። “ማንጠግቦሽ ምንድነው የሚያወሩት?” ብዬ ዘወር ስል የጎረሰችው ክትፎ ሚጥሚጣው በአፍንጫዋ መጣ። በሰው ሚጥሚጣ የሰው ስም ሲደለዝ እያየሁ ሳሽሟጥጥ የራሴ ብሶ ቁጭ። እኔስ ፈጣሪ ምሮልኛል። እስኪ እናንተም የራሳችሁን ተከታተሉ። ኋላ በትንታ ዋጋ እንዳትከፍሉ። የዘንድሮ ሚጥሚጣና ፖለቲካ ትንታው አይቻልም! መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት